ከአንድ በላይ ጋብቻን በማበረታታት
ላ ላ ገ ቡ ት ም እ ና ስ ብ
ስለ ትዳር ፋኢዳ ቢነገር አይዘለቅም ይሁንና በመጠኑም ቢሆን በማውሳት ለትዳር ያልታደሉትን ማሳወቁ መልካም ነው። በትዳር ዓለም ያሉትም በትዳራቸው እንዳይቀልዱ ማስታወሱ አይከፋም። በተለይ አቅሙም ሁኔታውም ተመቻችቶላቸው በዛሬ ነገ ወይም በቸልተኝነት ከትዳር ለራቁት ጥሩ ማስታወሻ ትሆናለችና።
ሴቶች በየአካባቢው ቁጥራቸው ተበራክተዋል። ወንዱ የትዳርን ጣጣ ሽሽት በየስርቻው ተደብቋል። ወደ ዝሙት የሚወስዱ መንገዶች ደግሞ አሸብርቀው ተመቻችተው ከብበውናል። ሴቷም ከተፈጥሮዋ ጋር በማይመጥን መልኩ ከተኩላዎች ጋር እየተፋጠጠችም ነው። ወንዱ አቅሙ ከሚፈቅደው በላይ ወስዋሶች በዙርያው ተሰልፈዋል። ዝሙት ተስፋፍቷል።
አላህ አዝዘ ወጀልለ ለቻለ ሰው አንድም ሁለትም ሶስትም አራትም ፈቅዷል። ላልቻለ አንዷ እንድትቀርበት መክሯል። የሰው ልጅ ክብሩንና ዲኑን እንዲጠብቅ ታዟል። እሱም ክብሩን ይፈልጋል፣ መደነቅን ይወዳል፣ ዝሙት ግን ይህንን ህልሙን ያሳጣዋል።
እህት ዓለም ☞ አባትሽ፣ አጎትሽ፣ ወንድምሽና ልጅሽ በተለይ ባልሽ ዝሙት ላይ ወድቆ ማየቱም መስማቱም ይዘገንንሻል። ለጋብቻ ያልታደሉት እህቶችሽ የሚሰበስባቸውና የሚከላከላቸውን ካላገኙ በተኩላዎች በቀላሉ ይጠቃሉ ። በዚህም የራሳቸውን፣ የባልሽንና ያንቺንም ህይወት ያናጋሉ። ባልሽ ☞ መብትሽን ጠብቆ፣ በስርዓት እንዳቅሙ እያኖረሽ፣ ከአደጋ እየተከላከለሽ፣ ባንቺ ላይ አለቃም ተፅዕኖ ፈጣሪም ሳያደርጋት እዚያው ራሷን ችላ ቤቷን ይዛ እንድትኖር አድርጓት ቢያገባት ምን ይጎድልብሻል ? … ነግ-በኔ የሚባለውንስ ሼም ምነው ዘነጋሽው !
ባልሽ የላጤዎችን ቁጥር ቢቀንስ ካንቺ ሚጎልብሽ ነገር የለም። የምትነጠቂው መብትና የምታጪው ክብርም የለም። ነገር ግን እህቶችሽ እንዳንቺው ለሀላል ህይወት ቢበቁ ባልሽንም ቤተሰቦችሽንም ራስሽንም ታስከብሪያለሽ።
ባልሽ ከቤቱ መውጣቱና ባንቺ ላይ ሌላ መከተሉ ካልቀረ፣ ይባስ ብሎም አንቺን አማርሮ አስወጥቶ ሌላኛዋን ደግሞ በተራዋ ሊጨቁናት ማምጣቱ እየታየ ከሆነ … ምነው ረጋ ብለሽ ብታስቢበትና ላንቺ የዘነበው ለሷም ቢያካፋላት ከንቺ ምንሽ ይነካል ?!
