ወደ ባለትዳሮቹ መቅረብ የሚችሉ ግለሰቦች ለነርሱ መራራቅና ለአንዳቸው ባንዳቸው ላይ ማመፅ ሰበብ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል።
በመሆኑም በሁለቱ ግለሰቦች ዙርያ የሚገኙ ወዳጆች መልካምን በማሰብም ይሁን በሌላ አስተሳሰብ…… የወዳጆቻቸውን ትዳር ከሚያናጋ አካሄድ ሊርቁ ይገባል።
ይህ ሲባል ግን እሷ ወይም እሱ ሲበደል በዝምታ ይለፉት ማለትም አይደለም። ይልቁንም ባላቸው ቅርበትና ወዳጅነት ልክ ለማግባባት መጣር አለባቸው።
በባለ ትዳሮች መሃል በመግባት በተለይ ሴቷን የሚቀይሩ፣ ባሏን እንዳትታገስ፣ በእቅሙና በኑሮው ልክ ተቻችላ እንዳትኖር እያናናቁ ገፋገፋ የሚያደርጓት ይኖራሉ።
በዚህም ሰበብ ቀላል የነበሩ ኣለመግባባቶችም ሆኑ ግጭቶች ወደ መካሰስ፣ ወደ መበዳደልና መለያየት ያመራሉ።
ስለሆነም አንዲትን ባለትዳር ሴት በባሏ ላይ እንድታምፅ ያደረጋት ማለትም ስነምግባሯ፣ ፀባይዋ እንዲበላሽ ሰበብ የሆነ ሰውን በተመለከተ ጠንካራ የሆኑ ማስጠንቀቂያዎች ተላልፈዋል።
የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዳሉት:
”مَنْ خَبَّبَ زَوْجَةَ امْرِئٍ أَوْ مَمْلُوكَهُ فَلَيْسَ مِنَّا “
« ያንድን ሰው ሚስት ወይም አገልጋይ (ሰራተኛ) በሱ ላይ ያሳመፀ ከኛ አይደለም።» ብለዋል።
እንዲሁም
" ملعون من خبَّب امرأة على زوجها "
« አንዲትን ሴት በባሏ ላይ ብልሹ እንድትሆን ያደረገ ዕርጉም ነው። » ብለዋል
ይህንን በተመለከተም ሸይኽ ሷሊህ ፈውዛን አልፈውዛን ሃፊዘሁላህ ሲያብራሩ :--
“ ለመጥፎ ፀባይዋ ሰበብ የሆነ፣ ወደ ክፋት የጎተጎታት ፣ የሳባትና በባለቤቷ ላይ እንድታምፅ፣ ስርዓት እንድትጥስ ያደረጋት ሰው ከመልካም ሙስሊሞች አባል እንዳልሆነና ኣልፎም ከአላህ ራህመት የራቀ ዕርጉም መሆኑን ያሳያል። ” ብለዋል
በዚህ መሰረት በተለይ ባሁኑ ወቅት ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ሆኗል። የእያንዳንዱን ቤተሰብ የሚያንኳኳ ዜናም እየሆነ ነው።
ይህ ባህሪ በሚስት ጓደኞች፣ ቤተሰቦች፣ ወላጆች፣ እንዲሁም ጎረቤቶችና ሌሎችም ጣልቃ ገብ ባህሪ ያላቸው ግለሰቦች የተፈተኑበት ሆኗል፡፡
" አዛኝ ቅቤ አንጓች " እንዲሉ
ለትዳሮች መፈረካከስ ሰበብ እየሆኑ ለሷ ብዬ ነው ለሱ ብዬ ነው የሚሉ ወገኖችም ሊመከሩና ይህንን የመሳሰሉ ሃዲሶችን ልብ ሊሉት ይገባቸዋል።
ሸይኽ ሷሊህ ፈውዛን አልፈውዛን አክለው ሲያስረዱ
“ በተለይ የሚስት ወገኖች በባሏና በርሷ መካከል ቁርሾን ሊያስወግዱና እርቅ ሊፈጥሩ በዚህም ላይ ሊተጉ ግዴታ ይሆንባቸዋል ።
ዞሮ ዞሮ ይህ ጉዳይ ለራሳቸውም ለሚስቲቱም ጥቅም መሆኑን ሊያስተውሉ ይገባልና። ” ብለዋል።
( 3 / 248 ، 249 ) " المنتقى من فتاوى الشيخ الفوزان "
ስለሆነም ከዚህ አይነቱ የአጥፊነት ጣልቃ ገብነት መጠንቀቅ አለብን።
አላህ በሰዎች ጉዳይ ገብተን ፊትና ከመፍጠርና ራሳችንንም ከማስረገም ይጠብቀን።
No comments:
Post a Comment