በነቢዩ ሙሳ (ዐለይሂሰላም) ዘመን የነበረው የፊርዐውን ባለቤት የነበረቿ ኣሲያ💐በታሪኽ ዘጋቢያን እንደተጠቀሰው ሙሉ ስሟ ኣሲያ ቢንት መዛሂም ትባላለች። የኣሲያ ታሪኽ ጎልቶ የሚጀምረው ነቢዩላሂ ሙሳን እናታቸው በሳጥን አድርጋ ከጣለቻቸው ወንዝ ላይ አግኝታ ወደ ቤቷ ከወሰደችበት እለት ጀምሮ ነው።
በወቅቱ ያ ዕርጉም ፊርዐውን ሸይጣንን የሚታዘዝና ፈጣሪም ጌታም አምላካችሁም እኔው ነኝ በማለት በዘመኑ ህዝቦች ላይ በደነገገው መሰረት አንዳንድ አመት እየታለፈ አዲስ የሚወለዱ ወንድ ልጆችን ይገድል ያስገድል ነበር።
ነቢዩ ሙሳም አለይሂ ሰላም የተወለዱት ወንድ ልጅ እንደተወለደ በሚገደልበት አመት ነውና እናታቸው የማሳደግ አማራጭ ስለሌላት በአይኗ እያየች ሲገደል ከማየትና አላህ በልቧ ውስጥ እንዲያድር ባደረገው ግፊት መሰረት በአላህ በመመካት በተቆለፈ ሳጥን አድርጋው በወንዙ ላይ ተንሳፍፎ እንዲሄድ አደረገችው።
ይህንን የታሸገ ሳጥን የፊርዐውን ሚስት ኣሲያ አገኘችው። ድንቅ ጉብልም ከውስጡ መኖሩን ስታይ በሁኔታው ብትገረምም የፊርዐውንን ገዳይነት በማሰብ
” وَقَالَتِ امْرَأَتُ فِرْعَوْنَ قُرَّتُ عَيْنٍ لِّي وَلَكَ ۖ لَا تَقْتُلُوهُ عَسَىٰ أَن يَنفَعَنَا أَوْ نَتَّخِذَهُ وَلَدًا وَهُمْ لَا يَشْعُرُونَ .“
القصص:٩
{{ የፈርዖንም ሚስት «ለእኔ የዓይኔ መርጊያ ነው፡፡ ለአንተም፡፡ አትግደሉት፡፡ ሊጠቅመን ወይም ልጅ አድርገን ልንይዘው ይከጀላልና» አለች፡፡ እነርሱም (ፍጻሜውን) የማያውቁ ሆነው (አነሱት)፡፡}}
አልቀሰስ: 9
ኣሲያ ረሂመሃላህ ያንን የግፈኞች ግፈኛ ጨካኝ ጠማማ ገዳይ ለማሸነፍና ያገኘችውን ሲሳይ ላለማጣት እንዲህ ኣለችው☞
« ለእኔ የዓይኔ መርጊያ ነው፡፡ ለአንተም፡፡ (ስለዚህ) አትግደሉት፡፡ » አለች።
ይሁንና ፊርዐውን የሚበገር ባለመሆኑ ገፋገፋ ሲያደርገው እንደሴትነቷ በብልሃቷ እንድታሸንፈው አላህ አስቻላት።
« ሊጠቅመን ወይም ልጅ አድርገን ልንይዘው ይከጀላልና » በማለት አግባባችው፡፡
በዚህም ሰበብ ነቢዩ ሙሳ ከፊርዐውን ግፍ እንዲተርፉ አላህ ሰበብ ሊያደርጋት መረጣት። የትዕቢተኛው ፊርዐውን ባለቤት እንደመሆኗም በዚያው ቤተመንግስት ውስጥ ነቢዩ ሙሳን ለማሳደግ ቻለች።
ይሁንና " የፈሩት ይደርሳል የናቁት ይወርሳል።" ነውና ተረቱ ጥበበኛውና ሁሉን አዋቂ የሆነው አሸናፊው አላህ አዝዘ ወጀልለ እንዳለው
« እነርሱም (ፍጻሜውን) የማያውቁ ሆነው (አነሱት)፡፡»
ለሷ በረከት የሆነው ሰበብ ለፊርዐውን ደግሞ ክስረት ሆነለት። ኣሲያ በዚህ ግፈኛ ቤት ሆናም ቢሆን ልቧ ያለው ጌታዋ አላህ ዘንድ ነው። ፊርዐውን የሚያራምደውን ፈጣሪን የመካድና ራሱን ጌታ የማድረግ ፉከራም ሆነ በህብረተሰቡ ላይ የሚያደርሰውን ግፍ አልደገፈችም።
በቤተመንግስቱ ውስጥና በዙርያዋ የነበረው ድሎት፣ ምቾትና የተንደላቀቀ ኑሮ ትዝም ሳይላት ለእውነተኛው ፈጣሪ ጌታዋ ለአላህ ፍቅሯን በመስጠት የሱን አምላክነት በመቀበል እምነቷን በመደበቅ ትኖር ነበር።
