Wednesday, 27 January 2016

የሒጃብ እንቅፋቶች

🍂 የሒጃብ  እንቅፋቶች 🍂

       እህቴ ሆይ ❗ሂጃብሽን እንዳትጠብቂ ያደረጉሽ ቀጫጭን ምክንያቶችና ስህተቶችሽን ታውቂያቸዋለሽን❓

.  የአጉል ተስፈኝነት ምክንያት

ኢማን በልብ ነው ሂጃብ በለበሱ አይደለም ፣ ዋናው ከልብ መስተካከል ነው....❗..
  እህቴ ሆይ ይህንን አባባል ወይም አመለካከት ከወደየት አመጣሽው ?
   ኢማን ማለት በልብ ውስጥ ብቻ በመቀመጥ ወጣ ብሎ የማይታይ ምናባዊ መፎከርያ አይደለም።
  ይልቅስ ኢማን በልብ የሚያድር በአንደበት የሚነገርና በተግባር የሚገለፅ ነገር ነው።
  እነዚህ ሶስቱ ተጣምረው ሲገኙም ነው ኢማን ምሉእ የሚሆነው።
   በእርግጥ ከመልእክተኞች በስተቀር ከሰው ልጅ በሙሉ ምሉእነት አይጠበቅም ። መሳሳት መርሳት፣ መዘናጋት፣ ኣለማወቅና ማመፅም ባህሪያችን ነው።
   ሆኖም አንድን ሸሪኣዊ ትእዛዝ ስንታዘዝ ቀጫጭን ምክንያቶችን በመደርደር ከህጉ ለማምለጥ መሞከር ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም።
  ስለሆነም በልቧ እውነተኛ ኢማን የሰረፀባት እንስት ሌሎች እንቅፋቶች ካልገጠሟት በስተቀር  ሂጃቧን ስርዓቱን ጠብቃ ከመልበስ የሚያግዳት ነገር የለባትም።
ኢማን በልብ ነው የሚለውም መከራከርያ ስህተትሽን ለመሸፈን ያመጣሽው ተራ ምክንያት ነውና ልትርቂው ይገባሻል።
  ልቧ በእውነተኛ ኢማን የተስተካከለላት እንስት ተግባሯም ይስተካከላልና።

. ቀጣዩ ኮሳሳ ምክንያቷ ደግሞ

    አላህና መልክተኛውን እወዳቸዋለሁ፤ ለመውደዴ ደግሞ የግድ ሂጃቤን ጠብቄ መልበስ አይጠበቀኝም.❗...  የሚል ነው።
   እህቴ ሆይ ይህ አነጋገር የግል ሃሳብሽ ነው ? ወይስ ከዲንሽ በመማር የቀሰምሽው ነው  ❓
   በመሰረቱ የዚህ አይነት ለአላህና ለመልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የሚገለፅ ፍቅር ወይም ውዴታ በቁርኣንም በሀዲስም አልሰፈረም። ይልቁንም በተቃራኒው ነው የተደነገገው።
  አላህን በእውነት የሚወድ ያለ ምንም ጥርጥር መልእክተኛውንም ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ይወዳል። መልእክተኛውን የወደደ ደግሞ ይዘውት የመጡትን መልእክት ያከብራል ይከተላል።
  ይህንን ባዶ ተስፈኝነት ሲያጋፍጥም አላህ እንዲህ ይለናል።
قُلْ إِن كُنتُمْ تُحِبُّونَ اللَّهَ فَاتَّبِعُونِي يُحْبِبْكُمُ اللَّهُ وَيَغْفِرْ لَكُمْ ذُنُوبَكُمْ ۗ وَاللَّهُ غَفُورٌ رَّحِيمٌ [٣:٣١]
በላቸው : « አላህን የምትወዱ ከሆነ ተከተሉኝ አላህ ይወዳችኋልና ኃጢያቶቻችሁንም ለእናንተ ይምራልና አላህ መሀሪ እና አዛኝ ነው:። » በላቸው ።(ኣሊ-ኢምራን 31)
  ስለዚህም አላህና መልክተኛውን መውደድሽን በአንደበትሽ እንደመሰከርሽው ሁሉ በተግባርም ያዘዙሽን ሂጃብ በመልበስ አረጋግጪው።
. ቀዝቃዛ ምክንያት ደግሞ

