ከቤተሰብ ጋር በመልካም ፀባይ መኗኗር
ሙስሊም የሆነ ሰው በቅድሚያ ከፈጣሪው ጋር በዲኑ በታዘዘው መሰረት ፀባዩን አስተካክሎ መገኘት አለበት። ከዚያም ከሰዎችና ከሌሎች ፍጥረታት ጋር ተገቢ በሆነ መልካም ባህሪ መኗኗር ይገባዋል። ይህም ነቢያዊ መመርያ ነው።
የአላህ መልእክተኛ ሰለለሁ አለይሂ ወሰለም ንግግርን ኢማሙ አህመድ ሙስነዳቸው ላይ እንዳሰፈሩት
« እኔ የተላኩት መልካም ባህሪን ለሟሟላት ነው።» ብለዋል። (አህመድ ዘግበውታል)
ከሙእሚኖች መሃከልም የተሻለው ማነው ተብለው ሲጠየቁ ጠበራኒ በዘገቡት ሀዲስ
« በባህሪው በላጫቸው የሆነ » ብለዋል። (ጦበራኒ ዘግበውታል)
የአንድ ሰው ትክክለኛ ማንነቱ የሚገልፀው ከቤተሰቦቹ ጋር ሲሆን በሚያሳየው ባህሪ ነውና።
የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ከዓኢሻ ረዲየላሁ አንሃ በተወራው ሀዲስ ለቤተሰብ በመልካም መኗኗር ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆን ሲገልፁም
« ከናንተ መሃል መልካም ነው የሚባለው ለቤተሰቦቹ መልካም የሆነ ነው። እኔ ለቤተሰቤ መልካም በመሆን ከናንተ በላጩ ነኝ። » ብለዋል። (ቲርሚዚይ ዘግበውታል)
እርግጥ መልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከማንም የበለጡ ወደር የሌላቸው ባለ መልካም ባህሪ ለመሆናቸው
” وَإِنَّكَ
لَعَلَىٰ خُلُقٍ عَظِيمٍ .“
القلم:4
﴾ አንተም በታላቅ ጠባይ ላይ ነህ፡፡} አልቀለም:4 በማለት አላህም መስክሮላቸዋል።
ስለሆነም እቤትም ከቤት ውጭም መልካም ባህሪን መላበስ የሚጠበቅብን ነው። ነገር ግን አንዳንዶች ከቤተሰብ ጋር ሲሆኑ ሌላ ለውጭ ሰው ደግሞ ወለላ እየሆኑ አስቸግረዋልም ተቸግረዋልም። እንደ እስስት እንደ ቦታው እየተቀያየሩ መታየትም ሁሌ ጥሩነት አይኖረውም። በተለይ በምናስተዳድራቸው ቤተሰቦች ላይ የመጨረሻውን ምርጥ ባህሪህን አጉልተን ማንፀባረቅ አለብን።
ሰዎች ከኛ ጋር ሲኖሩ ኑሮ አስገድዷቸውና አማራጭ አጥተው መሆን የለበትም። በየትኛውም ደረጃ ላይ ብንሆን የሚያቀራርብ ባህሪ፣ የሚማርክና የሚናፈቅ ቀለል ያለ ፀባይ ሊኖረን ይገባል።
እርግጥ እንዳጠቃላይ የመልካም ባህሪ ትሩፋት ይህ ነው ተብሎ የሚገመት አይደለም። ኢስላም ከመጣባቸው ዋና ዋና አላማዎች አንዱም ከፈጣሪና ከፍጡራን ጋር ያለንን የመኗኗር ፀባይ ስለማሳመር ነው። ወላጆች እንኳ ልጃቸውን ሊሰጡና ሊያጋቧት እንደ መስፈርት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም የመከሩት ዲኑና ባህሪው ተወዳጅ ለሆነ ሰው አጋቡ ነው ያሉት።
عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ قَالَ: قَالَ رَسُولُ
اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ: ( إِذَا خَطَبَ إِلَيْكُمْ مَنْ
تَرْضَوْنَ دِينَهُ وَخُلُقَهُ فَزَوِّجُوهُ، إِلَّا تَفْعَلُوا تَكُنْ فِتْنَةٌ
فِي الأَرْضِ ، وَفَسَادٌ عَرِيضٌ ) وحسنه الألباني في "صحيح الترمذي" .