ይህች የእንስቶቻችን ድንቅ ተምሳሌት የሆነች እንስት በአላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ቃል በቁርኣን ከተጠቀሱት ጥቂት ዓርአያ ሴቶች ስመ-ጥሯ ለመሆንም በቅታለች።
የአላህ መልዕክተኛ የአላህ መልክተኛ(ﷺ) አንድ ግዜ መሬት ላይ አራት መስመሮችን አሰመሩና ፤ ይህች ምን እንደሆነች ታውቃላችሁን ? ሲሉን
አላህና መልዕክተኛው ይበልጥ ያውቃሉ ኣሉ።
የአላህ መልክተኛም (ﷺ) እንዲህ ኣሉ☞
عن ابن عباس قال: خط رسول الله صلى الله عليه وسلم في الأرض أربعة خطوط وقال: " أتدرون ما هذا؟ " قالوا: الله ورسوله أعلم. فقال رسول الله صلى الله عليه وسلم: " أفضـل نساء أهل الجنة:
خديجة بنت خويلد وفاطمة بنت محمد ومريم ابنة عمران وآسية بنت مزاحم امرأة فرعون "
" ከጀነት ሰዎች መካከል ምርጦቹ ሴቶች: -
ኸዲጃ ቢንት ኹወይሊድ
ፋጢማ ቢንት ሙሀመድ
መርየም ቢንት ዒምራንና
ኣሲያ ቢንት ሙዛሀም ናቸው። » ብለዋል።
የአዕምሮዋን ምጥቀትና ብቃትም ሲያስረዱ
وقد ثبت في الصحيحين من حديث شعبة عن عمرو بن مرة عن مرة الهمداني عن أبي موسى الأشعري
«عن النبي صلى الله عليه وسلم قال: " كمل من الرجال كثير ولم يكمل من النساء إلا آسية امرأة فرعون ومريم ابنة عمران وخديجة بنت خويلد وإن فضل عائشة على النساء كفضل الثريد على سائر الطعام ".
« ከወንዶች መካከል የተሟላ ስብዕና ያላቸው ብዙዎች ናቸው። ከሴቶች ግን የፊርዐውን ሚስት ከኣሲያ፣ ከመርየም ቢንት ዒምራንና ከኸዲጃ ቢንት ኹወይሊድ በስተቀር ምሉእ የሆኑ የሉም። ከሴቶች መሃል የዓኢሻ በላጭነት ከተነሳማ ከምግቦች መሃል ፍትፍት በምግቦች ላይ የሚኖረው በላጭነት አይነት ነው።» ብለዋል።
ኣሲያ ኢማኗን ደብቃ ብትኖርም በቤቷ ውስጥም ሆነ በሀገሪቱ በሙእሚኖች ላይ የሚፈፀመው ግፍ ውስጧን አንገፈገፋት።
ፈጣሪ አምላኩን መካዱ ሳያንሰው፣ እኔው ነኝ ጌታ እያለ የሚፎክረውና ህዝቡን በማታለልም በማስገደድም ወደ ክህደት የሚነዳቸው ነገር አንገሸገሻት።
የሴት ልጁን ፀጉር የምታበጥርን አገልጋይዋን እንኳ ማለፍ ባለመቻሉ ለልጁ ጌታዬ የኔም የአባትሽም ጌታ የሆነው አላህ ነው በማለቷ በዚህም አማኝ በመሆኗ ሰበብ በሚዘገንን ሁኔታ ከነልጆቿ አሰቃቂ በደሉን እንደ ፈፀመባቸውም አስተዋለች።
ይህ ሁሉ በደል የሚፈፀመው በባሏ ሲሆን የሚፈፀምባቸው ደግሞ በንፁሃን ላይ ነውና የጌታዋን የአላህን እርዳታ ናፈቀች።
ስለነዚህ ተበዳዮች በተለይ ስለ ፀጉር አበጣሪዋና ልጆቿ የአላህ መልክተኛም (ﷺ) በሚዕራጅ ምሽት (ወደ ሰማይ ባረጉበት ምሽት) አላህ በሰማይ ላይ ያሳያቸውን ሲያስረዱንም ቀጣዩን ብለዋል።
