Wednesday, 27 January 2016

ጥንቁቅነት፣ ቆራጥነትና በአላህ መመካት

ጥንቁቅነት፣ ቆራጥነትና በአላህ መመካት
ነፍሲያ፣ የሰው ሰይጣናትና የጂን ሰይጣናት ዋነኞቹም ናቸው።
እህቴ ሆይ!  ወደ መጥፎ ነገሮች የሚጎተጉቱን ወስዋሶች በርካታ ናቸው።
ነፍሲያ ማለት የየራሳችን ስሜታዊነት ሲሆን፤  የሰው ሰይጣናት ደግሞ እንደኛው ሰዎች የሆኑ የሩቅም የቅርብም ሆነው ወደ ክፉ ነገር የሚጎተጉቱን፣ ወደ ስህተት የሚገፋፉንና የሚያመቻቹ ሰዎች ናቸው። ባህሪያቸውም የሰይጣን ባህሪ አይነት በመሆኑ የሰው ሰይጣናት ይባላሉ። የጂን ሰይጣናት ደግሞ ዋናው ኢብሊስና ዝርዮቹ ናቸው። የጂን ሰይጣናት የተባሉትም የተፈጠሩት ከጂን ስለሆነ ነው።
☞ የሰው ሰይጣንነት አንዳችን ባንዳችን ላይ የምናደርገው ክፉ እምነትና ተግባር በመሆኑም በብዙ ነገሮች ውስጥ ይገባል። ለምሳሌም በዘመኑ የመገናኛ አውታር በኢንተርኔት ብዙ ፈሳዶች ሲተገበሩ ይታያል ይሰማልም።  ሙስሊሟን ሴት ለማጥቃትና ወደ ብልግና ለመሳብም ከስክሪን በስተጀርባ እንዳሰፈሰፉ መሽቶ ይነጋል። በተለያዩ ዘዴዎች ካንቺ ጋር ይፃፃፋሉ። አንቺም ሂጃብሽ ትርጉም እንዲያጣ በሚያደርግ መልኩም ወሬ ለጀመረ ሁሉ በርሽን ክፍት ታደርጊያለሽ። የዚህኔ የባጡን የቆጡን እየፈለፈሉልሽና እያስለፈለፉሽ ወደ መረባቸው ይከቱሻል። የትዳርም ይሁን ሌላ ወሬ ይዘው ያስወኙሻል። ይህ ጉዳይ አንተ ወንድሜንም ይመለከተሃል
በእንደዚህ አይነቶቹ የሰው ሰይጣናት ተሸንግለህ እውነተኛ ማንነቷ በውል ላልተረጋገጠች ሴት የቻት ወሬ ውሃ ውስጥ እንደገባ ጨው ትሟሟለህ። ሀራምን የመራቅ ብቃትህ፣ ሃይልና ሰብርህ ሁሉ ይመክናል።
እናስተውል...❗
ነቢዩላሂ ዩሱፍ አለይሂሰላም ምርኮኛ ሆነው እንደፈለጉ በሚያዝዟቸውና በሚያደርጓቸው ንጉስ ስር በቤተመንግስት ነዋሪ ነበሩ።ንጉሱም ሆነ ንግስቲቱ ያዘዙትን ከመፈም ውጭ ማምለጫ አልነበራቸውም። በክፍሉ ውስጥ ብቻውን እያለ የንጉሱ ሚስት በጣም ተውባና ተቆነጃጅታ ዘው ብላ ገባችበት።  በሮቹን ሁሉ ቆላለፈቻቸው። ለእርሱ ስትል ዝግጅቷን እንዳጠናቀቀችም አበሰረችው። የምትፈልገውን እንዲያደርጋት ነገረችው።
ይህንን ታሪኽ አላህ በቅዱስ ቃሉ እንደገፀልን፦
وَرَاوَدَتْهُ الَّتِي هُوَ فِي بَيْتِهَا عَن نَّفْسِهِ وَغَلَّقَتِ الْأَبْوَابَ وَقَالَتْ هَيْتَ لَكَ ۚ قَالَ مَعَاذَ اللَّهِ ۖ إِنَّهُ رَبِّي أَحْسَنَ مَثْوَايَ ۖ إِنَّهُ لَا يُفْلِحُ الظَّالِمُونَ [١٢:٢٣]  
« ያቺም እርሱ በቤትዋ የነበረባት ሴት፣ ከነፍሱ አባበለችው፤ ደጃፎችንም ዘጋች፤ ላንተ ተዘጋጅቼልሀለሁና ቶሎ ና አለች፤ "በአላህ እጠበቃለሁ" እርሱ (አሳዳሪዬ የገዛኝ) ጌታዬ ኑሮዬንም ያሳመረልኝ ነውና (አልከዳውም)፤ እነሆ! በደለኞች አይድኑም፤ አላት።»  ዩሱፍ : 23
ነቢዩላሂ ዩሱፍ አለይሂ ሰላም ስሜቱን ከጫፍ የሚያደርሱ ነገሮች ቢመቻቹለትም ራሱን አቅቦ አሳዳሪ ንጉሱንም ላለመክዳት፣ ፈጣሪ ጌታው አላህንም በመፍራት ይህን አጭር ምላሽ ሰጣት። ምንም በንግስቲቷ ጥላ ስር ቢኖርም፣ በሩን ቆላልፋበት ብታስገድደውና አማራጭ ማምለጫ ባይታይም የጭንቅ ግዜ ደራሹ ወደሆነው አላህ ጥሪውን አቀረበ።
قَالَ مَعَاذَ اللَّهِ 
 «በአላህ እጠበቃለሁ አላት»  ዩሱፍ : 23
 በልቡ ውስጥ ያለና እርግጠኛ እምነቱ ነበርና ጌታው አላህም ጠበቀው ፤ ከፈተናው አዳነው።  የዚህ አይነቱ ወደ ፀያፍ ተግባር የሚደረግ ጥሪ ዛሬም በኢንተርኔት  የቻት መስኮቶች በተደጋጋሚ እየተተገበረ ነው። ነገር ግን ከወንዱም ከሴቷም የነብዩ ዩሱፍን አይነት አቋምና ምላሽ ማን ይስጥ ❓ «በአላህ እጠበቃለሁ!»  ከሰው ሰይጣናት ለመጠበቅ የአላህ ፍራቻና ዱዓእ ሊለየን አይገባም። 
ውድ እህቴ በተለያዩ የመገናኛ መስመሮች ከሚደረጉብሽ ትንኮሳዎችና የተሳሳቱ ግብዣዎች ራስሽን ተከላከይ❗
አላህ ሆይ ከጥፋት ሁሉ ጠብቀን።


No comments:

Post a Comment