ውድ እህቴ ሆይ! ኢስላም ከማንኛውም ነገር በፊት ዕውቀትን በመገብየት ላይ አደራ ይላል፡፡ ምክንቱም የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ዕውቀትን መሰረት ያላደረጉ ከሆነ አላዋቂ ሳሚ ... እንደሚባለው ብሂል ከልማቱ የምንዘፈቅበት አዘቅቱ ያመዝናል፡፡ አንዳንዴም በኛ ሳይገደብ የኛው የጥፋት ረመጥ ይቀጥልና ሌሎችን እኛ የሰመጥንበት አዘቅጥ ውስጥ እንዲዋኙ የጥፋት ጀልባ እና መቅዘፊያ እንድንሆን ያደርገናል፡፡
በማስከተል መልዕክቱ እህቴም ልብ ላይ ተፅዕኖ ያሳድር ዘንድ የተወሰኑ መረጃዎችን ከቁርአንና ሀዲስ እያጣቀስኩ መልዕክቴን እቀጥላለሁ፡-…
ከቁርአን
ስለ እውቀትን ፋይዳዎችና ስለ አዋቂዎች ደረጃ
ዓዋቂው አምላካችን ስለ እውቀት ባለቤቶች ከፍ ያለ ደረጃ ዓዋቂዎች በሚገነዘቡት መልኩ እንዲህ ይላል፡-
يَرْفَعِ اللَّهُ الَّذِينَ آمَنُوا مِنكُمْ وَالَّذِينَ أُوتُوا الْعِلْمَ دَرَجَاتٍ [٥٨:١١]
‹‹«አላህ ከናንተ እነዚያ ያመኑትንና እነዚያ ዕውቀት የተሰጡትን በደረጃ ከፍ ያደርጋል»››(ሙጃደላህ፡11)
የዲን ዕውቀትን የቀሰሙ ዓዋቂዎችን አንፀባራቂ ፈርጥነት በአንቀፁ ፍንትው ተደርጎ ተወስቷል፡፡
ታላቁ ሶሃብይና የቁርአን ተፍሲር ዓዋቂ ዓብደላህ ኢብኑ ዓባስ እንዲህ ሲል የቁርአን አያውን የሚያጠናክርና የዓዋቂዎችን ደረጃ የሚያጎላ ንግግር አክሏል፡-
‹‹«የተማሩ ሰዎች ደረጃ ከተራው ሙዕሚን ሰባት መቶ እጥፍ ይበልጣል፡፡ ከአንዱ ደረጃ ወደ ሌላ ደረጃ ያለው ርቀት የአምስት መቶ ዓመት ርቀት ይሆናል፡፡»››
በሌላም ቁርአን አንቀፅ አላህ እንዲህ ይላል፡-
إِنَّمَا يَخْشَى اللَّهَ مِنْ عِبَادِهِ الْعُلَمَاءُ [٣٥:٢٨]
‹‹«አላህን ከባሮቹ ውስጥ የሚፈሩት ዐዋቂዎቹ ብቻ ናቸው»››(ፋጢር፡28)
እንዴታ! የማያውቁትን አካል እንዴት ተገቢውን ፍራቻ ይፈሩታል ጃል! ለዚያም ሲሉ መልዕክተኛው (ﷺ) እንዲህ አሉ፡- ‹ ‹
«ዕውቀትን ቅሰሙ አላህን የምትፈሩት ባወቃችሁት ልክ ነውና፡፡»››
አላህ መልዕክተኛው (ﷺ) እንዲጨምርላቸው እንዲጠይቁት ያዘዘው ብቸኛ ነገር ዕውቀት ነው! ከየት አመጣኸው ትይኝ ይሆናልና ማስረጃውን :-
وَقُل رَّبِّ زِدْنِي عِلْمًا [٢٠:١١٤]
‹‹«ጌታዬ ሆይ! ዕውቀትን ጨመርልኝ በል»›› (20፡114)
ለዕውቀቱ ገደብ የሌለው ሁሉን ዓዋቂ ከሆነው ጌታ ቃል ቁርአን ይህን ያክል የጥቂት ጥቂት ግን የገዘፉ መልዕክት ያላቸው አንቀፆች ካየን በተጨማሪ ደግሞ ከተወዳጁ መልዕክተኛ (ﷺ) አይጠገብ ንግግሮች የተወሰኑ እንቋዳሰ ዘንድ ወደ ቀጣይ ደረጃ እንለፍ አላህ ያግዘን…
ከሀዲስ
ከታላቁ ሶሃብይ ሙአውያ ኢብኑ አቢ ሱፍያን እንደተወራው የአላህ መልዕክተኛ (ﷺ) እንዲህ ብለዋል፡-
‹‹«አላህ መልካም የሻለትን ሰው የዲን ግንዛቤ ይሰጣዋል» ›› (አል-ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)
ልብ በይ እህቴ! የዲን ዕውቀትና ግንዛቤ አላህ የሚሰጠው መልካም ለሻለትና ለወደደው ነው፡፡ ምንኛ ታላቅ እድል ነው! አላህ ይውደደን! መልካምም ከሻላቸው የዲን ግንዛቤ ከሰጣቸው ባሮቹ ያድርገን! አሚን!