عَنِ ابْنِ عَبَّاسٍ رضي الله عنهما قَالَ :قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ : ( لَمَّا كَانَتْ اللَّيْلَةُ الَّتِي أُسْرِيَ بِي فِيهَا ، أَتَتْ عَلَيَّ رَائِحَةٌ طَيِّبَةٌ ، فَقُلْتُ : يَا جِبْرِيلُ ، مَا هَذِهِ الرَّائِحَةُ الطَّيِّبَةُ ؟ فَقَالَ : هَذِهِ رَائِحَةُ مَاشِطَةِ ابْنَةِ فِرْعَوْنَ وَأَوْلادِهَا ، قَالَ : قُلْتُ : وَمَا شَأْنُهَا ؟ …… » الحديث
« ወደ ቤተመቅደስና ከዚያም ወደ ሰማያት በምወሰድበት ምሽት ቆንጆ የሆነ ሽታ መጣብኝ። ጅብሪል ሆይ! ይህች ቆንጆ ሽታ ምንድናት ? አልኩት። ይህች የፊርዐውን ሴት ልጅ አበጣሪ የነበረችውና ልጆቿ ናቸው። ተባልኩኝ:: ምን ነበር ጉዳይዋ ኣልኩኝ… … » ታሪኩ ረጅም ነውኢማሙ አህመድ፣ ጠበራኒ፣ ኢብኑ ሂባንና ሃኪም ዘግበውታል።
አሲያ በባሏ እየተፈፀመ ያለውን በደል መቋቋም ስላልቻለችም መቃወም ጀመረች። በአምላኩ ላይ ማመፁንም ይፋ አድርጋ ወቀሰችው። ይሁንና ለማንም ርህራሄ የሌለው ፊርዐውን በሷም ላይ የማሰቃያ በትሩን ዘረጋ። በእምነቷ እንደለናችም የደረሰባትን ግርፋትና ሌሎች ቅጣቶችን ተሸከመች።
ለሌሎች አምላካችሁ ነኝ እያለ ሲፈትናቸው እንደከረመ ሁሉ ለሷም ምርጫ ሰጣት። ወይ ጌታ የምትዪውን ክደሽ እመኚብኝ ወይ ደግሞ ቅጣቴን ትቀምሻታለሽ በሚል በደሉን ቀጠለ።
በተውሂድ ላይ መፅናትን በመምረጧም አንጀቱ ቆስሎ በአሽከሮቹ አስጠፈራትና የስቃይ ጅራፉን አዘነበባት። ብትቆስልም ብትደማም፣ ህመሙ ብሶባት ለሞት ብትቃረብም ከፅናቷ ፍንክች ሳትል የአላህን እርዳታ ከጀለች፣ ከሱ ነፃ መውጣትንና ከዱንያ ፀጋ ይልቅ ታላቁን የኣኺራ ፀጋ እንዲያወርሳት ጠየቀችውም። እሱም ወሊዮቹን ረጂ የሆነ ጌታ ነውና ዱዓእዋን ተቀበላት። የበላይም አደረጋት።
” وَضَرَبَ اللَّهُ مَثَلًا لِّلَّذِينَ آمَنُوا امْرَأَتَ فِرْعَوْنَ إِذْ قَالَتْ رَبِّ ابْنِ لِي عِندَكَ بَيْتًا فِي الْجَنَّةِ وَنَجِّنِي مِن فِرْعَوْنَ وَعَمَلِهِ وَنَجِّنِي مِنَ الْقَوْمِ الظَّالِمِينَ.
التحريم: 66
«ለእነዚያ ለአመኑትም የፈርኦንን ሚስት፤ አላህ ምሳሌ አደረገ፡፡ «ጌታዬ ሆይ! አንተ ዘንድ በገነት ውስጥ ለእኔ ቤትን ገንባልኝ፡፡ ከፈርዖንና ከሥራውም አድነኝ፡፡ ከበደለኞች ሕዝቦችም አድነኝ» ባለች ጊዜ፡፡» አት-ተህሪም 11
ይህንን አያህ ኢብኑ ከሲር ሲተነትኑ ስለ ኣሲያ ቀጣዩን ብለዋል።
“አላህ (ሱብሃነሁ ወተአላ) ጀነት ውስጥ ያለው ቤቷን አሳያት። እሷም ፈገግ አለች። ከዚያም ሞተች::” ብለዋል። አላህ ይዘንላት።
ውዷ እህቴ ከዓርአያሽ ከታላቂቷ ኣሲያ ቢንት ሙዛሀም በምትቀስሚው ትምህርት ራስሽን አጠንክሪ። የሚመጡብሽን ፈተናዎችም በንቃትና በፅናት ለማለፍ በእውቀት ላይ ትጊ። የትም ብትሆኚ ዲንሽን ከማወቅ የሚያቅብሽ የለምና ተጣጣሪ። ኣሲያ ስለ ጌታዋና ስለ ዲኗ ያወቀችው ሁሉ ለዚህ ፅናት አብቅቷቷልና አንቺም ንቂ❗
አላህ ሁላችንንም በሀቅ ላይ ያፅናን!!
No comments:
Post a Comment