ስለዚህ « ዲኑን እና ባህሪውን የምትወዱለት ሰው ልታጋቡት ከጠየቃችሁ አጋቡት። … »
የሚለው የመልእክተኛው ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ሃዲስ ስለምን እያወራና ለምንስ እንዳስፈለገ ልብ ብለን እናስተውል።
በተለይ ወንዶች ትናንት ራሳችንን አሰማምረንና ጣፋጭ ፀባይ አሳይተን የጠየቅነውን ሚስት ካገባናት በኋላ ምንና ምን ከወደኋላ ነው እንዲሉ ጊዜው ገፋ ሲል ጊንጥ የምንሆን ከሆነ በጣም ያሳዝናል። ይበልጥ ደግሞ የሚያሳፍረው ከቤት ወጣ ሲባል ለሌሎች የምናሳየው አጓጊ ባህሪ ወደቤት ካልመጣ አስመሳይ ያሰኛል ። በዚህ አጋጣሚ አዩሀል ወንድ ❗ ለምንስ እየተታለልክ መኖር እንደመረጥክ ግልፅ ካልሆነልህ ከዲንህ መመርያ መራቅህና የአላህን በሁሉም ቦታና ሁኔታ ተቆጣጣሪ መሆኑን መዘንጋትህ እንደሆነ ልታውቅ ይገባሃል።
ይኽ እንደ ቀላል ቤተሰቦችህን ነፍገህ ወደ ውጭ ብቻ የምትልከው መልካም ባህሪ ለምንም ስኬት እንደማያደርስህ በደንብ ልትረዳው ይጠበቅብሃል። ምክንያቱም ቤታችንን፣ ቤተሰቦቻችንን ነፍገን ከውጭ ጥሩ መስለን ለመታየት መሞከር ውድቀት ነው። ጥሩውን ወደ ውጭ ልከን የምናመጣው መልካም ነገር የለምና።
ቤተሰቦቻችንን ችላ ብለን ለውጭ ሰው ደጓሚ፣ ጋባዥ፣ በጉዳያቸው ተፍጨርጫሪ፣ በጎ አድራጊና አማካሪያቸው ብንሆን የሰዉን አድናቆት የምንሻ አስመሳይ መሆናችንን እንጂ ባለ መልካም ባህሪ ሰው መሆናችንን አያሳይም።
እርግጥ ኢማሙ ሙስሊም በዘገቡት ሀዲስ ነቢዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም
« በጎ ማለት መልካም ባህሪ ነው።» ብለዋል።
ይሁንና የተጠቀምንበት መንገድና ቦታ ክብራችንን እንድንነጠቅ ሊያደርግን ስለሚችል ቤታችንና ቤተሰባችንን አንዘንጋ። ቅድሚያ ለነሱ❗
ሸውካኒ ረሂመሁላህ ለቤተሰቦቹ በተለይም ለሚስቱና ለልጆቹ አስፈሪና የማይመች እንዲሁም ንፉግ ስለሆነ ሰው በሚቀጥለው መልኩ ጠቁመውናል።
☞
« አንዳንዱ ሰው ከቤተሰቡ ጋር ሲሆን ክፉ ባህሪን ተላብሶ ፣ ሀይለኝነት የተጠናወተውና መልካምነት የሌለው ሆኖ ታየዋለህ። ከሌሎች ባዕዳን ሰዎች ጋር ሲገናኝ ደግሞ ቀለል ያለ፣ ፀባዩም ምቹ የሆነ፣ ፈቃደኛና ተግባቢ እንዲሁም በርካታ ኸይር ሰሪ ሆኖ ታገኘዋለህ ። ይሁንና የዚህ አይነት ባህሪ ያለው ሰው ያለ ምንም ጥርጥር ሀቅን መግጠም የተነፈገ ነው። ከቅኑ መንገድም የጠመመ ነው። » ነይሉል አውጣር : 2/246
ውድ ወገኖቼ ከዚህ መልእክት የየድርሻችሁን እንደምትወስዱ ተስፋ አደርጋለሁ።
ከእንዲህ አይነቱ የፀባይ መቀያየር ክስረትም ሰላም እንዲያደርገን አላህን እማፀነዋለሁ❗
No comments:
Post a Comment