የደስታ ጉዞ
ደስታ የሁሉም ህልም ነው፤ ሁሉም ሠው ከሐሳብና ጭንቀት ነጻ
የሆነ ህይወትን ይመኛል። ሁሉም ግን የተመኘውን አያገኝም። ደስታን ለመፈለግ የጭንቀትና የዕድለ ንፍግነትን መንገድ
የሚከተልም አለ። ፍለጋው ተቃራኒ ውጤት ያስገኝለታል።
ደስታ ዝም ብሎ በፍላጎት ብቻ የሚገኝ ሀብት አይደለም። የሚመነጭባቸው እምነታዊና ድርጊታዊ መሠረቶች አሉት። ደስታን
ለማግኘት እነዚሁ መሠረቶች ማወቅና መተግበር ያስፈልጋል።
ትልቁና ዋነኛው የደስታ መሠረት በመልካም ስራዎች የተደገፈ እውነተኛ ኢማን ነው። የውሸት ካባ የደረበ ኢማን፣ ከመልካም ስራዎች ራሱን ያራቆተ ኢማን ፣ የአንደበት ብቻ ኢማን፣
ከጥቅም ጋር ሙቀትና ቅዝቃዜው ከፍና ዝቅ የሚል ኢማን ፣ በዚህ ውስጥ አይካተትም።
“ከወንድ ወይም ከሴት እርሱ አማኝ
ኾኖ በጎን የሰራ መልካም ኑሮን በእርግጥ እናኖረዋለን፡፡ ይሠሩትም ከነበሩት ነገር በመልካሙ ምንዳቸውን እንመነዳቸዋለን፡፡ ” «ነህል 97»
የማይለወጥ የአላህ ቃልኪዳን ነው። ንፁህ እምነትን ከመልካም
ስራዎች ጋር ያቀናጀ የደስተኛ ህይወት ቃል አለው። በመጨረሻም ዓለም መልካም ስራ ውጤትን ያገኛል።
መልካም ስራዎችን ማፍራት የቻለ ንፁህ ኢማን ያለው ሠው ልቦናውና ተግባሩ በመልካም ባህሪያት የታጨቁ በመሆናቸው
እነዚህ መልካም ባህሪያት በሚለግሱት የነጻነት ፣ የበጎ ሐሳቢነት ፣ የብሩህነት ዕይታ ምክንያት ደስታን ይጎናፀፋል። ሐሳብና
ጭንቀት ወደ አጠገቡ የመድረስ ኃይል አይኖራቸውም። የንፁህ ኢማን ባለቤቶች ደስታና ስኬት ሲያጋጥማቸው ይህን ሁሉ ላደረገላቸው
አላህ ምስጋናቸውን ያቀርባሉ። የአላህ ቸርነት ባይሆን ህልማቸው የሚሳካ እንዳልነበረ በሙሉ ልብ ያምናሉ። ለዓለማቱ ጌታ
ራሳቸውን ዝቅ ያደርጋሉ። አላህ የለገሳቸውን ችሮታም እርሱ በሚወደው ነገር ላይ ያደርጋሉ። ደስታቸው ሌላን ደስታ ይወልዳል፤
ስኬታቸው ሌላ ስኬትን ይጨምራል።
ችግርም ሲያጋጥማቸው በሠፊ ትዕግስት ያስተናግዱታል። በመከራ ፊት ጥንካሬያቸው አይሳሳም፤ በቁርጠኝነት ይጋፈጡታል።
ከችግራቸው ለመውጣት በአላህ ታገዛሉ። በትክክለኛ ሠነድ በተላለፈ ሐዲስ ነብዩ (የአላህ ሠላምና ሠላት በርሳቸው ላይ ይሁን)
እንዲህ ብለዋል
“የሙዕሚን ሁኔታ እጅግ የሚያስገርም ነው፤ ሁሉም ጉዳዩቹ መልካም ናቸው፤ ደስታ ሲያጋጥመው አላህን ያመስግናል፤
(የነገሩ ፍፃሜም) መልካም ይሆንለታል። መከራ ሲያጋጥመው ትዕግስትን ይላበሳል፤ (የነገሩ ፍፃሜም ) መልካም ይሆንለታል።
ይህ የሚሆነው
ለሙዕሚን ብቻ ነው። “
ንፁህ ኢማንን የታደለ ልብ እና ኢማንን የተነፈገ ልብ ክስተቶችን የሚያስተናግዱበት ሁኔታ በጣም የተለያየ ነው።
ንፁህ ኢማን ክስተቶችን በምስጋናና በትዕግስት ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ሲያስተናግድ ኢማን የተነፈገ ልብ መስተንግዶው ከዚህ
ይርቃል። ስኬት ካጋጥመው ኩራቱ አፍንጫውን ይሻገራል። ትህምክት እና ማን አለብኝነት ይጠናወተዋል። ስነ- ምግባሩ ይዘቅጣል።
ከርሱ በላይ ደስተኛ እንደሌለ ለማሳየት ይሞክራል፤ ሆኖም ግን ደስታዎቹ አካላዊና ቁሳዊ ብቻ ናቸው፤ ወደ ውስጥ የጠለቀና ልብን
በእርካታ የሚዳስሱ «መንፈሳዊ» አይደሉም። ከዚህ ጀብደኝነት በተቃራኒ ደግሞ መከራን
በከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ ያስተናግዳል። በችግሩ ፊት በጥንካሬ ለመቆም አይችሉም፤ ፍርሃት ያንዘፈዝፈዋል። በችግሩ ወቅት አላህን
ማስታወስ ስላማይችል የሚደርስበት ስቃይ ብዛትና ክብደት አይጠየቅም። ስነ - ልቦናው ይደቃል፤ መንፈሱ ይናወጣል። ራሱን መምራት
ይሳነዋል።
وَمَنْ أَعْرَضَ عَن ذِكْرِي فَإِنَّ لَهُ مَعِيشَةً ضَنكًا
وَنَحْشُرُهُ يَوْمَ الْقِيَامَةِ أَعْمَىٰ [٢٠:١٢٤]
«ከግሣጼዬም የዞረ ሰው ለእርሱ ጠባብ ኑሮ አለው፡፡ በትንሣኤም ቀን ዕውር ኾኖ እንቀሰቅሰዋለን፡፡ (ጠሀ - 124)
አላህ ሁሌም እርሱን የምናስታውስበት ንፁህ ኢማን ይለግሠን፤ እንደ ምስራቅና ምዕራብ በእኛና በኢማን ባዶነት መካከል መራራቅን ያድርግን!
No comments:
Post a Comment