ወላጆቼ ሂጃብ እንድለብስ አይፈቅዱልኝም  የሚል ነው።
   በመጀመርያ ደረጃ ሙስሊም ወላጆች አላህን ሊፈሩትና ነቢያቸውንም ሊያከብሩ በሃይማኖታቸውም ሊኮሩ ይገባል።
    ምንም የማይጎዳቸውን  ይልቁንም የሚያኮራቸውን የሴት ልጃቸውን መከበር ኣለመፍቀዳቸው ተገቢ ባለመሆኑ ከዚህ አይነቱ ስህተት ሊመለሱ ግድ ይላቸዋል።
   ቀጥሎም በልጆቻቸው ላይ መብታቸው እስከየት እንደሆነም መረዳት አለባቸው። መውለድ፣ መቀለብ፣ ማኖርና ማልበሳቸው እንዲሁም ጣጣቸውን ችለው ተንከባክበው ማሳደጋቸው የልጃቸውን መብት ለመግፈፍና የአላህን ዲን ለመፃረር ሊያበቃቸው አይገባም።
  
    እህቴ ሆይ ካንቺ የሚጠበቀው ቤተሰቦችሽን በመልካም ፀባይ ይዘሽ ሃይማኖትሽ ያዘዘሽን የመተግበር ግዴታ እንዳለብሽ፣ የከለከለሽንም የመራቅ ሃላፊነት እንደሚጠበቅብሽ ልታሰረጂያቸው ግድ ይልሻል። አሻፈረን ቢሉ እንኳ እስከዚህ ድረስ ሃያልነት የላቸውምና አለባበስሽን ማስተካከል አያቅትሽም።
   ያውም ባሁኑ ዘመን የትኞቹ ወላጆች ናቸው ልጆቻቸውን ሙሉ በሙሉ አየመሩ ያሉት❓ የአላህን ትእዛዝ ለመጣስ ሲሆን ብቻ ነው ወላጅ የሚፈራው  ❗
ነብዩም ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም
(لا طاعة لمخلوق في معصية الخالق)
  የፈጣሪን ትዕዛዝ ለመጣስ ለፍጡር መታዘዝ የለም ብለዋልና ሰበብሽ ውድቅ ነው፡፡
   ምክንያትሽ ልባዊና ተጨባጭ ከሆነ በዚህ ይስተካከላል። ቀዝቃዛው ሰበብ ከሆነ ግን አላህን ፈርተሽ ወደ ዲንሽ ልትመለሺና ክብርሽን ልትጠብቂ ይገባሻል።

. ግልጥ ያለ የአመፀኝነት ምክንያት❗

መደነቅን ስለምወድ ቁንጅናዬና ደም ግባቴ እንዲሁም አቋሜ እንዲታይልኝ ፈልጋለሁና ሂጃብ ደግሞ ይህንን ይጋርድብኛል
ይኸ ምክንያት ሰብሰብ ሲደረግ እንጂ በውስጡ በርካታ አባባሎች ኣሉት።
ቆንጆ ልብስ ለምን አስፈለገኝ ?
ፀጉሬን መሰራት  ለምን አስፈለገ ?
መዋብ ማማር መቀባባት ለምን ?
እንዳሮጊት ተጀቡኜ ልኑር ?
እዚህ ውስጥ ተሸሽጌ ማን ሊያየኝ ነው ?
ባልስ እንዴት ነው ማገኘው ?
የመሳሰሉ ምክንያቶችን በማሰብ በሂጃብ ጥላ ስር ላለመጠለል ይሟገታሉ።
   በመሰረቱ የተዘረዘሩት ነገሮች በሙሉ ካገባሽ በኋላ ለባልሽ የምታደርጊውና ለቅርብ ቤተሰቦችሽ ብቻ የሚፈቀድልሽ ነውና እህቴ ሆይ ሂጃብሽን አደራ❗፡፡
  የዓለም ህዝቦች በአጠቃላይ ቁንጅናሽን ቢያደንቁልሽ አንቺን ከአንቺነትሽ ስንዝር ከፍ የሚያደርጉሽ ይመስልሻልን ? አይምሰልሽ❗
   ይሄ አካሄድሽ ጉራ ፍለጋም ይመስላል። አላህ ደግሞ ጉረኛን አይወድም።
  መሸፈንሽ ውበትሽ ነው። በአላህና በመልእክተኛው ዘንድም ቆንጆ የሚያስብልሽ ነው።

   መገላለጥሽ ደግሞ በሰይጣንና በጭፍሮቹ ዘንድ አድናቆትን ያተርፍልሽ ይሆናልና የሚሻልሽን የመከበርያሽን መንገድ ብትመርጪ ይበጅሻል።

No comments:

Post a Comment