Wednesday, 27 January 2016

ጥንቁቅነት፣ ቆራጥነትና በአላህ መመካት

ጥንቁቅነት፣ ቆራጥነትና በአላህ መመካት
ነፍሲያ፣ የሰው ሰይጣናትና የጂን ሰይጣናት ዋነኞቹም ናቸው።
እህቴ ሆይ!  ወደ መጥፎ ነገሮች የሚጎተጉቱን ወስዋሶች በርካታ ናቸው።
ነፍሲያ ማለት የየራሳችን ስሜታዊነት ሲሆን፤  የሰው ሰይጣናት ደግሞ እንደኛው ሰዎች የሆኑ የሩቅም የቅርብም ሆነው ወደ ክፉ ነገር የሚጎተጉቱን፣ ወደ ስህተት የሚገፋፉንና የሚያመቻቹ ሰዎች ናቸው። ባህሪያቸውም የሰይጣን ባህሪ አይነት በመሆኑ የሰው ሰይጣናት ይባላሉ። የጂን ሰይጣናት ደግሞ ዋናው ኢብሊስና ዝርዮቹ ናቸው። የጂን ሰይጣናት የተባሉትም የተፈጠሩት ከጂን ስለሆነ ነው።
☞ የሰው ሰይጣንነት አንዳችን ባንዳችን ላይ የምናደርገው ክፉ እምነትና ተግባር በመሆኑም በብዙ ነገሮች ውስጥ ይገባል። ለምሳሌም በዘመኑ የመገናኛ አውታር በኢንተርኔት ብዙ ፈሳዶች ሲተገበሩ ይታያል ይሰማልም።  ሙስሊሟን ሴት ለማጥቃትና ወደ ብልግና ለመሳብም ከስክሪን በስተጀርባ እንዳሰፈሰፉ መሽቶ ይነጋል። በተለያዩ ዘዴዎች ካንቺ ጋር ይፃፃፋሉ። አንቺም ሂጃብሽ ትርጉም እንዲያጣ በሚያደርግ መልኩም ወሬ ለጀመረ ሁሉ በርሽን ክፍት ታደርጊያለሽ። የዚህኔ የባጡን የቆጡን እየፈለፈሉልሽና እያስለፈለፉሽ ወደ መረባቸው ይከቱሻል። የትዳርም ይሁን ሌላ ወሬ ይዘው ያስወኙሻል። ይህ ጉዳይ አንተ ወንድሜንም ይመለከተሃል
በእንደዚህ አይነቶቹ የሰው ሰይጣናት ተሸንግለህ እውነተኛ ማንነቷ በውል ላልተረጋገጠች ሴት የቻት ወሬ ውሃ ውስጥ እንደገባ ጨው ትሟሟለህ። ሀራምን የመራቅ ብቃትህ፣ ሃይልና ሰብርህ ሁሉ ይመክናል።
እናስተውል...❗
ነቢዩላሂ ዩሱፍ አለይሂሰላም ምርኮኛ ሆነው እንደፈለጉ በሚያዝዟቸውና በሚያደርጓቸው ንጉስ ስር በቤተመንግስት ነዋሪ ነበሩ።ንጉሱም ሆነ ንግስቲቱ ያዘዙትን ከመፈም ውጭ ማምለጫ አልነበራቸውም። በክፍሉ ውስጥ ብቻውን እያለ የንጉሱ ሚስት በጣም ተውባና ተቆነጃጅታ ዘው ብላ ገባችበት።  በሮቹን ሁሉ ቆላለፈቻቸው። ለእርሱ ስትል ዝግጅቷን እንዳጠናቀቀችም አበሰረችው። የምትፈልገውን እንዲያደርጋት ነገረችው።
