አል ሂጃብ
አላሁ (ሱብሃነሁ ወተአላ) ሴትን ልጅ ካዘዘበት ነገር የርሷ ተቃራኒ ባእድ ከሆነ ወንድ አልያም እርሷን ሊያገቡ ከሚችሉ ወንዶች ጋር ለሚኖራት ግንኙነት ያስቀመጠላት መስፈርት ነው፡፡እርሱም ሂጃብ ነው፡፡
ሂጃብ የአማኝ ሴት መገለጫ የንጽህናዋ ማስታወቂያ ነው። እንዳትደፈርና ክብሯ እንዳይነካ መከላከያ መሳሪያዋ:: ሂጃብ የለበሰች ሴት በህይወት ጉዞዋ የነቃችና የበቃች ናት ፡፡ ለራሷም ይሁን ለሌሎች በምታበረክተው መልካም አስተዋጽኦ በጽናት እንድትወጣ ሂጃብ ታላቁ ደጋፊዋ ነው ፡፡ ምክንያቱም፡- ለሰው ልጆች አጥፊና አውዳሚ ከሚባሉት ሁለት ፈተናዎች ውስጥ አንዱ የሆነውን የስሜትን ፈተናን በሂጃብ ልጎም እንዳትሰረው ስለሚያስችላት ነው፡፡
አዎ! ህጋዊ ሃላል ባልሆነ መንገድ የሚደረግ ልቅ የሆነ የሁለት ተቃራኒ ጾታዎች ግንኙነትና መደባለቅ ከግለሰብ አልፎ ማህበረሰብን ያወደመ ከባድ ወረርሽኝ ነው፡፡ የታሪክ መዛግብትን ብናገላብጥ ይህ የወረርሽኝ ምችና ልክፍት አጣሞ ጥሏቸው የጠፉና እየጠፉም ያሉ ህዝቦችን እንመለከታለን፡፡ በዚህ ስሜት ላይ ያላቸው እይታ ልጔመ ቢስ ልቅ በመሆኑ ለራሳቸውም ይሁን ለሌሎች መልካምና ጠቃሚ ነገሮችን የማበርከት መቅኒያቸውን አፈሰሰባቸው ፡፡ታዲያ በትምህርት ገበታውም ይሁን በስራ ቦታዎች ላይ ሳይቀር ፍጹም ዘግናኝና እንስሳዊ ግንኙነቶቸ ተንሰራፋ ፡፡ፈጣሪ ያስቀመጠውን ተስማሚና ምቹ ህግን በመጣሳቸው የሚደሰቱበትና የሚረኩበት ቢያጡ ከእንስሳውም ከግኡዙም አካል ጋር ተያያዙት ፡፡በተመሳሳይ የጾታ ባለቤቶች መካከልም የሚደረገው ግንኙነት እዚህ ውስጥ የሚገባ ነው ፡፡በርግጥ ይህ ለናሙና ተገለጸ እንጂ የዚህ የዘቀጠ ግንኙነት አራማጆች አጠቃላይ ሁኔታና የዘቀጡበትን የጥፋት ማእበል እንዘርዝር ቢባል ብእሮች በዋዛ የሚወጡት አይሆንም ፡፡እንደሚባለው “ብልጥ ልጅ በጥቆማ ይገባዋል” በማለት በዚህ ብንወሰን ይሻላል፡፡
ኢስላም ከዚህ አይነት መስመር ዘለልና ፈር ለቀቅ አካሄድ ለመዳን የጥፋቱ ሰለባ ከመሆን ለመቅረፍ ለሴት ልጅ ሂጃብን ደንግጔል ፡፡ አላሁ (ሱብሃነሁ ወተአላ) እንዲህ ብሏል ፡-
وَقُل لِّلْمُؤْمِنَاتِ يَغْضُضْنَ مِنْ أَبْصَارِهِنَّ وَيَحْفَظْنَ فُرُوجَهُنَّ وَلَا يُبْدِينَ زِينَتَهُنَّ إِلَّا مَا ظَهَرَ مِنْهَا ۖ وَلْيَضْرِبْنَ بِخُمُرِهِنَّ عَلَىٰ جُيُوبِهِنَّ ۖ وَلَا يُبْدِينَ زِينَتَهُنَّ إِلَّا لِبُعُولَتِهِنَّ أَوْ آبَائِهِنَّ أَوْ آبَاءِ بُعُولَتِهِنَّ أَوْ أَبْنَائِهِنَّ أَوْ أَبْنَاءِ بُعُولَتِهِنَّ أَوْ إِخْوَانِهِنَّ أَوْ بَنِي إِخْوَانِهِنَّ أَوْ بَنِي أَخَوَاتِهِنَّ أَوْ نِسَائِهِنَّ أَوْ مَا مَلَكَتْ أَيْمَانُهُنَّ أَوِ التَّابِعِينَ غَيْرِ أُولِي الْإِرْبَةِ مِنَ الرِّجَالِ أَوِ الطِّفْلِ الَّذِينَ لَمْ يَظْهَرُوا عَلَىٰ عَوْرَاتِ النِّسَاءِ ۖ وَلَا يَضْرِبْنَ بِأَرْجُلِهِنَّ لِيُعْلَمَ مَا يُخْفِينَ مِن زِينَتِهِنَّ ۚ وَتُوبُوا إِلَى اللَّهِ جَمِيعًا أَيُّهَ الْمُؤْمِنُونَ لَعَلَّكُمْ تُفْلِحُونَ [٢٤:٣١]
