Wednesday, 27 January 2016

PART 3 እናታችን ዓኢሻ

ውሸት መሆኑ አልጠፋቸውም ግን ኸልቁ ሁሉ እያወጋው ነው፤ ወሬው ሲጠና 'ፍታት' ብሎ የሚመክርም ነበር፣ 'የለም እንታገስ' የሚልም አለ።
ዓኢሻ አይኖቿ እንባ ማዝራት እንጂ ሌላ አያውቁም። ስታለቅስ ትውላለች እንዲሁ ታነጋለች። ጭንቅ ሆነ!
የሚገርምሽ ግን እናትሽ ይሄኔ አልተማረረችም፣ በጌታዋም አልተበሳጨችም ፤ በእድሏም አልተቆጨችም! ብቻ ሀቁን እንዲየወጣው ጌታዋን ለመነችው። እሱም ተቀበላት!
አላህ እውነቱን ገለፀ፤ የዓኢሻ ንፅህና አወጀ። አሉባልታ ያናፈሱትን አሳፈረ፣ በቅጣትም ዛተባቸው።
ምእመናን ፈነደቁ! ዓኢሻ ትላለች "አላህ ለኔ የቁርአን አንቀፅ ያወርዳል ብዬ አላሰብኩም ነበር"
ግን አላህ አደረገው፤ ስለሷ ንፅህና ለመግለፅ የሀሜተኞቹንም  ውሸት ለማጋለጥ አስር ተከታታይ አንቀፆችን አዥጎደጎደ። አልሀምዱሊላህ!
إِنَّ الَّذِينَ جَاءُوا بِالْإِفْكِ عُصْبَةٌ مِّنكُمْ ۚ لَا تَحْسَبُوهُ شَرًّا لَّكُم ۖ بَلْ هُوَ خَيْرٌ لَّكُمْ ۚ لِكُلِّ امْرِئٍ مِّنْهُم مَّا اكْتَسَبَ مِنَ الْإِثْمِ ۚ وَالَّذِي تَوَلَّىٰ كِبْرَهُ مِنْهُمْ لَهُ عَذَابٌ عَظِيمٌ [٢٤:١١] "
እነዚያ መጥፎን ውሸት (ዓኢሻን በማነወር) ያመጡ፣ ከናንተው የሆኑ ጭፍሮች ናቸው፤ ለናንተ ክፉ ነገር ነው ብላችሁ አታስቡት፤ በውነቱ እርሱ ለናንተ መልካም ነገር ነው፤ ከነርሱ (ከጭፍሮቹ) ለያንዳንዱ ሰው፣ ከኀጢአት የሰራው ሥራ ዋጋ አለው፤ ያም ከነሱ ትልቁን ኀጢአት የተሸከመው (ወሬውን ያጋነነው) ለርሱ ከባድ ቅጣት አለው" 24፥11
 ከላይ ያነበብነው አንዱን አንቀፅ ብቻ ነው፤ ለትምህርት እንዲሆነን ከወረዱት አስር አናቅፅት መሀል አንዱን ልድገም ...
"እነዚያ በነዚያ ባመኑት ሰዎች ውስጥ መጥፎ ወሬ እንድትሰፋፋ የሚወዱ ለነሱ በቅርቢቱም በመጨረሻይቱም ዓለም አሳማሚ ቅጣት አላቸው፤ አላህም ያውቃል፤ እናንተ ግን አታውቁም" 24፥19
ቀሪውን ከሱረቱ ኑር አንቀፅ ፥12 ጀምረሽ ኮምኩሚ ...
ዓኢሻ ከሰማየ ሰማያት በወረደው የአላህ ቃል ነፃ ወጣች፤ እነዛ ነውርን ለማሰራጨት ይጣደፉ የነበሩ መናፍቃንም አፈሩ፣ በነርሱ ሀሰተኛ አሉባልታ የተሸነገሉ ጥቂት አማኞችም ታረሙ፤ የእውነተኛው አቡበክር ልጅ እውነተኛነቷ ተረጋገጠ።

