Wednesday, 27 January 2016

PART 1 እናታችን ዓኢሻ

ለሷ ሰምተሽ ታውቂያለሽ?

'እሷ' ብዬ ስጠራት ስቅቅ እያለኝ ነው። በአንቱታ ብጠራት ደስ ባለኝ ነበር፤ ግን እናት 'አንቱ' አትባልምና 'እሷ' እያልኩ እቀጥላለሁ ... እያከበርሻት ተከተይኝ።

ከፈቀድሽልኝ ላወጋሽ ያሰብኩት ስለእናትሽ ነበር። አዎን ስለአንቺ እናት!
እናትነቷን በደም ሳይሆን በተውሂድ ስላገኘሽው፤
በስጋ ሳይሆን በእምነት ለተዋሀድሽው፤
አይተሻት ሳይሆን ስለእሷ ሰምተሽ ያወቅሻት፣
አሳድጋሽ ሳይሆን ዲንሽን አስተላልፋልሽ የወደድሻት ...
   ስለሷ! ያንቺ ብቻ ሳትሆን የምእመናን ሁሉ እናት ስለሆነችው፤ ሲዲቃህ ቢንት ሲዲቅ!
   መካ ላይ ከምርጥ እናቷ ከኡሙ-ሩማን እና በጀነት ከተመሰከረለት የነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ቅርብ ባልደረባ አባቷ አቡበክር ሲዲቅ ተወለደች።
በኢስላም ብርሀን ባጌጠው ቤትም በመልካም እንክብካቤ፣ በኢስላማዊ አስተዳደግና በጥሩ ስነምግባር ተኮትኩታ አደገች።
ያ ወቅት ነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ውድ ባለቤታቸውን ኸዲጃን አጥተው በሀዘን የተቆራመዱበት ጊዜ ነበር።
   ያኔ ኸውላ ቢንት ሐኪም(የዑስማን ቢን መዝዑን ባለቤት) ነቢዩን (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ዘንድ ገባችና ጠየቀቻቸው ... "አታገባም እንዴ?"
ነቢዩም (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) መለሱ "ማንን?"
ኸውላ ቀጠለች "ከፈለክ ልጃገረድ ካሻህ ደግሞ ትልቅ?"
ነቢዩም (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) "ከልጃገረድ?" አሏት
ኸውላም "ከፍጡራን ሁሉ አንተ ዘንድ የተወደደውን ሰው ልጅ - ዓኢሻ ቢንት አቢበክር" ...
ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) በኸውላ ምርጫ ተስማሙ መልእክት እንድታደርስላቸውም ላኳት።
ኸውላ ትቀጥላለች ...
"ወደ አቡበክር ቤት ሄድኩ የዓኢሻን እናት ኡሙ ሩማንን አገኘኋት እንዲህም አልኳት "ኡሙ ሩማን ሆይ! አላህ እንዴት አይነት ጥሩ ነገርና በረከትን  ሰጣችሁ"
ኡሙ ሩማንም "ምንድን ነው እሱ?" አለችኝ
እኔም "ነቢዩ  (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም)  ዓኢሻን እንዳጭላቸው ልከውኛል አልኳት" ከዛም 'አቡበክር ይመጣልና ቆዪ' ብላ አስጠበቀችኝ፤
አቡበክር t ሲመጣ ... "አላህ እንዴት አይነት ጥሩ ነገርና በረከትን  ሰጣችሁ" አልኩት
"ምንድን ነው እሱ?" አለኝ፤
"ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ዓኢሻን እንዳጭላቸው ልከውኛል" አልኩት
ይሄኔ አቡበክር ልጄ ገና ነች ብለው አልተግደረደሩም፣ እንዴት አስችሏቸው በነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ጥያቄ ላይ ይግደረደራሉ? ይልቁኑ በደስታ ፈነደቁ በጥያቄውም ተስማሙ!
አላህም ይህን የነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ምር ጫ አጠነከረላቸው። በህልማቸው ዓኢሻን በተዋበ መልኩ ተመለከቷት፤ ዓኢሻ ስለሁኔታው ስትናገር እንዲህ ትላለች ...
"ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) 'ሶስቴ በህልሜ አይቼሻለሁ' አሉኝ፤ '... መላኢካው ባማረ ሐር አድርጎ ይህች ያንተ ሚስት ነች ይለኛል፤ ግልጥ አድርጌ ሳይ አንቺ ነሽ ..."

