በዚህም እነደ ኒያቸው የአላህን ምንዳ ይቀራመታሉና። የአላህን ውሳኔም ከመውደድና ከመቀበል ያለፈ ልባዊም ሆነ አንደበታዊ ስህተት ውስጥ ሊገቡ አይገባም።
وَمَا كَانَ لِمُؤْمِنٍ وَلَا مُؤْمِنَةٍ إِذَا قَضَى اللَّهُ وَرَسُولُهُ أَمْرًا أَن يَكُونَ لَهُمُ الْخِيَرَةُ مِنْ أَمْرِهِمْ ۗ وَمَن يَعْصِ اللَّهَ وَرَسُولَهُ فَقَدْ ضَلَّ ضَلَالًا مُّبِينًا [٣٣:٣٦]
« አማኝ (ሙእሚን) ለሆነም ሆነ ሙእሚን ለሆነች ግለሰብ አላህ በአንድ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ከሰጠ በኋላ ከመቀበል ውጭ ምንም አማራጭ ሊኖራቸው አይገባም። »
~ አላህ አዝዘ ወጀልለ ደግሞ ሁሉን አዋቂ የሆነ ጌታ ነውና ብልሹ ኣድርጎ አልፈጠረም።
~ የሰውን ልጅ በመልካም ሁኔታ ነው የፈጠረው።
وقال تعالى :
لَقَدْ خَلَقْنَا الْإِنسَانَ فِي أَحْسَنِ تَقْوِيمٍ [٩٥:٤]
« ሰውንም በጣም ባማረ አቋም ላይ ፈጠርነው »
በፈለገው አይነት የመፍጠር ብቃቱም መብቱም የሱ ነውናም የተሰጠንን ኣመስግነን፣ የቸገረንን እንዲያመቻችልን እንጠይቀው።
የወር አበባ ደም መፍሰስ ከጀመረ በኋላ የቆይታ የግዜው መጠን ላይ የሊቃውንት አስተያየትና ትክክለኛው አቋም
የመጀመርያው: አስተያየት
አነስተኛው አንድ ቀንና አንዲት ሌሊት ሲሆን ረዥሙ አስራ አምስት ቀን የሚል ነው
ይህንንም ሃሳብ አብዛኞቹ የኢስላም ሊቃውንት (ፉቀሃእ) ያሉት ሲሆን፣ ይህም የወር አበባ የቆይታ ግዜ ትንሹ አንድ ቀንና አንድ ሌሊት ሲሆን ረዥሙ ግዜ ደግሞ አስራ አምስት ቀናት ናቸው የሚል ነው።
2ኛው: አስተያየት
አጭሩንም ሆነ ረዥሙን የቆይታ ዘመን ቢጠቅሱም ቁጥሩ ላይ ግን መለያየታቸው
ሸይኹል ኢስላም ረሂመሁላህ እንዲህ ይላሉ:
“ ከሊቃውንት መሀከል አጭሩን ና ረዥሙን የሀይድ (የወር አበባ) የቆይታ ዘመን የጠቀሱ ቢኖሩም በቀናቱ ቁጥር ላይ ግን ተለያይተዋል።
አንዳንዶች የአብዛኛውን የቆይታ ግዜ መጠን ሲጠቅሱ አነስተኛ የሆነውን የቆይታ ግዜ ወስነው ወይም ገድበው አልጠቀሱም። ”
3ኛው: አስተያየት
የወር አበባ የቆይታ ዘመን ገደብ የለውም የሚል ነው
F ይህ ሶስተኛው የኢስላም ሊቃውንት (ዑለማኡል ኢስላም) አቋም ወደ ትክክለኛነት ያደላ ነው።
ይህም
F የሀይድ የቆይታ ዘመን ትንሹ ግዜው ይህን ያህል ነው፣ ረዥሙ ግዜም እስከዚህ ቀን ነው በሚል ገደብ የሌለበት ነው።
በመሰረቱ ሴት ልጅ ከወር አበባ የመንፃቷ ምልክቱ ወይም ማረጋገጫው የደሙ መቋረጥ ነው።
ይህም የግዜ ዘመኑ ወይም የቆይታው ቀናት ለአጭርም ይሁን ለረዥም ግዜ ቢሆን ዋናው ሚታየው የደሙ መቆም ነው።
ሸይኩል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያ እንዳሉት
የወር አበባ ቆይታን በተመለከተ አጭርም ሆነ ረዥም የሚባል የተገደበ የግዜ ቀመር የለም። ይልቅ የታወቀው የወር አበባ ደም ምልክቶች እስካሉባት ድረስ ለአጭር ግዜም ይቆይ ለረዘመ ቀናትም ይቆይ የወር አበባዋ ግዜ ያ ነው ብለዋል።