«ለምእምናትም ንገራቸው፡- ዓይኖቻቸውን ይከልክሉ፡፡(ሰበር ያድርጉ) ብልቶቻቸውንም ይጠብቁ፡፡ ጌጣቸውንም ከእርሷ ግልጽ ከሆነው በስተቀር አይግለጡ፡፡ ጉፍታዎቻቸውንም በአንገትጌዎቻቸው ላይ ያጣፉ፡፡ (የውስጥ) ጌጣቸውንም ለባሎቻቸው ወይም ለአባቶቻቸው ወይም ለባሎቻቸው አባቶች ወይም ለወንድ ልጆቻቸው ወይም ለባሎቻቸው ወንድ ልጆች ወይም ለወንድሞቻቸው ወይም ለወንድሞቻቸው ወንድ ልጆች ወይም ለእህቶቻቸው ወንድ ልጆች ወይም ለሴቶቻቸው ወይም እጆቻቸው ለያዙት (ባሪያ) ወይም ከወንዶች ለሴት ጉዳይ የሌላቸው ለሆኑ ተከታዮች ወይም ለነዚያ የሴቶችን ሐፍረተ ገላ ላላወቁ ሕፃኖች ካልሆነ በስተቀር አይግለጹ፡፡ ከጌጣቸውም የሚሸፍኑት ይታወቅ ዘንድ በእግሮቻቸው (መሬትን) አይምቱ፡፡ ምእመናኖች ሆይ! ትድኑ ዘንድ ሁላችሁም ወደ አላህ (በመመለስ) ተጸጸቱ፡፡»(ምእራፍ አንኑር ቀጥር 31)
ሴት ልጅ ሂጃብ በመልበሰ ወንዶች እርሷን አይተው ከመፈተን ትጠበቃለች፡፡ ኧረ እንዲያውም አይናቸውን ሰበር ለሚያደርጉ ብርቅዮዎች ብቻ ሳይሆን ላይ ታቹን ለሚያማትሩትም አደብ ታስገዛበታለች፡፡
ምክንያቱም ምንም ቢቁለጨለጩ የሚያገኙት ነገር የለምና ነው፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው የምትገላለጥ ከሆነ የፈተና የጥፋት በር በማይዘጋ መልኩ ይበረገዳል፡፡ በዘመናችን ያለውን ሁኔታ ያስተዋለ አላህ ያዘነላት ካልሆነች በስተቀር ሴት ልጅ በገዛ እራሷ ክብሯን አሽቀንጥራ ወርውራዋለች፡፡
በሰበቡም የቂሎችና ጅቦች ጉርሻና እራት ሆና አንግታለች፡፡ አይንሽ፣ከንፈርሽ፣ዳሌሽ ብለው በማማለል የማይረግብ ስሜታቸው ማርኪያ ሎሌ አድርገዋታል፡፡ እርሷም የዚህ መርዝ ያስቀረባት ጠባሳ ይመስላል ፊቴ አምሮ ቅርፄ ተስተካክሎ ይሆን እያለች የነሱ የወሲብ መግነጢስ ሆኖ ከመቅረት ውጪ ሌላ ግብና አላማ በእጅ አልልሽ ብሏታል፡፡
ይባስ ብሎ አሁን አሁንማ ለዚሁ ከንቱ አላማ የህይወት መስዋዕትነትም እየከፈለችበት ይገኛል፡፡
አፍንጫ፣ አይን ፣ከንፈር ፣ ሆድና የመሳሰሉትን ቀዶ ጥገና በማድረግ አምሮና ሸንቅጦ ለመቅረብ የሚደረገው መራወጥ ለዚህ በቂ ምስክር ነው፡፡ይህ መሰል ከምእራቡ አለም የመጣው አባዜ ሙስሊሙንም አለም እየናጠው ይገኛል፡፡እዚህ ጋር ሊታወቅ ሚገባው ነገር ምእራቡ አለም ላይ ልብስ ለጌጥነት እንጂ ለሲትርነት እንደማይውል ነው፡፡ ሙስሊሞች ዘንድ ግን የዚህ ተቃራኒ ነው ፡፡
ልብስ መሰረታዊ አላማው አፍረተ ገላዎችን ለመሸፈንና ለመደበቅ ነው፡:
አላህ (ሱብሃነሁ ወተአላ) ይህን ሲናገር እንዲህ ብሏል:-
يَا بَنِي آدَمَ قَدْ أَنزَلْنَا عَلَيْكُمْ لِبَاسًا يُوَارِي سَوْآتِكُمْ وَرِيشًا [٧:٢٦]
«የአደም ልጆች ሆይ ሃፍረተ ገላችሁን የሚሸሽግ ልብስ ጌጥንም በርግጥ በእናተ ላይ አወረድን»(7:26)
ከላይ ያሳለፍነው ምእራፎች ላይ አላሁ (ሱብሃነሁ ወተአላ) ለጠቀሳቸው የወንድ ክፍሎች ካልሆኑ በስተቀር ሴት ልጅ ሂጃብ እንድታደርግና እንዳትገላለጥ ትእዛዝ አስተላልፏል፡፡ እንዲሁም ከዚሁ ጎን ለጎን ለእርሷ ባእድ ለሆኑ ወንዶች ብቻ ሳይሆን ከሴቶችም ጋር ስትሆን ልትለብሰው የሚገባውን በግልፅ አስቀምጧል። ይሄውም አንቀፁ ላይ እንደተቀመጠው ለእርሷ መህረም ወይም ሊያገቧት ከሚከለከሉት ወንዶች ፊት የምትለብሰውን ልብስ ነው ለሴቶችም መልበስ ያለባት። ይህ ከሆነ እንግዲህ አሁንም ምን ያህል ከመራቆት መራቅ እንደሚገባ መገመት አያቅትም።
No comments:
Post a Comment