Wednesday, 27 January 2016

PART 5 የእንስቶች ወርሃዊው ዙር

① ሀይድ ወይም ጀናባ የገጠማቸው ሰዎች ቁርኣንን ስለመንካት ያለው ድንጋጌ
   ከነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንደተነገረው
« ንፁህ ካልሆነ (ሰው) በስተቀር ቁርኣንን አይንካው። » ብለዋል የሚለውን ሙርሰል ሀዲስ ምሁራን ተቀብለውታል። ይህንንም በማስመልከት ሸይኹል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያ ቀጣዩን አስተላልፈዋል።

{ ኢማሙ አህመድ እንዳሉት ነቢዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ቁርኣንን ንፁህ ያልሆነ ሰው አይንካው የሚለውን ለየመን ህዝቦች በፃፉት ደብዳቤ ላይ ማስፈራቸው ጥርጥር የለበትም።

   እንዲሁም ይህ ቃል የሰልማን አልፋሪሲ እና የአብደላህ ኢብኑ ዑመር ብሎም የሌሎች ሰሃቦች ጭምር ነው። ከሰሃቦች መካከልም ይህንን የሚቃረን አይታወቅም። } ሲሉ ሀይድ ወይም ጀናባ በገጠመን ወቅት ቁርኣን በአካል ቀጥታ መነካት እንደሌለበት አስረድተዋል።

   እንደሚታወቀው ንፁህ ሲባል የቃሉ ትርጉም ሁሉንም አይነት ንፅህና ያጠቃልላል። ከሽርክና ወንጀሎች መፅዳትን፣ ከነጃሳዎችና ቆሻሻዎች መፅዳትን፣ እንዲሁም ከትንሹ ሀደስና ከትልቁም መፅዳትን ያጠቃልላል።

  *** በዚህም መሰረት ሀይድ ላይ ላለች ሴት ቁርኣንን ለሂፍዝም ሆነ ለትምህርት መንካት አይፈቀድላትም። ነገር ግን ሳትነካው መቅራትን ከላይ እንደሰፈረው ውስን በሆኑ ሁኔታዎች ብታነብ ችግር የለውም።

  አንዳንድ ሊቃውንት እንደሚሉትም ቁርኣንን ለመንካት፣ ለመያዝ አማራጭ የሌለው አስገዳጅ ነገር ከተፈጠረ እንኳን መነካት ያለበት ቀጥታ በአካል ሳይሆን በጨርቅና በመሳሰሉት ሽፋን መሆን አለበት። ይህንን በማስመልከት ሸይኩል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያ አክለው ሲያስረዱ:

« ንፁህም ባይኮን  መፅሀፉ ሳይነካ ከመፅሀፉ ወይም ከሰሌዳ ላይ ቢነበብ ይፈቀዳል። » ብለዋል።
በሌላም በኩል ሲያስረዱን
" لا تقرأ الحائض، ولا الجنب شيئاً من القرآن " فهو حديث ضعيف.

«  ሀይድ ላይ ያለች ሴትም ትሁን ጀናባ የሆነ ሰው ከቁርኣን ምንም ነገር አይቀራም»   የሚለው ሀዲስ ደዒፍ የሆነ ሀዲስ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም።

ጀናባ ላይ ያለ ሰውን በተመለከተ ግን
هناك حديث صحيح أن النبي صلى الله عليه وسلم  لا يمنعه شيء عن القرآن إلاَّ الجنابة
ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም
« ቁርኣንን ከመቅራት ከጀናባ በስተቀር የሚከለክል የለም » ብለዋልና ወንድም ይሁን ሴት ጀናባ እስከሆኑ ድረስ ቁርኣንን በልባቸውም ሆነ ከፅሁፍ ላይ ማንበብ አይፈቀድም።
እንዲሁም ቁርኣንን መንካትም አይፈቀድላቸውም።
   እንደሚታወቀው ቁርአንን ሳንነካው የምንቀራበት ሌሎች መንገዶች ኣሉና ለማንበብ ሲባል መንካቱ ግዴታ አይደለም። በሂፍዝ መቅራት አንዱ ሲሆን፤ ብዙ ኡለማዎች እንደተስማሙበትም የሙስሀፍ ህግጋት አይመለከቱትምና ከተፍሲርና የቁርአን ፍቺ ካላቸው መፅሀፎች በመጠቀም መቅራት ትችላለች።