ይህንን ታሪኽ አላህ በቅዱስ ቃሉ እንደገፀልን፦
وَرَاوَدَتْهُ الَّتِي هُوَ فِي بَيْتِهَا عَن نَّفْسِهِ وَغَلَّقَتِ الْأَبْوَابَ وَقَالَتْ هَيْتَ لَكَ ۚ قَالَ مَعَاذَ اللَّهِ ۖ إِنَّهُ رَبِّي أَحْسَنَ مَثْوَايَ ۖ إِنَّهُ لَا يُفْلِحُ الظَّالِمُونَ [١٢:٢٣]  
« ያቺም እርሱ በቤትዋ የነበረባት ሴት፣ ከነፍሱ አባበለችው፤ ደጃፎችንም ዘጋች፤ ላንተ ተዘጋጅቼልሀለሁና ቶሎ ና አለች፤ "በአላህ እጠበቃለሁ" እርሱ (አሳዳሪዬ የገዛኝ) ጌታዬ ኑሮዬንም ያሳመረልኝ ነውና (አልከዳውም)፤ እነሆ! በደለኞች አይድኑም፤ አላት።»  ዩሱፍ : 23
ነቢዩላሂ ዩሱፍ አለይሂ ሰላም ስሜቱን ከጫፍ የሚያደርሱ ነገሮች ቢመቻቹለትም ራሱን አቅቦ አሳዳሪ ንጉሱንም ላለመክዳት፣ ፈጣሪ ጌታው አላህንም በመፍራት ይህን አጭር ምላሽ ሰጣት። ምንም በንግስቲቷ ጥላ ስር ቢኖርም፣ በሩን ቆላልፋበት ብታስገድደውና አማራጭ ማምለጫ ባይታይም የጭንቅ ግዜ ደራሹ ወደሆነው አላህ ጥሪውን አቀረበ።
قَالَ مَعَاذَ اللَّهِ 
 «በአላህ እጠበቃለሁ አላት»  ዩሱፍ : 23
 በልቡ ውስጥ ያለና እርግጠኛ እምነቱ ነበርና ጌታው አላህም ጠበቀው ፤ ከፈተናው አዳነው።  የዚህ አይነቱ ወደ ፀያፍ ተግባር የሚደረግ ጥሪ ዛሬም በኢንተርኔት  የቻት መስኮቶች በተደጋጋሚ እየተተገበረ ነው። ነገር ግን ከወንዱም ከሴቷም የነብዩ ዩሱፍን አይነት አቋምና ምላሽ ማን ይስጥ ❓ «በአላህ እጠበቃለሁ!»  ከሰው ሰይጣናት ለመጠበቅ የአላህ ፍራቻና ዱዓእ ሊለየን አይገባም። 
ውድ እህቴ በተለያዩ የመገናኛ መስመሮች ከሚደረጉብሽ ትንኮሳዎችና የተሳሳቱ ግብዣዎች ራስሽን ተከላከይ❗
አላህ ሆይ ከጥፋት ሁሉ ጠብቀን።


