የምርጧ አርዓያሽ የመልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ልጅ የፋጢማ ረዲየላሁ ዓንሃ ታሪክ
ተወዳዳሪ ካልተገኘላቸው እፁብ ድንቅና የሙስሊሟ ሴት አርዓያ ከሆኑት እንስቶች መካከል ፋጢማ ቢንት ሙሀመድ (ﷺ) በቀዳሚነት ትጠቀሳለች፡፡
ፋጢማ ረዲየላሁ ዐንሃ ለአባቷ ታዛዥና ወዳጅና አክባሪ ልጅ ናት።
F ባሏን አፍቃሪ፣ አክባሪና ተንከባካቢ ሚስትም ነበረች።
F ልጆቿን በጥሩ ምግባር ኮትኩታ በማሳደግም ምርጥ እናት ነበረች።
F በቤተዘመዶቿ ዘንድ በጥሩ ባህሪዋ የተከበረች ነበረች።
F ከጎረቤቶቿ ወቀሳ ያልተሰማባት ኩሩ ሴት ነበረች።
F ከምዕመናት እንስቶች ጋር ባላት ግሩም የመኗኗር ብቃት ተወዳሽ እህታቸው ነበረች።
ፋጢማ ረዲየላሁ ዐንሃ ከአንዲት ሙስሊም ሴት የሚጠበቀውን ለወላጇ ለባሏ፣ ለልጆቿ፣ ለጎረቤቶቿና ለቤተሰቦቿ እንዲሁም ለማህበረሰቧ መልካም የመሆን ብቃትን ተወጥታለች። ለዚህም የአማኝ እንስቶቻችን የምን ግዜም አርዓያ ሆናለች። ረዲየላሁ ዓንሃ ወአርዷሃ።
ለዛሬ የምንመለከተው የህይወቷ ክፍል ከባሏ ያላትን የመተጋገዝና ቤቷን የመንከባከብን አንድ መልእክት እናካፍላችኋለን።
አሊይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላሉ፤ « ፋጢማ ከስራ ብዛት በእጇ ላይ የሚደርሰውን ህመም አማረረችና፤ ሰራተኛ እንዲሰጣት ለመጠየቅ መልእክተኛው ﷺ ዘንድ ሄደች። ነገር ግን አላገኘቻቸውምና ለባለቤታቸው ለዓኢሻ ተናግራ ተመለሰች። ዓኢሻም ሲመጡ ነገረቻቸው።
የአላህ መልክተኛም ﷺ ጉዳዩን እንደሰሙ ወደኛ ሲመጡ ተጋድመን አገኙን።
ተነስቼ ልቆም ስል እዚያው በቦታህ ሁን አሉኝ። ከዚያም የእግራቸው ቅዝቃዜ ደረቴ ላይ እስኪሰማኝ በመሀከላችን ተቀመጡ ።
እንዲህም አሉን፡-
«ለናንተ ከአገልጋይ የተሻለውን ነገር ላመላክታችሁን ? ወደ ፍራሻችሁ ስትጠጉ ወይም በመኝታችሁ ላይ ስትሆኑ:•
ሰላሳ አራት ጊዜ አላሁ አክበር፣
ሰላሳ ሶስት ጊዜ ሱብሃነ'ላህ፣
ሰላሳ ሶስት ጊዜ አልሀምዱ ሊ'ላህ፣ በሉ።
ይህ ለእናንተ ከአገልጋይ የተሻለ ነውና።»
ብለዋል ሲሉ ዓሊይ ቢን አቢጣሊብ አስተላልፈዋል። ቡኻሪና ሙስሊምም ዘግበውታል።
እንደሚታወቀው ሙእሚኗ ሴት ከዚህ ታሪክ በርካታ ቁምነገሮችን ትማራለች።
