Wednesday, 27 January 2016

ስለ ሴቶች የተነገረ ኑዛዜ

ስለ ሴቶች የተነገረ ኑዛዜ💐 
الوصيـة بالنسـاء


ከሴቶች ምዕራፍ (سورة النساء) አንቀፆች መካከል አንቀፅ 19 ، 34 እና 129 ምን ይመክሩናል❓
 ወንዱ ለሴቷ እንዲያደርግ ከሚጠበቅበትን ኢስላማዊ እንክብካቤ⇘መካከል⇘   
                   
በሰብዓዊነት የመያዝን                                 
ሞራሏን የመደገፍን                                  
ድካሟን የመጋራትን                                   
እዝነትና ርህራሄን የመለገስን                            
ግድፈቷን የመታገስና የመሳሰሉትን ሳይሸራርፍ ሊቸራት እንደሚገባ ሊያስተውለው ይገባል።

  ያለዚያ ምግብ አብሳይ፣ ቤት አሟሟቂ፣ ጣጣ ተሸካሚና፣ ብሶት ማራገፊያ ተደርጋ በቸልታ መታየቷ አስጠያቂ ጉዳይ ነው።

  እነሆ እርስዎም የቤትዎንና የእናት፣ የእህት፣ ወይም የባለቤትዎን ከዚያም አልፎ በርስዎ ጥላ ስር የሚገኙትን የሴት ዘመዶች፣ ጥገኞችና የሰራተኞችን ጭምር ክብርና መብት ጠብቀው ጣጣቸውን ተጋርተው እነሱም በወሩ ዒባዳ ላይ ንቁ ሆነው እንዲያሳልፉ እድል ይስጧቸው። ምክንያቱም ስለ እንስቷ የተሰጠውን ኑዛዜ በተግባር ማዋል ሲባል በተለይ በባለቤትዎ ላይ ለስላሳ ባህሪን ማሳየት፣ ጠንከር ጨከን አለማለትን ያካትታል።
  
ስለሆነም በትዳር ዓለም ሲሆን በመካከላቸው በሚፈጠሩ ነገሮች ሰበብ በሷ ላይ ድንበር ባለማለፍ አላህን መፍራት ግድ ነው። ምክንያቱም ሴቶች በተፈጥሯቸው ተንከባካቢ ጠጋኝ የሚፈልጉና ለአደጋም በቀላሉ የሚጋፈጡ በመሆናቸው በነሱ ላይ ሃላፊነትን ያገኘ ሰው ልክ እንደ ወንዱ ሊያያት አይገባም። ብዙውን ነገሯን ቻል ማድረግ ግድ ነውና። የማስተዳደር መብቱ እንዳለው ሁሉ ብቃቱም በሷ ይመዘናል።