“ ሀይድን (የወር አበባን) በቁርኣንና በሱና እንደሰፈረው አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ከበርካታ አህካሞች (ህግጋት) ጋር አቆራኝቶታል ። አጭሩንም ሆነ ረጅሙን የግዜ ገደብ ደግሞ አላስቀመጠም። ”
ሸይኹል ኢስላም አክለው ሲያስረዱ
“ ስለ ሀይድ ቆይታ ማወቁ ለህብረተሰቡ አስፈላጊና አሳሳቢ ከመሆኑም ጋር የሀይድን የቆይታ ግዜና በሁለቱ የሀይድ ወቅቶች (ባለችበት ወርና በቀጣዩ ወር) መሀል ያለውን የግዜ ክፍተት ወይም የንፅህናዋን የግዜ ቀመር አላስቀመጠም። ”
መጅሙዕ አልፈታዋ ጥራዝ 19: ገፅ 237
በዚህም መሰረት ለሀይድ የተገደበ የግዜ ቀመር ካልተቀመጠ ባህሪውና ምልክቶቹ ላይ መመርኮዝ የሀይድን ደም ከኢስቲሃዳ ደም መለየት የተሻለ አማራጭ ነው።
=> እንደሚታወቀው የያንደንዷ እንስት የወር አበባ ባህሪም ይለያያል።
ጠቅለል ሲል የወር አበባን የቆይታ ዘመን በግዜ ቀመር ገድቦ መለየት የማይመችና በዚህ መልኩ እንድንለይ የሚያስገድደን ግልፅ መረጃም ባለመኖሩ የሌሎችን ምሁራን አስተያየት በኢጅቲሃድነቱ ከማክበር ጋር የሀይድ ደም የአጭር ወይም የረዥም ቆይታ ጊዜው የሚወሰነው በደሙ መኖርና ኣለመኖር ላይ ይሆናል የሚሉትን ሊቃውንት አስተያየት እናስቀድማለን።
በዚህም ለዒባዳዋም ሆነ ተያያዥ ለሆኑት ሙኣመላዎች ራስዋን እንድታዘጋጅ ምቹ ሁኔታን ይፈጥርላታል።
የኢስቲሃዳ ደም
ኢስቲሃዳ ከሀይድ ደም በባህሪው የተለየ ነው። ከሸሪዓዊው ደንቦቹ (ህግጋቱ) አንፃርም ይለያያሉ። የኢስቲሃዳ ደም እንደ ሀይድ ደም በጤናማነት በተለመደው የግዜ ቀመርና አይነት የሚመጣ ሳይሆን መንስኤው ህመም ወይም አደጋ ነው። የኢስቲሃዳ ደም ምንጩ ከወር አበባ ሳይሆን ከደም ስር መበጠስ የሚከሰት ነው።
መልእክተኛው ﷺ ለፋጢማ ቢንቱ አቢ ሁበይሽ ረዲየላሁ ዐንሃ እንዳስረዱትና በሰሂሀይን እንደሰፈረው
” إنما ذلك عرق وليس بحيض “
« እሱኮ (ኢስቲሃዳ) ከደምስር ነው ። ከሀይድ አይደለም። » ብለዋል።
በኢማሙ ቱርሙዚይና በአቡ ዳዉድ ረሂመሁሙላህ ዘገባ ደግሞ ሀሙና ቢንት ጃህሽ ረዲየላሁ ዐንሃ የአላህ መልእክተኛን ﷺ ስለ ኢስቲሃዳዋ ደም መፍሰስ ጠይቃቸው በሰጧት ምላሽ መሰረት መንስኤው የሸይጣን ተፅእኖ መሆኑም ተዘግቧል።
«ይህችማ (የደሙ መፍሰስ) ከሸይጣን እርግጫ (የመጣች) ናት»
ይህንን የሸይጣን ትንኮሳ ለመከላከልና የደረሰውን ህመምም ለማስወገድ ዋናው ፍቱን መድሃኒት ወደ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ መመለስና በዚክር፣ በዱዓእ እንዲሁም ቁርኣንን በመቅራት መታገል ሲሆን የህክምና ባለሞያዎችንም በተጓዳኝ በማማከር መታከም ያስፈልጋል።
قال تعالى:
” وَنُنَزِّلُ مِنَ الْقُرْآنِ مَا هُوَ شِفَاء وَرَحْمَةٌ لِّلْمُؤْمِنِينَ “ {الإسراء:82}،
« ከቁርኣንም ለምእመናን መድሃኒትና እዝነት የሆነን እናወርዳለን» (አል ኢስራ : 82)
የአላህ መልእክተኛ ﷺ እንዳሉት
« ታከሙ (መድሃኒትን ተጠቀሙ)፣ አላህ ከአንድ በሽታ በስተቀር ለሁሉም በሽታዎች መድሃኒትን አድርጓለት (ፈጥሮለት) ቢሆን እንጂ በሽታ እንዲኖር አላደረገም (አልፈጠረም) ። ያም አንዱ በሽታ እርጅና ነው። »
No comments:
Post a Comment