① ኛ• በደስታም በሃዘንም ከውድ ባሏ ጎን ትቆማለች። በዚህም የቤት ውስጥ ጣጣዎችን ለመሸፈን በምታደርገው ጥረት ይህን ያህል እስኪሰማት እንኳ ሰርታ ባሏን ለመውቀስ ሳይሆን ለመፍትሄ ፍለጋ ነበር የተንቀሳቀሰችው።
②ኛ• በቤቷ ውስጥ ስራዎች በሚገጥሟት ድካምና ጉዳት ላይ ታጋሽ ናት።
የመልእክተኛው ﷺ ልጅና የአሚረል ሙእሚኒን ሚስት እንዲሁም የምርጦቹ የጀነት ሙሽሮች የሀሰን እና የሁሰይን እናት ታላቋ ፋጢማህ ረዲየላሁ ዐንሁም ያንን ጣጣ በትእግስት አሳልፋው ከአቅሟ በላይ ሲሆን ግን እርዳታ ፈለገች።
③ኛ• ዚክር ማለትም አላህን ማወደስ በብዙ ጎኑ ብርታት ይሰጣል
F አላህን ስናስታውስና ስናወድስ መንፈሳችንንም ሆነ አካላችንን ያበረታልናል
F እየዘከርን ስንሰራ ስራው እንዳይታወቀን ስነልቦናችን ይጠነክርና ድካማችን ይወገዳል።
F የምትረዳን ሰራተኛ ይዘን ስራውን ከመግፋት ዚክር እያልን ደክመን ብንሰራ የተሻለ ምንዳ እናገኝበታለን።
ሸይኹል ኢስላም ኢብኑተይሚያህ ረሂመሁላህ
" ይህ ዚክር እውነትም ላመነበት ሰው አካላዊ ጥንካሬን ይለግሳል።" ብለዋል።
④ኛ• አንዲት እንስት ኑሮ ከበድ ሲልባት፣ ስራ ሲጠናባት፣ አጋዥ ሲያስፈልጋት ከቅርብ ቤተሰቦቿ እርዳታ መጠየቋ፣ አጋዥ እንዲፈልጉላት ተባበሩኝ ማለቷ የሚያስወቅስ ኣለመሆኑና ገበናሽን አወጣሽ እንደማያስብል ያስረዳናል።
⑤ኛ• ሙስሊሟ የግድ የሚያስፈልጋትን ነገር ለማሟላት ከባሏ ጋር ተስማምታ ለቤተሰቧ ለማሳወቅ ኩራት አያግዳትም። ከነሱ የተሻለ ችግሯን የምታካፍለው የላትምና።
⑥ኛ• ዐሊይና ፋጢማ ፍቅራቸው ተግባራዊ በመሆኑ መልእክተኛው ሲመጡባቸው ጋደም ብለው ሲጨዋወቱ ነበር።
ደከምኩ ተጎዳሁ በሚል ጭቅጭቅ ላይ አልነበሩም። ባልም የራስሽ ጉዳይ በሚል አላራቃትም፤ ይልቅስ ከጎኗ ሆኖ ያበረታት ነበር። ባሎችም ከዚህ ብዙ ይማራሉ።
⑦ኛ• ዓዒሻ ረዲየላሁ ዐንሃ የፋጢማ እናት ባትሆንም እንኳ የደረሳትን መልእክት መልኩን ሳትቀይር፣ ሳትደብቅና ሳታቆይ ለባለቤቷ መንገሯ ታማኝነቷን፣ አዛኝነቷን፣ ቀናተኛ አለመሆኗንና ታላቅነቷን ያንፀባርቃል።
ከዚህም እንጀራ እናት የሚሰኙት ወይዘሮዎች ሊማሩ ይገባቸዋል።
☞ ውዷ እህቴ ለቤትሽ ድከሚ ታገሺም
ባልሽንም ተንከባከቢ።
አላህ ትዳር ላላገኙት መልካም ትዳር ይለግሳቸው። ተጋብተው ላሉትም ያሰማምርላቸው።
ባለቤትሽን በመኻደምና በማስደሰት ፋጢማን አርአያ ለማድረግ ዝግጁ ነሽን❓?
No comments:
Post a Comment