የመጀመርያውም ኑዛዜ ስለ ሃላፊነቱ ያሳውቀዋል

 (الرِّجَالُ قَوَّامُونَ عَلَى النِّسَاءِ بِمَا فَضَّلَ اللَّهُ بَعْضَهُمْ عَلَى بَعْضٍ ) [النساء: 34] .
[ወንዶች በሴቶች ላይ ቋሚዎች (አሳዳሪዎች) ናቸው፡፡ አላህ ከፊላቸውን በከፊሉ ላይ በማብለጡ]  አል ኒሳእ: 34
 የሪያዱ ሳሊሂን ኪታብ አዘጋጅ ኢማሙ አልነወዊ ስለ ሴቶች አያያዝ ሲገልፁ ዋነኛውን የኑዛዜ ቃል እንደጠቀሱት "የታወቀ በሆነው በመልካም ተኗኗሯቸው" የሚለውን አንቀፅ ሲያብራሩ
 ( وَعَاشِرُوهُنَّ بِالْمَعْرُوفِ )
النساء:19
መልካም ተብሎ የሚታወቀው በጥሩ ፀባይ አያያዙን አሳምሮና ችግሮቿን ተረድቶ እንዳቅሙ ጥበቃም እንክብካቤም ማድረግ ማለት ነው ብለዋል ። በመልካም መኗኗር ሲባል እንደሚታወቀው ሸሪዓ የተቀበለውንና ያፀደቀውን የአኗኗርና የአያያዝ ስልት ለማለትም ነው።
  ምክንያቱም ከዚህ ባሻገር የልብ ጉዳይ በጃችን አይደለምና የመውደድ ወይም የማፍቀር ፍላጎቱ ቢኖረን እንኳን ፍቅርን ለተለያዩ ሰዎች እኩል ማካፈልም ሆነ እንደተፈለገው ልባዊ ፍቅርን ለቀረብነው ሁሉ መለገስ አንችልምና ነው።
 ለዚህም ነው ጌታችን ከአንድ በላይ ሚስት ላለው ሰው ሲመክር
( وَلَنْ تَسْتَطِيعُوا أَنْ تَعْدِلُوا بَيْنَ النِّسَاءِ وَلَوْ حَرَصْتُم ) [النساء: 129]☞
[በሴቶችም መካከል ምንም እንኳ ብትጓጉ (በፍቅር) ለማስተካከል አትችሉም፡፡] አል ኒሳእ
ሲል የገለፀው ከኛ የሚጠበቀው ፍቅር ቢኖረንም ባይኖረንም ርህራሄና መልካም ባህሪ ሊለየን እንደማይገባ ነው።
በእጃችን ያለው መንከባከቢያም ያለ አድሎና ያለ በደል ደግፎና ታግሶ ችላ ሳንላቸውና ክብራቸውንም ሆነ መብታቸውን ሳንሸራርፍ መኗኗር ነው።💥ይህንንም በማስመልከት ከአንድ በላይ የማግባት ፀጋን ላገኙት እንደገና ሲመክር ብዙሃን የወደቁበትን ኑዛዜ ሲገልፅ እንዲህ ይላል☞
 { فَلَا تَمِيلُوا كُلَّ الْمَيْلِ فَتَذَرُوهَا كَالْمُعَلَّقَةِ ۚ وَإِن تُصْلِحُوا وَتَتَّقُوا فَإِنَّ اللَّـهَ كَانَ غَفُورًا رَّحِيمًا ﴿١٢٩﴾ }
እንደ ተንጠለጠለችም አድርጋችሁ ትተዋት ዘንድ (ወደምትወዷት) መዘንበልን ሁሉ አትዘንበሉ፡፡ ብታበጁም ብትጠነቀቁም አላህ መሓሪ አዛኝ ነው፡፡ (129)]
💥በቃ እቤቱ ውስጥ ለጌጥ ወይም ለሌላ ጉዳይ እንዳስቀመጠው እቃ ርስት ማድረግ፤ ሀሳቧን፣ አስተያየቷን፣ ምክሯን፣ ፍላጎቷን፣ ምርጫዋንና የህይወቱ አጋርነቷን ችላ ማለት፤ ቦታ መንፈግ፣  እንዳትናገር እንዳትሳተፍ አናት አናቷን መኮርኮም እና የመሳሰሉት ሁሉ ከአንድ በላይ ሚስት ለሰላቸውም ሆነ ለባለ አንዶቹም አስነዋሪ የሆነና የመልካም ባሎች ባህሪም ያልሆነ አያያዝ ነው። 💥
  እሱ የሚፈልገውን ሲያስደርጋትና ሲያዛት ችላ የማይላትን የሷ መብት ግዜ መዘንጋቱ የማያዋጣ ሲሆን ትእዛዝንም የመጣስና የማመፅ እንዲሁም የበዳይነት ምግባር ነውና እርምት ያስፈልገዋል።
አላህ አዝ'ዘ ወጀል'ለ በኑዛዜው
« በመልካም ተኗኗሯቸው።»
«እንደተንጠለጠለ እቃ አታድረጓቸው።» ሲል
መልእክተኛውም [ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም]
«ሙእሚን ሙእሚኗን (ሚስቱን) አይጠላም። የሆነ ነገሯን ቢጠላ እንኳ ሌላ ነገሯን ይወዳልና።» ባሉት መሰረትና
« ኸይረኛ ማለት ለቤተሰቡ መልካም የሆነ ነው።» …… ሀዲስ
 የሚሉት አንቀፆችና ሀዲሶች ሁሉ በተለይ በአንዳንድ ባሎች ዘንድ ተገቢውን ቦታ እንዳላገኙ ያሳያል። ሚስቶች ባሎች እንደሚፈልጉት ሁልግዜ ሙሉ በመሉ ተወዳጅ የሆነን ባህሪ ያሳዩ ማለት ይከብዳል። ወንዶችም እንደዚሁ።
  ነገር ግን አብዛኛው ጉዳይ አግባቢ እስከሆነ ድረስ ሌሎች የቁርሾ ሰበቦችን ናቅ በማድረግ ልብን ማስፋት ይቅርታን ማብዛት የክቡሮች ባህሪ ነውና እንንቃ።❗

No comments:

Post a Comment