አሁን አሁን የሚለበሱ አልባሳቶች ኢስላም አይደለም የኢትዮጵያ ባህልም አይፈቅደውም። የውስጥ ልብሶችን ሳይቀር የሚያሳይ፤እያንዳንዱን የሰውነት ቅርፅና ከፍፍል ቁልጭ አድርጎ የሚያስቃኝ ልብስ መልበስ ልማዳዊ ሆኗል። አላህ ይጠብቀን።
አሁን አንቀጹ ላይ ያለውን የሂጃብ ድንጋጌ በዝርዝ ከማየታችን በፊት ኢስላማዊ የሂጃብ መስፈርቶችን ለማስቀመጥ እሞክራለሁ ፡-
ኢስላማዊ የሂጃብ መስፈርቶች
1. ሙሉ የሰውነት ክፍልን መሸፈን አለበት::
2. ጠባብ ሆኖ የሰውነትን ቅርፅ የሚያስገምት መሆን የለበትም::
3. ስስ ሆኖ የሰውነት ከለርን ማሳየት የለበትም::
4. ያሸበረቀና እይታን የሚስብ መሆን የለበትም::
5. ለየት ብሎ ዝናን ለማትረፍ የሚለበስ መሆን የለበትም::
6. ከወንዶች ልብስ ጋር መመሳሰል የለበትም::
7. የሌሎች ሀይማኖት መለያ ልብስ ሆኖ የሚያገለግል መሆን የለበትም::
አላሁ (ሱብሃነሁ ወተአላ) ባሳለፍነው አንቀጽ ላይ ሴት ልጅን በሂጃብ ሲያዝ እንዲህ ብሏል ፡-
وَلَا يُبْدِينَ زِينَتَهُنَّ إِلَّا مَا ظَهَرَ مِنْهَا
«ጌጣቸውንም ከእርሱ ግልጽ ከኾነው በስተቀር አይግለጡ፡፡»
እዚህ ጋር ታላቁ የተፍሲር ባለቤት ኢብኑ ከሲር ይህን አስመልክቶ ዓብደላህ ኢብን መስኡድ እንዲህ ማለቱን ተናግሯል፦
ይህ ማለት ልብሳቸውንና የሚያጣፉትን ማለት ነው” በመቀጠልም ኢብኑ ዓባስና ተከታዮቹ ይህንን በፊትና መዳፎች እንደፈሰሩትም አስቀምጧል። (ተፍሲር ኢብኑ ከሲር)
ሸይኽ አብዱራህማን ቢን ናስር አስሰዕዲ አላህ ይዘንላቸውና ይህን አንቀጽ አስመልክተውም ሲተረጉሙ እንዲህ ብለዋል፦
“ማለትም ግልጹን ሲባል ልብሱን ማለት ነው ፡፡ይህም በተለምዶ የሚለበሰው ነው። ወደ መፈተን የማይጠራ እስከሆነ ድረስ” ሱብሃነላህ! እዚህ ጋር አላህ (ሱብሃነሁ ወተአላ) ግልጽ ከሆነው በስተቀር አለ እንጂ ግልጽ ካደረግነው በስተቀር አላለም፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዥነት ፊትን በመግለጽ የሚነሱ ጥያቄዎች በሚከተለው መልኩ ባጭሩ ተብራርቷል፡፡
በመጀመሪያ ፊት ስለመግለጽ የሚወሩ ሃዲሶች ደካማዎች ሲሆኑ
አንዳንድ ትክክለኛዎችም አሉበት፡፡
ከደካማዎች ውስጥ ይሄ ይገኝበታል፦
የአዒሻ ሀዲስ ሲሆን አስማዕ ቢንት አቢበክር (ረድየላሁ አንሀ) ወድ ነብዩ (ﷺ) ገባች፡፡ እላይዋ ላይ ያለው ስስ ልብስ ነበር ነብዩም (ﷺ) ከእርሷ ዞሩና እንዲህ አሉ፡-
«አስማዕ ሆይ ሴት ልጅ ለአካለ መጠን ከደረሰች እርሷን ማየት አይቻልም። ይህና ይህ ሲቀር። ከዛም ወደ ፊታቸውና እጃቸው አመለከቱ»
ትክክል ከሆነው ደግሞ ኢብን አባስ (ረድየላሁ አንሁ) ያወራው ሃዲስ ነው እንዲህ ብሏል :-
«(የሃጅ ወቅት ሆኖ) የእርዱ ቀን ነበር ነብዩ (ﷺ)አልፈድል ኢብን አባስን በመጔጔዣቸው ኃላ አፈናጠጡት:: አል ፈድል የሚያምር ወንድ ነበር:: ነብዩ (ﷺ) ቆሙና ለሰዎች ብይን (ፈትዋ) ይሰጡ ጀመር:: ከየመን የምታምር የሆነች ሴት ወደ ነብዩ (ﷺ) መጥታ ፈትዋ ትጠይቃቸዋለች:: ነብዩ (ﷺ) ዞሩ:: አል ፈድል ደግሞ ውበቷ ማርኮት ወደ እሷ እየተመለከተ ነበር። ነብዩም (ﷺ) በእጃቸው በመመለስ የአልፈድልን አገጭ ይዘው ከእርሷ እይታ በማዞር አሰተካከሉት።”´
(ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)
እዚህ ጋር ታልቁ ሸይኽ አብዱል ሙህሲን አል ዓባድ (አላህ ይጠብቃቸውና) ይህንን ሃዲስ ፊት ስለመግለጥ ማስረጃ ስለማድረግ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:- “
«ሴት ፊቷን ስለመግለጥ ይህን ሀዲስ ማስረጃ የሚያደርጉ ይህ አጠቃላይ ሳይሆን ውስን ሁኔታን አመልካች ነው:: ስለዚህ ይህ ሀዲስ በጣም በርካታ የቁርአንና የሀዲስ ማስረጃዎችን ፈጽሞ የሚቃወም አይደለም። ሌላው ይህች ሴት ኢህራም ላይ ነበረች። ስለዚህ ፊቷን የገለጠችው ለኢህራሙ ሊሆን ይችላል ፡፡ምክንያቱም በሀዲስ ውስጥ ይህ እንዳለ አሳልፈናል:: ቡኻሪ በዘገቡትና ዓብደላህ ኢብን ኡመር እንዳወራው የአላህ መልእክተኛ ﷺ ይህን ተናግረዋል:-
«ኢህራም ውስጥ ያለች ሴት ለፊቷ መሸፈኛ የተዘጋጀውን (ኒቃብ)ና ጔንት አትለብስም»
አሊያም ይህ መገለጽ ለሌላ ጉዳይም ሊሆን ይችላል። ምሳሌ ነብዩ (ﷺ ) እንዲያገቧት ፈልጋ ሊሆን ይችላል:: ሀፊዝ ኢብኑ ሀጀር ይህንን በፈትሁል ባሪ (4/68) የአቢያዕላ ሙስነድ ላይ ይህንን የሚያመለክት የጠነከረ ሰነድ እንዳለ ጠቅሰዋል፡፡
እንግዲህ ለአንዲት በንጽህናና ጨዋነት ህይወት መድመቅና መፍካት ለምትሻ አማኝ ይህ ማስረጃ ከበቂዋ በላይ ነው::
" ኡስታዛ ነፊሳ ሙሀመድ
No comments:
Post a Comment