ሴቶች ከወንዶች ጋር እንደ ልብ መቀላቀል ስለመከልከላቸው

ከአቢ ኡሰይድ አል አንሷሪይ ረዲየላሁ ዐንሁ እንደተወራልን

    የአላህ መልእክተኛ () ከእለታት አንድ ቀን ከመስጂድ በመውጣት ላይ ሳሉ ወንዶች ከሴቶች ጋር በመንገድ ላይ ተቀላቅለው ተመለከቱ ይህንን ክስተት በማስመልከትም:-
📃‹‹ከወንዶች ወደ ኋላ ሁኑ፤ የመንገዱንም መሀከል ይዛችሁ ልትጓዙ አይገባም፤ የመንገዱን ጥግ ያዙ ›› አሉ፡፡  
ይህንን ሀዲስ ያወራልን ሰሀቢይ ክስተቱን እንዲህ ሲል ገለፀ:
📜 ‹‹ከዚያ በኋላ ሴቶች በጣም ወደ ዳር ከመውጣታቸው የተነሳ ልብሳቸው በአጥር ይያዝ ነበር፡፡›› በማለት ይናገራል፡፡

📇[አቡዳውድ ሱነናቸው ላይ ሲዘግቡት አልባኒ ሀሰን የሚል ደረጃ ሰጥተውታል]

ከሐዲሱ የምንማራቸው ነጥቦች
•••••••••••••••••••••••••••••••••
1 ሴቶች መስጂድ በመሄድ የግዴታን ሰላት ከወንዶች ጋር መስገዳቸው የተፈቀደ መሆኑን
2 ሴቶች ከወንዶች ጋር ከሚያነካካቸውና ከሚያጋፋቸው እንቅስቃሴዎች መራቅ እንዳለባቸው
3 እንኳንስ ለዱንያዊ ጉዳያቸው ሲንቀሳቀሱ ይቅርና ለኢባዳ እንኳን በሚወጡበት ግዜ በተቻላቸው አቅም ከወንዶች ጋር ልቅ በሆነ ሁኔታ ከመቀላቀል መቆጠብ እንዳለባቸው
4 ለፈተና የሚዳርግ ወይም ብዙሃኑን ጎጂ የሆነ ነገር ሲታይ እውቀቱና አቅሙ ያለው ሰው በዝምታ ማለፍ እንደሌለበት
5 አንድን ስህተት በምንቃወምበት ግዜ በጥሩ ስርአት መሆን እንዳለበትና መፍትሄውንም መስረዳት ተገቢ እንደሆነ
6 ሰሃቢያት አላህ ከሁሉም ላይ ስራዎቻቸውን ይውደድላቸውና ፤ ግዴታቸውን ለመወጣት፣ ትእዛዝ ለማክበር ምን ያህል ትጉህ እንደነበሩ
7 አንድን የአላህ ትእዛዝ ለመተግበር ስንንቀሳቀስ ሌላውን ትእዛዝ ወይም ደንብ መጣስ እንደሌለብን
8 ሰሃቢያት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከወንዶች እንዳይጋፉ ሲለዩአቸው :
ምን ችግር አለው፣ ኒያችንን አላህ ያውቃል፣ የመጣነው ለኢባዳ ነው፣
 የመሳሰሉትን ራስን መሸንገያ ቃላቶች እንዳላንፀባረቁና ጭራሽ ልብሳቸው በአጥር እስኪያዝ ድረስ ከፈተና ለመራቅ ይጠነቀቁ እንደነበር ተምረንበታል።
አላህ ሀቅን ያሳውቀን ባወቅነውም የምንሰራበት ያድርገን።


አምስት ምክሮች ለላጤዋ እህቴ

ከሸይኽ ኡበይድ አልጃቢሪይ
ምክሮች
ጥያቄ፦
ትዳር ሳትይዝ በመዘግየቷ ሀዘን ውስጥ ተዘፍቃ ላለችዋ እንስት ምን ይመክራሉ ?

ምላሽ፦
ማንኛውም ሰው ወንድም ይሁን ሴት፤ ከሀራም ለመጠበቅ፣ ጉድለቱን ለመጠገንና፣ አላህ የፃፈለትን ልጅ ለማግኘት ሲል፤
ገና በጊዜ ቢያገባ ደስ ይለዋል ይፈልጋልም ።
★ ነገር ግን የብዙሃኑ ሰው ትዳር ይዘገያል፤
በተለይ ደግሞ የእንስቶች ይበልጥ ይዘገያል ።
የእንስቶችን ጉዳይ በተመለከተ፤
አላህ ካዘነለት በስተቀር በሁሉም ስፍራዎች ቤቶች ትዳር በሌላቸው ሴቶች ተሞልተዋል። ከላጤ ሴቶች ነፃ የሆነ ቤት የለም።
ለእነዚህ እንስቶች የምመክረው
1ኛ: ሰብር ( ትዕግስት)
★ መልዕክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ለአጎታቸው ልጅ ለዐብደላህ ኢብኑ ዐባስ ረዲየላሁ ዐንሁማ
ረዘም ባለው ሀዲሳቸው እንዳሉት:
እወቅ (ግንዛቤ ይኑርህ)
ድል ከትዕግስት ጋር ነው!
(ስኬት የሚገኘው በትዕግስት ነው)
ከጭንቀት ግልግልም ከችግር ጋር ነው። (ጭንቀትን ለመገላገል ችግርን መቋቋም ግድ ይላል። )
ከችግር ጋርም ገር ነገር አለ።
ይህንን የነቢዩን صلى الله عليه وسلم
ምክር አትርሺ።
 ( የምትፈልጊው ምቾት መምጫው ቀርቦ ይሆናልና፤ ያለሽበት ችግር ትካዜ ውስጥ አይዝፈቅሽ )

