Wednesday, 27 January 2016

PART 2 እናታችን ዓኢሻ

አስቢ! ያገባችው እኮ ወደ ሰባት ሰማያት ያረገ ነቢይ ነው፤ እሷኮ ከቁረይሽ ያውም ከነቢያት ቀጥሎ በኢማኑ ተስተካካይ ከሌለው አቡበክር የተገኘች ነች፤ ግን ኢማን እንዲህ ነው!
ዛሬ የወደፊት የትዳር አጋራቸውን አሊያም በቅርብ የምታገባ ዘመድ ጓደኛቸውን ባል በተለያዩ ወጪዎች ቁም-ስቅል የሚያሳጡ ሰዎች እዚህ ጋር በእናታችን ዓኢሻ ታሪክ ሊመከሩ ይገባል።
መኸር በአስር ሺህ ቤቶች ይቆጠር የሚሉ፣ ጥሎሽ ለሙሽሪት ሳያንስ ቤተዘመድ ካልለበሰ በቃኝ የማያውቁ፣ ወርቅ በየአይነቱ የሚያማርጡ፣ ባለብዙ ክፍል ቤት የሚያማትሩ፤ ሞዝቮልድ አልጋ ካልተዘረጋ፣ ቁምሳጥን ካልተገዛ፣ ፍሪጅ ካልተገተረ ፣ አረቢያን መጅሊስ ካልተደረደረ ትዳር መስሎ የማይታያቸው ቆም ሊሉ ይገባል፤ የትዳር ደስታ በገንዘብ አሊያም በቁሳቁስ ብዛት የሚገኝ አይደለም በኢማን እንጂ!
ዲን ካለ ግን ሁሉም ነገር አለ። ለዚህም ነበር እነ ዓኢሻ ህይወታቸው በፍቅር የተሞላ የነበረው። ኢማን ሞልቶ የተትረፈረፈበት ነበርና።
ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ስለሷ አንስተው አይጠግቡም "ከሴቶች ሁሉ የምወደው ዓኢሻን ነው" እስኪሉ ድረስ ፤  ዓኢሻ ጠጥታ ያስቀመጠችው ኩባያ ዳግም የነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) መጠጫ ነበር። የሷ ከንፈር ያረፈበትን ፈልገው ይጠጡበት ነበር፤ ያ-ረብ!
እህቴ ይህን የመሰለ ፍቅር ማግኘት አትሺም? ወዶሽ እንስፍስፍ እንግብግብ የሚልልሽ የትዳር አጋር አትመኚም?
አታስቢ! ብቻ አንቺ ዲንሽን አጥብቀሽ ያዢ፤ ከዛ እየከነፈ ይመጣል። የት ያመልጣል?! አንቺ ለአላህ ብለሽ ዲነኛ ሁኚ! በቃ!
ግንኮ እናትሽ እንዲህ በፍቅር ስትኖር ችግሮችም አልተለያትም ነበር። ፈተናዎች ተፈራርቀውባታል ግን ፅኑ ነበረች፤ አላማዋ ጀነት እንጂ ዱኒያ አልነበረምና አልተበገረችም።
በቤቷ የሚበስል ምግብ  ባለመኖሩ ለወራት እሳት ሳይነድ ያልፍ ነበር። የገብስ ቂጣ እንጂ የሚላስ የሚቀመስ እስኪጠፋም ይቸገሩ ነበር። አንዳንዴማ ባስ ሲል ተምር እና ውሀ ብቻ እየተጠቀሙ ያሳልፋሉ።
ዓኢሻ እንደዛሬው በሰፊ ቤት በቅምጥል ህይወት አልኖረችም። ጀነትን እያለመች ከውድ ባለቤቷ ጋር በችግር አሳለፈች እንጂ ... ቢሆንም ይህ ችግሯ ደስታዋን አልቀነሰባትም። ኧረ እንደውም ፍቅር ጨመረ እንጂ!
ዛሬ ስንቶች በቪላ ቤቶች፣ በተሟላ የቤት እቃ በተትረፈረፈ ሀብት ተከበው ደስታ ማግኘት ሲሳናቸው፣ በበሽታ ሲወረሩ፣ በጭንቀት ሲወጠሩ፤ ጭራሽ ተፈጥሮአዊውን እንቅልፍ እንኳ ሲያጡ እያየን፤
ከነሱ ሊነፃፀሩ የማይችሉ የእለት ጉርስ እንኳ የሌላቸው ምስኪኖች፤ ነገር ግን የኢማን ሀብት የሞላቸው ቆሎ ቆርጥመው በውሀ አወራርደው በፍቅር ሲዋኙ እናያለን!
ይህ ነው የኢማን ፍሬው። የዓኢሻ ደስታ ምስጢሩ!
ዓኢሻ ትናገራለች "ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ለይል እየሰገዱ እኔ ከፊታቸው እተኛ ነበር፤ ሱጁድ ለማድረግ ሲወርዱ እግሬን ቆንጠጥ ያደርጉኝና እሰበስበዋለሁ፤ ሲነሱ ደግሞ እዘረጋዋለሁ" ትላለች።