በሰላም እያስተዳደረሽ፣ በክብር እየያዘሽ፣ መብትሽን እያስከበረም እያከበረልሽም ያለው ባልሽ … ሌላዋን ክቡር እህትሽን ሲያገባት ስለምን ዱንያን ትገለባብጫለሽ ❓ ለምንስ ሰላም ትነሺያቸዋለሽ ❓ ምን መጣና ነው ይህን ያህል ምሬት ይሉት ቅናት የወረረሽ ❓
እህት ዓለም ሌላም መልእክት አለኝና ልብ በይው የማግባቱን ጥቅምና ያለ ማግባቱንም ተፅዕኖ ጠቁሜሻለሁ። ግዴታውንም በአግባቡ መወጣት እንዳለበትም ተዋውሰናል። ይህ በፍትህና በእኩልነት ባቅሙ ልክ የመንከባከብ ብቃት ያለው ባልሽ … ሁለትና ከዚያም በላይ የማግባት መብቱ የሱ ነው። ማግባቱን እልል ብለሽ ተቀበይው፣ በደስታም ፈንጥዢለት ብዬም የማይገጥም ምክር አልሰጥሽም። እንደ ተፈጥሮሽ ማስተናገድሽን አልወቅስምም። ባልሽ ስላጓደለብሽ መብትሽ መቆርቆርሽንም አልፃረርም። ነገር ግን የፍትሃዊውና የጥበበኛው ጌታሽን ፈቃድ ሰጪነት እንድትፃረሪ አልፈቅድም። ህጉን ስታጣጥዪም ዝም አልልሽም። ያለ መብትሽ ካልወሰንኩ ስትዪም አልደግፍሽም።
የሴቷን ጉልበትና ጥቅም ሊዘርፏት እዚያም እዚህም ጉልቻ አዋቅረው የሚጠፉትን በጋራ እንዋጋለን። ከቤት እያቃጠለሽ ከውጭ የሚያራግበውንም እብረን እንጠላለን። ነገር ግን ጌታውን እየፈራ ነገ ባንቺ ላይጠየቅ እየተጠነቀቀ ሌላ እንዳንቺው የዚህ አይነቱን ባልና ህይወት የናፈቀችን ደርቦ ፍቅርን ቢያጣጥም መቅናትሽን ባልከራከርሽም መስገብገብ ግን የለብሽም። ማንም የማይነጥቀው፣ ጌታሽ የሸለመው መብቱ ነውና ላንቺም ለሷም ለነሱም እስከበቃ ድረስ በደረሰሽ አመስግኚው። ካንቺ የሚጠበቀው ስላጣሽው ወይም ስለጎደለው መብትሽ፣ እንደ አቅሙ ያኖርሽ ዘንድ በጨዋነት ማስከበር እንጂ ወደላይ ሄደሽ የመፍቀድና የማገድ እንዲሁም በፍቺ የማስፈራራትና ህይወታችሁን የማናጋት ስራ ውስጥ መግባትሽ አግባብ አይደለምና ተመከሪ።
አብዛኞቹ ሴቶች ባሎቻቸው እንዲደርቡባቸው ባይፈልጉም በዚያው ቁጥር ልክ ደግሞ ሁለተኛ ተደርበው ማግባት የሚፈልጉ የተከበሩ እንስቶች በራችሁ ላይ ቆመዋል። እንደናንተው መልካም ወንዶችም ቁምነገር ለመስራት አሰፍስፈዋል። ነገር ግን በአንዳንድ ድንበር ዘለሎች ተሸማቅቀው ታቅበዋል። እንዲሁ በደረቁ ባሌ አያግባ የምትል እንስት ምሳሌዋም ለስንቱ የሚበቃን አስቤዛ ብቻዋን ለመፍጀት እንደሚታገል ሰው አይነት ነውና ልቦናሽን ሰፋ አድርጊ፣ እልህና ከልኩ ያለፈ ቅናትም ይቅርብሽ።
እንደምታውቂው ያንን ጨዋና ተንከባካቢ ባልሽን ወደ ውጭ የሚያሳየው ብልግና ብቻ ነው ብለሽ አታስቢ። ልቦች ያፈቅራሉ፣ በጥሩ ነገሮች ይሳባሉ፣ በልቅነት ዓለም ስላለንም ይወሰወሳሉ፣ ለመብታቸውም ይቆረቆራሉ፣ በርከት አድርገው መውለድን ይሻሉ፣ እህቶቻቸውን የመሰተር ግዴታቸው ያሳስባቸዋል፣ ካንቺ የጎደለና አልሟላ ያለ ነገርም ይገፋፋቸዋል፣ ብዙ ነገር ከቦሻል፣ ከብቦታልም … ስለዚህ ሰፋ አድርገሽ አስቢና በክብር በስርዓት ያገባው ባልሽን ተንከባከቢ። ፍቅር እንደሆን እንደምታውቂው ሊገደብ የማይችል ነገር ነው። ልቦችን የሚመራው ፈጣሪ አምላክሽ አላህ ነውና ወዳሻው ይቀያይረዋል። ስለወደደሽ በጣም ቢንከባከብሽም፣ ስላልወደደሽ ግን መብትሽን ሊገፍፍ ሊጨቁንሽ፣ ኑሮን ሊያጠብብሽ፣ አማርሮሽ እንድትሰናበቺው ወይም ዝቅ ብለሽ እንድትኖሪለት የማድረግ መብት የለውምና እንደ ኢስላማዊው ደንብም ይይዝሻል። አንቺም በስልጣኑ መግባትና ጋብቻውን መቃወም እንደማትችዪ ሁሉ እሱም ካንቺ በባሰ በመብትሽና በክብርሽ ይጠየቅበታል። ካንቺ ጋር የሚኖረው ኑሮ ሳይስተካከልለት፣ ከሱ የሚጠበቀውን የአስተዳዳሪነት ሚና ሳይወጣ ማግባት መብቴ ነው እያለ የሚሮጥ ባልም… እየመሰረተ ያለው ጉልቻ ሳይሆን እሳቱን ነው። የውመል ቂያም በደል ፅልመቶች ትሆናለችና እዚህም አይሳካለትም እዚያም ስለሚያስጠይቀው አደብ ይግዛና " ካልቻለ " የሚለውን የቁርኣን አንቀፅ ልብ ሊለው ይገባልም።አንቺንም ያቺንም ማግባቱ ቁምነገር አይደለም። ምክንያቱም ቁምነገሩ አቻችሎና ችሎ በስምረት ማኖር ነውና።
ያለዚያ አንዷን ባየ ቁጥር በጁ ያለቿን የሚረሳ አልፎም አብርሯት ከሌላ የሚንጠለጠል ሰው ትዳር ሳይሆን የያዘው የመብት ጥሰት ነው። የተፈቀደበት አላማውም የላጤን ቁጥር ማሳነስና የሚከሰቱ ፀያፍ ድርጊቶችን ለመቀነስ ስለሆነ ሁሉ አማረኝ ማለት ግን ጭራሽ ወንጀልን ማስፋፋት ይሆናል። ስለሆነም አቶ ባል መብትና ግዴታዎን ለይተው ይወቁ። በሚስቶች መሃል ሆነው አንዷን ቢበድሉ የቂያም እለት ውርደት ይከናነባሉና ያስቡበት። ስርአት ያላቸው አስተዳዳሪ ብሎችንም አያስሰድቡ። የአላህንም ህግ እንዲጠላ አያድርጉ። እርስዎ ወይዘሪት ሚስት በባልዎ ማግባት ወሳኝ አይደሉም። ላገባ ነው ብሎ ቀድሞ ሊነግርዎትም ሆነ ሊያማክሮት አይገደድም። ይሁንና ለትዳር ሲዋዋሉ ሚስት ባሏ በሷ ላይ እንዳይደርብባት ተስማምተው ከተጋቡ ያንን ቃል ማክበር ግዴታ ይሆንበታል ።
የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዳሉት☞
« ፍቁድ ነገርን እርም ካደረገ ወይም እርም ነገርን ከፈቀደ ውል ውጪ ሙስሊሞች በውላቸው መሰረት ይፀናሉ ።» ብለዋል።
ይሁንና ይኸ ውል አላህ ለወንድ ልጅ ሀላል ያደረገለትን ያግዳልና የአታግባብኝ ውልን አይመለከትም የሚሉ አልሉ። ነገር ግን
ኡቅባ ቢን አሚር (ረዲየላሁ አንሁ) ከአላህ መልእክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ሰምቶ እንዳወራልን
« ከውሎች (ከመስፈርቶች) መሃል ይበልጥ ሊሟላ (ሊጠበቅ) የሚገባው ብልቶችን ሀላላችሁ ያስደረጋችሁበት ውል ነው።» ብለዋልና የእንስቷን ብልት የተፈቀደለት የሚያደርገው በጋብቻ ስለሆነ ለጋብቻው ስኬት ሲል ሌላ ላይደርብባት ቀድሞ እስከተስማማ ድረስ በኋላ ማግባት ሲያምረው በፈቃዱ ብቻ ውሉን ሊሽረው አይችልም።
አዩሀል ባል በመብትህ ከመገልገልህ በፊትም ጥቅምና ጉዳቱን አመዛዝን። ከምታስገኘው ጥቅም ይልቅ የምታጣው መብዛት የለበትም። ከዚያ እያማለልክ ከቤት እያቃጠልክ ከሆነ ብዙም ሳትቆይ አንተው መንደድ ትጀምራለህ። ምንዳህ እንደስራህ ነውና።
አላህ መብትና ግዴታችንን ለይተን አውቀን የምንሰራበት ያድርገን።
ላላገቡትም ብናስብ አይሻልም ❓
No comments:
Post a Comment