2ኛ: ዚክር፣ ዱዓእ፣ ቁርኣን መቅራት

 yአላህን በማውሳት በዚክር፣
yእሱን በመለመን በዱዓእ፣
yቁርኣንን በመቅራት፣
yበተስቢህ (ሱብሃን አላህ በማለት)
yበተህሊል (ላኢላሃ ኢለላህ
በማለት)
ራስሽን ወጥሪ (ቢዚ አድርጊ)።
በተለይ ምርጥ ወይም ብልጫ ባላቸው ወቅቶች :
የሌሊቱ ሁለት ሶስተኛው ካለፈ
በኋላ
የጁምዓ የመጨረሻዋ ሰዓት ላይ
ዝናብ እየወረደ (እየዘነበ) ባለበት ወቅት፤
ሙስሊሟ፤ ለዲኗም ለዱንያዋም የሚደግፋትን የትዳር ጓደኛ ከአላህ ትለምን።
ዋናው ነገር ባል ማግኘቱ ብቻ አይደለም።
ይህ ባል የሚጠቅማትና የምትደሰትበት ሰው መሆኑ ነው)
አንዳንድ ባሎች ፀጋ (ምቾትና ድሎት) አይደሉም። እንዲያውም ቅጣት፣ መከራና ስቃይ ናቸው።
ስንትና ስንት ሴቶች ናቸው በእንዲህ ዓይነቱ ትዳር ሰበብ በስቃይ ተንገላተው የተፈተኑ።
ከምሬት የተነሳም በወንጀሎች ላይ የወደቁም ቀላል አይደሉም።
3 ኛ : አላህ ከዚህ የላጤነት ችግር እንደሚያወጣት እርግጠኛ መሆን ይገባታል።
~> አላህ እሱን ፈሪ ለሆኑት በሙሉ ቃል የገባዉን (በማሰብ ከችግሯ እንደሚያላቅቃት) እርግጠኛ መሆን አለባት። ይህም ጉዳይ ወንዱንም ሴቷንም የሚያጠቃልል ነው።
قال الله تعالى:
وَمَن يَتَّقِ اللَّهَ يَجْعَل لَّهُ مَخْرَجًا وَيَرْزُقْهُ مِنْ حَيْثُ لَا يَحْتَسِبُ وَمَن يَتَوَكَّلْ عَلَى اللَّهِ فَهُوَ حَسْبُهُ [الطلاق ٢]

አላህንም የሚፈራ ሰው ለእርሱ መውጫውን ያደርግለታል። ከማያስበውም በኩል ሲሳይን ያደርግለታል” (አል-ጠላቅ 2)