ይህን ሲነግሯት ምንኛ ትደሰት ይሆን? የባሏ ምርጫ በመለኮታዊ ራእይ ሲደገፍ ያውም 'ይህች ያንተ ሚስት ነች' ብሎ አላህ ስለሷ መግለፁን ስትሰማ ምን ያህል ይሰማት?!
ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ዓኢሻን እንዳጩ ወዲያው አግብተው ወደቤት አላስገቡም፤ ይልቁኑ እስክትደርስ ድረስ አባቷ ቤት እንድትቆይ አደረጉ፤ እናቷን 'ደህና አርገሽ ያዢልኝ' ይሉ፣ ደጋግመው መዘየር ያበዙም ነበር። (መውደድ ነዋ!)
ነገሩ በእንዲህ እያለ የመካ ከሀድያን በሙስሊሞች ላይ የሚያደርሱት በደል አየለ። ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ከባልደረባቸው አቡበክር ጋር ወደ የስሪብ(መዲና) ተሰደዱ። ዓኢሻም እንዲሁ ከነቤተሰቧ መዲና ከተመች።
    ሁለቱም ቤተሰቦች በመዲና ተገናኙ፤ አዲሲቷን ሀገር ሲላመዱም ያቀዱትን ትግበራ ተንቀሳቀሱ። ከሁለት አመት በኋላ ነበር በሸዋል ወር ዓኢሻ ወደ ነቢያት አለቃ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ቤት መግቢያዋ የደረሰው።

 እናቷ እና ሌሎችም ለሰርጓ ያሰናዷት ጀመር። አስማእ ቢንት የዚድ ካስዋቧት አንዷ ነበረች፤ ከዛም ወደ ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ይዛት ገባች...
ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ከጎኗ ቁጭ አሉ። ከያዙት ወተት ተጎነጩና ለዓኢሻ ሰጧት፤ እሷ ግን አፍራ አንገቷን ደፋች፤ አስማእ ተቆጣቻትና ተቀብላ እንድትጠጣ ነገረቻት፤ ዓኢሻም ተቀብላ ፉት አለች።
ተመልከች እህቴ! አይናፋርነቷን፣ እንዳሁኑ ሴቶች በሰርጓ ቀን ልትደልቅ፣ ልትጨፍር፣ እስክታ ልትወርድ ቀርቶ አንገቷን እንኳ ቀና ለማድረግ አልደፈረችም። የአቡበክር ልጅ፣ የነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ሚስት፣ የአንቺ እናት፤ ዓኢሻ!
በሰርጓ ቀን ግመል አልታረደም፣ በሬም አልተጣለ ኧረ ፍየልም ቢሆን፤ በሳህን የቀረበ ምግብ እንጂ። ነቢዩም (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ጋር ስትገባ ምቹ አልጋ የተሟላ ቤት አልጠበቃትም፤ ደከም ያለ ፍራሽ ... አንስተኛ እቃዎች ... በቃ!
እሷ ነቢዩን (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) አግኝታለች ታዲያ ሌላ ምን ትፈልጋለች?

መኸሯን ጠይቀሻል? ስንት ቢሆን ጥሩ ነው?
500 ዲርሀም -በቃ!የዓኢሻ ቤተሰቦች ለልጃችን ጥሎሽ ለኛም ስጦታ ብለው ግብግብ አልፈጠሩም፣ እንዴት ሳይደገስ እንዴት ሳይበላ ብለው 'ቡራ-ከረዩ' አላሉም። ዲን አጠንክሯቸዋልና!


No comments:

Post a Comment