ትዳር:-
በባልና ሚስት መካከል የሚደረግ የጋራ ስምምነትና መቻቻል ላይ የተመሰረተ ውልና ሂደት ነው ። በውስጡ በርካታ ሚስጢሮችንም ያቀፈ ህይወት ነው።
F በዚህም ሂደት ለየት ያለ የህይወት መስመር ይዘረጋል።
F ወንዱም ሆነ ሴቷ በየትኛውም ፕሮጀክት ሊያስገኙት የማይችሉትን ጥቅሞች ያተርፉበታል።
በትዳር:-
ሰዋዊ ወይም ስጋዊ ስሜታቸውን በሃላል ያረኩበታል። ገላ ሰውነታቸውን እንዲሁም አዕምሯቸውን ያነቃቁበታል ያሳርፉበታል።
ይህንን ታላቅ ልገሳም አላህ አዝዘ ወጀልለ በሚቀጥለው መልኩ ይገልፅልናል
الأعراف: 189 « هُوَ الَّذِي خَلَقَكُمْ مِنْ نَفْسٍ وَاحِدَةٍ وَجَعَلَ مِنْهَا زَوْجَهَا لِيَسْكُنَ إِلَيْهَا…… »
« እርሱ ያ ከአንዲት ነፍስ (ከኣደም) የፈጠራችሁ ከእርሷም መቀናጆዋን ወደርሷ ይረካ ዘንድ ያደረገ ነው። … »አል-አዕራፍ : 189 ይላል
በሌላ በኩል ከትዳር:~
የሚወዱትን፣ የሚናፍቁትን የአይን ማረፍያ፣ የልብ መርጊያ ፍቅረኛ ወዳጅ በፍቁድ መንገድ ያገኙበታል።
ብሎም በትዳር:-
ዝርያ ይቀጥሉበታል፣ አይናቸውን በአይናቸው በማየት የአብራካቸውን ክፋይ፣ ተተኪያቸውን በትክክለኛው የማፍሪያ መስመር ያፈሩበታል።
እንዲሁም በትዳር:~
ልክ ወላጆቻቸው ዘንድና ጓዶቻቸው ዘንድ አይተው ሲመኙት የነበረውን በቁጥርም በይዘትም መልካም የሆነን ቤተሰብ ያቋቁሙበታል። ዘመድ አዝማድም ያስፋፉበታል።
ለትዳር ከታደሉ:-
የራስ ቤት የራስ ጎጆ በመፍጠር አዲስ ጎረቤት፣ አዳዲስ ወዳጆችን ይመሰርቱበታል።
በተለይ በትዳር:-
የኔ የሚሉትን ደጋፊና ተቆርቋሪ ታማኝ ወዳጅ ከጎን ያገኙበታል። እሱ ለሷ አሷም ለሱ ከማንም በላይ ጓጊና አዛኝ ይሆናሉና።
አላሁ ሱብሃነሁ ወተዓላ ይህንኑ እንድናስተውል ያመላክተናል ።
« وَمِنْ آَيَاتِهِ أَنْ خَلَقَ لَكُمْ مِنْ أَنْفُسِكُمْ أَزْوَاجًا لِتَسْكُنُوا إِلَيْهَاوَجَعَلَ بَيْنَكُمْ مَوَدَّةً وَرَحْمَةً إِنَّ فِي ذَلِكَ لَآَيَاتٍ لِقَوْمٍ يَتَفَكَّرُونَ الروم: 21.»
« ለእናንተም ከነፍሶቻችሁ (ከጎሶቻችሁ) ሚስቶችን ወደ እነርሱ ትረኩ ዘንድ መፍጠሩ ፤ በመካከላችሁም ፍቅርንና እዝነትን ማድረጉ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው። በዚህም ውስጥ ለሚያስተውሉ ህዝቦች ተዓምራቶች ኣልሉ። »
አል ሩም: 21 ይለናል
ሌላኛው ጥቅም በትዳር:~
ከተለያዩ የዘመኑ ፈተናዎችም ሆነ ከግልፁ ዝሙት ይጠበቁበታል። ብሎም የላጤነትን ቁጥር በማሳነስ ብልሹና ርካሽ ምግባርን ለመቀነስ ድርሻቸውን ይወጡበታል። የህብረተሰቡም ክብርና ዝርያ ይፀዳበታል።
የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዳስጠነቀቁን
« إذا جاءكم من ترضون دينه وخلقه فأنكحوه إلا تفعلوا تكن فتنة في الأرض وفساد كبير …… »
«ዲኑንና ስነምግባሩን የምትወዱለት ሰው ለጋብቻ ፍለጋ ሲመጣችሁ አጋቡት። ይህ ካልሆነ ግን በምድር ላይ ከባድ የሆነ ፈተናንና ብልሽትን ታሰፍናላችሁ »
በዚህ ሀዲስ መልእክተኛው ዲኑን በመተግበር የሚታወቅ ብሎም መልካም ባህሪ ያለው ሰው እናንተ ዘንድ ያለችን ሴት ሊያገባት ሲጠይቃችሁ እምቢ አትበሉትና አጋቡት። የማታጋቡትና ምትመልሱት ከሆነ ትርፉ ሴቷን መበደልና ወንጀልን ማስፋፋት እንጂ ጠቃሚ ነገር የለውም እያሉን ነው።
በተጨማሪም ለመልካም ትዳር የታደሉ:-
ክቡር መንደር፣ ሃገርና ማህበረሰብ ይገነቡበታል ።
እንዲሁም አሱ በሷ እሷ በሱ ብሎም በሚያፈሩት ልጆችም ሰበብ የዱንያ ላይ ሪዝቃቸውን ያሰፉበታል።
ከጋብቻ በፊት የነበረው ጥበትና ድህነትም ከትዳር በኋላ እየቀለለና የጎደለው እየሞላ እየተመቸ ይሄዳል።
በመልካምነታቸው ልክም የዱንያንና የኣኺራን ስኬት ይጎናፀፉበታል።
ሱረቱል ኑር ላይ ያለውን አንቀፅ 32 ትን ልብ ይበሉ
« وَأَنْكِحُوا الْأَيَامَى مِنْكُمْ وَالصَّالِحِينَ مِنْ عِبَادِكُمْ وَإِمَائِكُمْ إِنْ يَكُونُوا فُقَرَاءيُغْنِهِمُ اللَّهُ مِنْ فَضْلِهِ وَاللَّهُ وَاسِعٌ عَلِيمٌ »
{النور:32}
« ከእናንተም ትዳር የሌላቸውን አጋቡ። ከወንዶች ባሮቻችሁና ከሴቶች ባሮቻችሁም ለጋብቻ ብቁ የሆኑትን አጋቡ ። ድሆች ቢሆኑ አላህ ከችሮታው ያከብራቸዋል። አላህም ስጦታው ሰፊ አዋቂ ነውና ። »
ስለሆነም ይህንን ታላቅ የሆነ የህይወት ማዕከል በቀላሉ ማፍረስና መበተን ጉዳቱ የከፋ በመሆኑ ሁሉም የየራሱን መልካም አስተዋፅዖ ማድረግ ይገባዋል።
No comments:
Post a Comment