  ባሁኑ ጊዜም የተለያዩ ተች የማያስፈልጋቸው ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች አሉ፤ እነዚህን መጠቀም ችግር እንደሌለው አያጠራጥርም። ነገር ግን የተለያዩ ተች ስክሪን ሞባይሎችና መሳሪያዎች ላይ መቅራትን በተመለከተ ታላቁ አሊም ሸይኽ አብዱልከሪም አልኹደይር ተች ማድረግ ወይም በእጅ መንካት እንደማይፈቀድ  ተናግረዋል። በድምፅ የሚታዘዝ ወይም የሞባይሉን በተኖች (ቁልፎች) በመጠቀም ከገፅ ወደገፅ መሄድ የምንችልበት ከሆነ ግን ችግር የለውም እንደዚሁም ንት በመጠቀም ስክሪኑን መንካት ችግር የለውም።

②  ሀይድ ላይ ያለች ሴት ቁርኣንን ሳትነካ መቅራት የምትችልባቸው ሁኔታን በተመለከተ የሸይኽ ሷሊህ አል ዑሰይሚን ረሂመሁላህ ማብራርያ

« ሀይድ ላይ ያለች ሴት ለአስገዳጅና አስፈላጊ ጉዳይ ቁርኣንን ማንበብ ትችላለች።
   ለምሳሌ
1 መምህር ብትሆንና ተማሪዎቿን ለማስተማር ፣ እንዲሁም
2 ተማሪ ሆና ቁርኣንን ለመማር ስትል ፣ ወይም
3 ልጆቿን ለማስተማር ስትል 
እነሱ የሚቀሩትን ታርማለችም ቀድማቸውም ታነብላቸዋለች። ባጠቃላይ አስፈላጊ ሁኔታ ከገጠማት ማንበብ ይፈቀድላታል ፤ ችግርም የለበትም።

  በተጨማሪም የቀራችው ቁርኣን እንዳይረሳት ለማስታወስ ስትል ማንበብ ትችላለች። በዚህም ሀይድ ላይ መሆኗ ችግር አይፈጥርባትም።
   ባጠቃላይ ሀይድ ላይ ያለች እንስት ቁርኣንን ሳትነካ ማንበብን በተመለከተ በምሁራን መካከል ሶስት አይነት አስተያየቶች ይገኛሉ።

F አንዳንድ ምሁራን ሀይድ ላይ ያለች ሴት ያለ ምንም አስፈላጊ ጉዳይ ቁርኣንን ማንበብ ትችላለች ሲሉ

F ሌሎች ደግሞ አስፈላጊ ጉዳይ እንኳ ቢገጥማት ቁርኣንን ማንበብ ሀራም ይሆንባታል ይላሉ፡፡
F ሶስተኛው አቋም ደግሞ እንደ ማስተማር፣ መማርና እንዳትረሳው በመስጋት በመሳሰሉት ቁርኣንን ለማንበብ የሚያስፈልጋት ጉዳይ ሲገጥማት ብታነብ ችግር የለባትም። የሚል ነው። ይህ ሶስተኛው አስተያየት ተቀባይነት ያለውና ሚዛን ደፊ አቋም ሊባል የሚገባውም ነው።»
مجموع فتاوى ورسائل الشيخ محمد صالح العثيمين - المجلد الحادي عشر - باب الحيض.
 ማጠቃለያ፤
🌸በሀይድ ጊዜ ቁርኣንን መንካትን በተመለከተ  ቀጥታ በእጅ ወይም በሌላ አካሏ መንካት አይፈቀድም። በጓንትና መሰል ጨርቅ በመጠቀም መቅራት ለችግር ግዜ ተፈቅዷል።
🌸 ጀናባ ላይ የሆነ ወንድም በተመሳሳይ መንካት አይፈቀድለትም።
🌸 ከሚቀራ ሰው ጋርም ይሁን ለብቻ ቁርአኑን ሳትነካው መቅራትን በተመለከተ አስፈላጊ የሚሆንባቸውን ሁኔታዎች ገልፀን በሌላ ጊዜያት አለመቅራቷ የተሻለ መሆኑን የሊቃውንት ማብራርያን አስፍረናል።
🌸 ከሞባይል ላይ የቁርአንን ፅሁፍ ተች በማድረግ መንካት አይፈቀድም።  በሌላ መንገድ ስክሪኑ ሳይነካ ቁርአኑን መግለፅና ሶፍርዌሩን መጠቀም ከተቻለ በዚህ መልኩ መቅራት ግን ችግር የለውም።

አህመድ (አቡ ፈውዛን)


No comments:

Post a Comment