4 ኛ: ወደ ሀዘን አትዘፈቅ

ሀዘን ወይም ትካዜ ከበስተጀርባው ጉዳት ያስከትላል ። ሃዘን አይጠቅምም፤ ወደ ሴቶቻችን ልቦናቸው ሸይጣን እንዲገባም መንገድ ይከፍታል።
እኔ እንደሚታየኝ ሀዘን ሙስሊሟን ተስፋም ያስቆርጣታል። ተስፋ መቁረጥ ደግሞ ሀራም ነው፤ ጭራሽ ወደ መጥፎ አካባቢዎች ይወስዳትም ይሆናል።
ወደ መጥፎ እርምጃም ይከታት ይሆናል፤
P አላህን ትፍራ
Pትታገስም
 ከአላህ ጋርም ትተሳሰብ (በደረሰባት እንግልት ከአላህ መልካምንዳን ትከጅል)
 እሱ ያለችበትን ህይወት ወደ መልካሙ የሚቀይርላት ጥራትና ልቅና የተገባው አምላክ ነውና።

5 ኛ: አንዳንድ እንስቶቻችን የሚፈፅሙት ስህተት ኣለ¹

እሱም የሚያጫትን ሰው በራስዋ መንገድ ለራስዋ ማፈላለጓ ነው።
ታፈላልጋለች ከዚያም ወደ ቤተሰቦቿ ታመጣዋለች።
ሁሉም ሰው የየራሱ አስተያየት አለውና እነርሱ ባልተቀበሏት ግዜ ትቆጫለች፣ ቅስሟ ይሰበራል፣ ሀዘንም ላይ ትወድቃለች።
ሙስሊም እንስቶች ሆይ! ይህ አካሄድ ስህተት ነው፤

 በቤትሽ እርጊ አላህ የለገሰሽን ዲን ኢስላምን ተላብሰሽ በሃይማኖተኝነትሽ ፅኚ።

 ቀድሞ የመከርኩሽንም ደግሜ እመክርሻለሁ
 ራስሽን ለውርደት አትዳርጊ
 ከውርደትም አንዱ ወንድ ልጅ በውጭ አፈላልገሽ ወደ ቤተሰቦችሽ ማምጣትሽ ነው።
 ይህ ደግሞ በባህላችንም ሆነ በሸሪዓችን ጉድለት ነው።
==============

¹ ( ኢስላም የጥፋት በሮችን ከጅምሩ ይዘጋል፤ የሁለትዮሽ ግንኙነትና መለማመድ የሚያስከትሏቸው መዘዞች ከባድ ናቸው። ሸይጣንም ሶስተኛ ነውና አጉል በራስዎ አይተማመኑ።
ይጠንቀቁ –ተርጓሚው―)

ABU FEWZAN

የፌስቡክ ዉሏችንን እንገምግም... አላሁል ሙስተዓን!

የፌስቡክ ዉሏችንን እንገምግም... አላሁል ሙስተዓን!

ፌስቡክም ይሁን መሰል የማህበራዊ ድረገፆች ብዙ ጥቅም እንዳላቸው የማይካድ ቢሆንም ጥፋታቸውም ከባድ ነው።  ባለፉት አመታት በሀገራችን የታዩ ኢስላማዊ መነቃቃቶችን ተከትሎ ፌስቡክ አብዛኛው ህዝበ ሙስሊም ዘንድ እንደብቸኛ የዜና እና የዳእዋ ምንጭ በመታየቱ ተቆጥሮ የማይዘለቅ ህዝብ ፌስቡክን ተቀላቅሏል።  ያውም ጥሩ ዲነኛ የሚባለው የማህበረሰብ ክፍል። ታዲያ በአብዛኛው በጥሩ ኒያ የተጀመረው የፌስቡክ ህይወት ግን ሁሉንም አልጠቀመም። የማንበብ ልምድ መዳበር እና ግንዛቤን ማሳደግ እንዳለ ሆኖ ለአንዳንዶች ግን ፌስቡክ ከግል ቻት እና ከሰዎች ከተገለለ የሚስጥር ግንኙነት ያልዘለለ ትርጉም ብቻ ነው ያለው። ያነባሉ ይጠቀማሉ በማይባልበት ደረጃ የጊዜ መግደያ ብቸ ያደረጉት ብዙ ናቸው።