ዓኢሻ "የዛኔ በቤታችን መብራት አልነበረም" አለች። ምነው ስትባል "ለመብራት የሚሆነን ጮማ ቢኖረንማ በበላነው ነበር!" ሱብሀን አላህ!
ዛሬ አንቺ በኢማን የታነፀ ባል መጥቶልሽ ወይም አግብተሽ በእንዲህ ያለ ቤት ላኑርሽ ቢል ትቀበይው ይሆን? ወይስ ዞርበል ትይዋለሽ? እናትሽ ግን እንዲህ አልነበረችም!
ዓኢሻ ምንም ቢቸግራት፣ ምን ያህል ብትጎሳቆል ከውድ ባለቤቷ ተለይታ ዱኒያን ማጣጣም አልተመኘችም። በፍፁም!
አንዴ አላህ በወህይ ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ባለቤቶቻቸውን ወይ ከሳቸው ጋር ቀጥለው አኸይራን አሊያም መለየትን እንዲያስመርጡዋቸው አዘዛቸው። ይህንኑ ይዘው ወደ ዓኢሻ መጡ... እንዲህ ትተርካለች
"ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉኝ 'እኔ አንድ ነገር አወሳሻለሁ ወላጆችሽን ሳታማክሪ ለውሳኔ እንዳትቸኩይ' አሉኝ፤ መቼም ወላጆቼ እሳቸውን እንድለይ እንደማይመክሩኝ ያውቃሉ። ከዚያም እንዲህ አሉኝ 'አላህ እንዲህ ብሏል ...
((አንተ ነብይ ሆይ! ለሚስቶችህ ፤ 'የዱንያን ህይወትና ጌጦቿን የምትፈልጉ እንደሆናችሁ መልካም መልቀቅን(ፍቺን) እለቃችኋለሁ' በላቸው)) ብሏል አሉኝ፤ 
እኔም ታዲያ በምኑ ነው ወላጆቼን የማማክረው እኔ እንደሆንኩ አላህን፣ መልእክተኛውንና የአኸይራን አገር እፈልጋለሁ አልኳቸው" ሱብሀን አላህ! እናትሽ እንዲህ ነበረች።
ሌላው ዓኢሻን የገጠማትን ላውሳልሽ ...
እስኪ እራስሽን በዓኢሻ ቦታ አድርጊውና ተከትዪኝ፤ እንዲህ ባልሽን በፍቅሩ ተማርከሽ እየወደድሽ፣ ምንም ቢቸግርሽ ለዲኑ ስትዪ በሱ ጥላ ስር መሆንን መርጠሽ፤ እሱ በያዘው ተልእኮ ላይ ስኬታማ እንዲሆን እያበረታሽው፤ የሚጠበቅብሽን ሁሉ እያደረግሽ፣ በታማኝነት እየጠበቅሽው ...
ድንገት! በቃ ድንገት ... የሆኑ ሰዎች ... በአንቺ ንፁህነት ላይ ጥላሸት የሚቀባን ወሬ ቢነዙ፣ እጅግ ፀያፍ በሆነ ነውር ቢያሙሽ፣ ቀስ በቀስ ወሬው ቢሰራጭ፣ በከተማው ሁሉ ስምሽ ቢጠፋ፣ ሳር ቅጠሉ እርግጠኛ ሆኖ ቢወነጅልሽ፤ የምትወጂው ባልሽ የምታምኛቸው ወላጆችሽ የሚሆኑት ጠፍቷቸው በጭንቀት ቢዋጡ ...ምን ትሆኚ?
ባላደረግሽው፣ ባልቀረብሽው ጭራሽ ባላሰብሽው ዚና ብትጠረጠሪ ... ምን ይውጥሻል?
ከበደሽ?!
እናትሽ ግን ይህ ገጥሟት ነበር። አጥንቷን የሚሰብር፣ ማንነቷን የሚከ ሰክስ፣ ሞራሏን የሚያደቅ አስቸጋሪ ወቅት ...

ሙናፊቆች እጅግ ተደስተዋል ፤ በዓኢሻ ክብር በመረማመድ ጮቤ እየረገጡ ነው። እየፈለሰፉ ይቀባጥራሉ፤ እየጨማመሩ ይንደቀደቃሉ፤ እየተሳለቁ ይንቦለቦላሉ ... ወሬያቸውን አሜን ብሎ የሚቀበል ተገኝቷል የነርሱን ቱልቱላ የሚነፋ ሞልቷል። ብቻ ለመናፍቃን አለም ዘጠኝ ሆነች!
ወር ያህል መዲና በወሬ ታመሰች፤ የምእመናን ቤት በአሉባልታ ተንጧል! ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ግራ ግብት ብሏቸዋል...

No comments:

Post a Comment