በሌላም ሀዲስ ዕውቀትን ከመቅሰም እንዳንቦዝን ፈዘዝ ቀዘዝ ቆረጠኝ ፈለጠኝ አያልን እንዳንዳከም የሚያግዝ ልጅ አዋቂ ሴት ወንድ ሳይሉ ሁሉን ያቀፍ መልዕክት ነብዩ (ﷺ) አስተላልፈውልናል፡-
«ዕውቀትን መፈለግ በእያንዳንዱ ሙስሊም ላይ ግዱታ ነው»››
(አልባኒ ሰሂህ ብለውታል)
ውድ እህቴ! ሸሪኣዊ ዕውቀትን ከመፈለግ እድሜ ፆታ መሰል ምክንያቶች ፈፅሞ ሊያግዱሽ አይገባም!ሌላው ዒልም የወንዶች ስራ ነው እኔን አይመለከተኝም ብለሽ ራስሽን እንዳትሸነግይ! አደራ እንዳትሳነፊ! በዲናችን ላይ በወርቅ የሚፃፍ ታላቅ ጀብድ ፈፅመው ያለፉ እንስቶችን አትዘንጊ በዚህ ረገድ ታላቋ አርዓያሽ ውዷ እናታችን ዓኢሻ ልትሆን ይገባል፡፡ የሷን ጀብድ የኔ ደካማ ብዕር ለጊዜው ለመግለፅ ከበዳትና በይደር አለፈችው! ሴትነትሽ ክብር እንጂ የደካማነት መገለጫ አይደለም! ይልቁኑ ነቃ ብለሽ ልትተጊ ይገባል፡፡ ራስሽንም ለዚህ ታላቅ ተግባር እንድታዘጋጂ አደራ እልሻለሁ፡፡ ዕውቀት ለመቅሰም በምታደርጊው ጥረት ድካም ብጤ ተሰምቶ ተራራን የመውጣት ያክል ካሰላቸሽ ይህችን ሀዲስ አስታውስሻለሁ ፡-
‹‹«ዕውቀትን ለመፈለግ መንገድ የጀመረ አላህ ወደ ጀነት የሚያስገባውን መንገድ ይመራዋል!»
(ሙስሊም ዘግበውታል)
ታዲያ ከዚህ በላይ ብርታት የሚለግስ ማነቃቂያ አለን? ጀነት እኮ ነው!
በሌላም ሀዲሳቸው መልዕክተኛው (ﷺ) ሌላ ብስራት አክለውልሻል፡-
‹‹«ዕውቀትን ለሚፈለግ ሰው መልዕክቶች ክንፎቻቸውን በደስታና በእርካታ ዝቅ ያደርጉለታል»›
›(አህመድ ዘግበውታል)
እንግዲህ ይህች ከውቂያኖስ በመርፌ ተነክራ እንደወጣች ውሃ ስለ ሸሪያዊ ዕውቀት አስፈላጊነት የምትዘክር አጭር ማስታወሻ ናት፡፡በበለጠ ለመገንዘብ ከውድ ጊዜሽ ቆርሰሽ በመስጠት ዕውቀትሽን ለማዳበር እና ዲንሽን ለመገንዘብ እንድትጥሪ የማንቂያ ደውል ለማሰማት ያህል ነው፡፡ አላህ ለጥሪው ጆሮ ከሚሰጡ መልካሞች ያድርግሽ!
መሰነባበቻ!…
ታላቁ ሶሃብይ ኢብኑ መስዑድ እንዲህ ይላል፡-
‹«ዕውቀት በአላህ ከመወሰዷ በፊት አካብቷት»
ማለትም አላህ የእውቀት ባለቤቶችን (ዑለማዎችን) ወደ አኼራ ከመውሰዱ በፊት ማለት ነው፡፡
መልካም የዒልም ፍለጋ ጊዜ!
ፀሃፊውንም አንባቢውን አላህ ተጠቃሚ ያድርገን!
BY ABU HAMMAD
No comments:
Post a Comment