ኢብኑ መስኡድ እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፤

لا تزول قدم ابن آدم يوم القيامة من عند ربه حتى يسأل عن خمس : عن عمره فيم أفناه ، وعن شبابه فيم أبلاه ، وماله من أين اكتسبه وفيم أنفقه ، وماذا عمل فيما علم

 «በትንሳኤ እለት የአደም ልጅ አምስት ነገሮችን ሳይጠየቅ እግሮቹ ከጌታው ዘንድ አይራመዱም።  እድሜውን በምን እንደፈጀው፣ ወጣትነቱን በምን እንዳሳለፈው፣ ገንዘቡን ከየት እንዳመጣውና በምን ላይ እንዳዋለው፣ ባወቀው ምን እንደሰራበት» ቲርሚዚ ዘግበውታል
በእውነቱ ብዙዎች ማንነታቸውን አጥተውበታል። የሀቅ ተፃራሪ መሆኑን በይፋ ለሚለፍፍ ሁሉ  ጊዜና ልባቸውን በመስጠታቸው የእምነትና የስነምግባር መላሸቅ ውስጥ ገብተዋል። የኢማንና የአላማ ፅናትን ማጣት፣ ወንጀል በሚያወርሰው የስነልቦና ቀውስ መጠቃት የብዙዎች እጣፈንታ ከሆነ ሰነባብቷል። የነበሩበትን የእምነትና የኢባዳ ጥንካሬ ተነጥቀዋል። በየመስጂዱ ዲን ሲማር የነበረና የኢልም ጥማት የነበረው ብዙ ወጣት ኪታቦችንም ይሁን የኢልም መድረኮችን ከራቀ ሰነባብቷል።

    የተቃራኒ ፆታ ፈተናም ብዙዎችን አጭዷል። ፀረ አኽላቅ እና ፀረ ሀያእ የሆኑ ዋልጌዎች ሁሉ ሰው ጋር የሚደርሱበት ድልድይ ተዘርግቶላቸዋል። በተለይ ለሙእሚናት ፈተናው በእጅጉ ከባድ ነው!!  በፌስቡክ ምክኒያት የፈረሱ ትዳሮች እጅግ ብዙ ናቸው። በቅርቡ በምእራቡ አለም የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ፌስቡክ ከፍቺ ምክኒያቶች ሁሉ ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል። በአንዳንድ ማህበረሰቦች 60% ለሚሆኑት ፍቺዎች መከሰት ዋነኛ ምክኒያት ማህበራዊ ድረገፆች መሆናቸውን ይናገራሉ።  በአኼራ ስለ ሁሉም ነገር ከመመርመራችን በፊት ዛሬ የፌስቡክ አጠቃቀማችንን ማጤን፤ በግልም ይሁን በገሀድ ጣቶቻችን የሚፅፉትን ሁሉ መገምገምና አራስን ማረም ወሳኝ ነው።
ይህንን አውሎ ጥፋት በዝምታ መመልከትም ብዙ ዋጋ ያስከፍላልና ሁላችንም መመካከርን መተዋወስን መዘንጋት የለብንም። ኸሊፋው ኡመር ኢብኑልኸጣብ እንዲህ መክረዋል፤

«ከመመርመራችሁ በፊት እራሳችሁን ተሳሰቡ። ከመገምገማችሁ በፊትም ስራችሁን ገምግሙ። የዛሬ እራስን መመርመርና መተሳሰብ ከነገው ምርመራ ለናንተ የቀለለ ነው። »

ጊዜው አልረፈደምና አሁኑኑ እራሳችንን እንገምግም። 

ለዱንያም ይሁን ለዲናችን የማይበጀን ከሆነም ባፋጣኝ መፍትሄ እንፈልግ። አላህን በማውሳት ልቦች ይረጋጋሉ።  የፌስቡክ ምርኮኛ ከመሆን አላህ ይጠብቀን!