 ሲዲቃህ ቢንት ሲዲቅ!
ዓኢሻ ከባለቤቷ ጋር በፍቅር ቀጥላለች። ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) በመልካም ይኗኗሯት፣ ያጫውቱ ያዝናኗትም ነበር፤ እሷን ለማስደሰት ሩጫም ይሽቀዳደሟት ጭምር ነበር፤ መጀመሪያ ትላለች ዓኢሻ እቀድማቸው ነበር ኋላ ላይ ስወፍር ግን ይቀድሙኝ ጀመር :)
በስተመጨረሻ ዓኢሻ ከነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ጋር የመሰናበቻውን ሐጅ አድርጋ ነበር። በመንገዳቸው ላይ የገጠማቸውን ስትናገር ...
"ከነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ጋር ሙህሪሞች(የሐጅ ስርአት ላይ) ሳለን ጋላቢዎች በኛ በኩል ያልፉ ነበር፣ (ተጓዦቹ) ወደ እኛ ሲቀርቡ አንደኛችን ጅልባቧን በፊቷ ላይ ትለቃለች ሲያልፉን ደግሞ እንገለጣለን" ትላለች ዓኢሻ።
እንዴት ነው እህቴ አንቺስ ሂጃብ አጠቃቀምሽ እንደ እናትሽ ነው? ፊትሽን ትሸፍኛለሽ? ነው ወይስ ጅልባቡም አልገራልሽም? ... አትዘናጊያ ሲስቱካ ከዚህ በኋላ ምን ትጠብቂያለሽ ...
ሞት እንደሆነ ነጋሪት እየጎሰመ፣ መለከት እየነፋ፣ አዋጅ እያስለፈፈ አይመጣ፤ ድንገት ነው ከተፍ የሚል ... ታዲያ ምን አዘጋጅተሻል? አስቢበት!
ጊዜ ጊዜን ሲወልድ ነቢዩም (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ለሞታቸው ሰበብ የሆነው ህመም ሲይዛቸው ሚስቶቻቸውን አስፈቅደው ዓኢሻ ቤት ተኙ፤ በዓኢሻ ጉያ ውስጥም ሁነው የማይቀረውን የሞት ፅዋ ተጎነጩ። (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም)

ዓኢሻ ከነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ህልፈት በኋላ የአኸይራ አገሯን ፍለጋ በዒባዳ መማሰኗን ቀጠለች። ለይል በመቆም፣ ቀን በመፆም፣ ባሪያ ነፃ በማውጣት፣ ሚስኪኖችን በመርዳት፣ በመልካም በማዘዝ ከመጥፎ በመከልከል፣ የነቢዩን (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ሐዲስ በማስተማር ተሰማራች።

ዓኢሻ እያንዳንዱን የነቢዩን (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንቅስቃሴ በመከታተል ለኛ ካስተላለፉልን ባለውለታዎች ቀንደኛዋ ናት። በተለይ ደግሞ ሌሎች ሶሀቦች ሊታደሙበት በማይችሉት የቤት ውስጥ ተግባራቶቻቸው ሁነኛ የሐዲስ ምንጭ ነበረች።
ከ1500 በላይ ሐዲሶችን በማስተላለፍ ለነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ሱና መተላለፍ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክታለች። ከነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ማለፍ ጀምሮ እስከ ህልፈቷም ድረስ ግር በሚያሰኙ ሸሪዓዊ ጉዳዮች ላይ ብያኔ(ፈትዋ) ትሰጥ ነበር።
አንቺስ እንደሷ መሆን አትሺም? ታዲያ ምን ትጠብቂያለሽ!? ዲንሽን የምትማሪባቸው መንገዶች እጅግ በዝተዋል፤ ቂርአት፣ ሙሐደራዎች፣ ፅሁፎች፣ መፃህፍት፣ በተለያዩ ዘዴዎች ቀርበዋል፤ ተጠቀሚበት!
ጊዜ ሳይሄድ ወቅት ሳያልፍሽ ልክ እንደናትሽ አሪፍ ሁኚ፣ በዘመን አመጣሽ ፋሽኖች ጊዜሽን አትፍጂ እንደፋራ ራስሽን የምእራባውያንና የአመፀኞች ዲዛይን መሞከሪያ አትሁኚ፤ ብልጥ ቆፍጣናና የዲኑ ሙድ የገባሽ ሁኚ!
ጀግናዋ እናትሽ ዓኢሻ(ረ.ዓ) ከነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ከተለየች ከ 48 አመታት በኋላ ለውድ ባለቤቷ ያልተመለሰው ሞት ለሷም ቀረበ።
ዓለም የማይረሳውን ስራዋን ለታሪክ አሳልፋ በተወለደች በ66 አመቷ በ58ኛው አመተ ሂጅራ ረመዷን 17 ማክሰኞ ቀን ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች። ታላቁ ሶሀቢይ አቡሁረይራ ተቀድመው አሰገዱ በበቂዕ መካነ መቃብር ተቀበረች።
ረድየላሁ ዓንሀ ወአርዳሀ 
BY MUHAMMED IBRAHIM ALI

No comments:

Post a Comment