Tuesday, 21 February 2017

በሁለተኛ ጋብቻ ዙርያ የተደቀኑ እንቅፋቶች

በሁለተኛ ጋብቻ ዙርያ የተደቀኑ እንቅፋቶች

 ሁለተኛ፣ ሶስተኛም ሆነ አራተኛ ሚስት ለማግባት የቀድሞ ሚስትን ማሳወቅ ወይም ማስፈቀድ የጋብቻው የግዴታ መስፈርት ነውን ????

  ይህ ሀሳብ ወይም መጠይቅ የበርካታ ሙስሊሞች የልብ ትርታ እየሆነ የመጣ ጉዳይ ነው። ይህም አንዳንድ እንስቶች ባሎቻቸው ሌላ ሚስት ሲደርቡባቸው የራሳቸውን የትዳር ህይወት ጨምሮ አዲሱንም ጎጆ የማወክ ተግባር በመፈፀም የብዙሃኑን ትኩረት በመሳብ ላይ ተገኝተዋልና።

  ሆኖም አንድ ሙስሊም ግለሰብ ተጨማሪ ሚስት ከማግባቱ በስተፊት የመጀመሪያዋን ሚስቱን ማስፈቀድ ግድ አይሆንበትም። ይህንን እንደ ግዴታ የሚመለከት ካለ ማስረጃውን እንዲያቀርብ ይገደዳል። ምክንያቱም ኢስላማዊው ሸሪዓ ለጋብቻ ካስቀመጣቸው መስፈርቶች ውስጥ የመጀመሪያ ሚስቱን ያስፈቅድ የሚል ደንብ አልተጠቀሰበትምና። አንድ ሙስሊም በቀዳሚዋ ሚስቱ ላይ ሌላ ለመጨመር የሚያስችለው በቂና ጤናማ ምክንያት እስካለው ድረስ  ሚስቱን ሆነ ቤተሰቦቹን ቀድሞ ማሳወቁ ሸርጥ ወይም መስፈርት ነው ያለ ሊቅ አይታወቅም። ነገር ግን ለቀድሞውም ሆነ አዲስ ለሚመሰርተው ትዳሩ ጤናማነትና ከቤተሰቦቹም ሆነ ከማህበረሰቡ ጋር ያለው ትስስር እንዳይጎዳበት ድብብቆሹን ቢተወው መልካም ነው ይላሉ ምሁራን። ሆኖም ግሃድ ማድረጉ አዲሱንም ሆነ ነባሩን ትዳሩን እንደሚጎዳበት ባብዛኛው የታመነበት ከሆነበትና ለመላው ቤተሰቡና ለሚመራው ህይወት ደህንነት ሲል ቢሸሽግ ኢን ሻአ አላህ አይጎዳም።

  ከኒካህ ሸርጦች ዋነኛው የሴቷ ወሊይ በግልፅ አውቆ መፍቀዱ ሲሆን በምስክሮች ፊት በይፋ መፈፀሙ ደግሞ ተከታዩ ነው። በዚህም መሰረት ትዳሩን ልደብቀው ቢል እንኳ በአጭር ግዜ ውስጥ ወይም ገና ከጥንስሱ ለውዷ ባለቤቱም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ሊደርስ ይችላል። ባንደበቱ ያላሳወቀውን በሃሜት ተሸካሚዎች በኩል ቤቱን ማሳመሱ የማይቀር ይሆንበታል። በዚህም ሰበብ ላላስፈላጊ ሀሜት፣ ግጭትና የኑሮ መናጋት ሊጋፈጥ እንደሚችልም ሊገምት ይገባዋል። በራሱ በኩል ብታውቅና ምላሿም ሆነ አፀፋዋ እስከምን እንደሆነ በይፋ ማወቁ ራሱ ለመፍትሄው መዘጋጀትን ያፈራ ይሆናል። ሆኖም ይህ አካሄድ የሚመረጠው ከባለቤቱ ግንዛቤና ሁኔታ አንፃር ለጉዳዩ የሚኖራትን ምላሽ በመገመት ይሆናል።

የመጀመርያው ሳንካ

የቀዳሚ ሚስቶች ተቃውሞ ሲሆን በዚህ አካሄዳቸው በርካታ ጥፋትን አስከትለዋል። ከዚህ ስጋት የተነሳም ደፍረው ወደ ጋብቻው የተጓዙ ባሎች እንኳን ነገሩን በድብብቆሽ ይጀምሩታል።

   ደርቦ ማግባትን በተመለከተ ሚስቶች የመፍቀድም ሆነ የመከልከል ስልጣን ባይኖራቸውም በመልካም አብሮ መኗኗር የትዳር ዋነኛው ተፈላጊ መርህ በመሆኑ ያንን ሊጎዱ ከሚችሉ ውዥንብሮች ለመራቅም ሲባል ጭውውቱን በይፋ ማድረጉ ለባል የውስጥ ለውስጥ ጦርነቶችን ይቀንስለታል። ቀድሞ በይፋ እንዳያሳውቅ ከሚያደርጉት ምክኒያቶች ዋነኛው ግን ብዙሀኑ ሴቶች ለጉዳዩ ያላቸው አሉታዊ ምልከታ ነው።

 እንደሚታወቀው አላህ በእዝነቱ ልቦናቸውን ያቀናላቸው እንስቶች ሲቀሩ አብዛኞቹ ሴቶች ባላቸው ሌላ ሴት መደረቡን መቀበል ይከብዳቸዋል። ይኸ ደግሞ የምቀኝነትና የአልጠግብ ባይነት ውጤት ብቻ ነው ብሎ ማሰብ ስህተት ነው። ምክንያቱም የራሳቸውን ለራሳቸው ብቻ እንዲሆን መመኘታቸው ፈጣሪያችን አላህ በነሱ ውስጥ የፈጠረው ጤናማ ስሜትና እውነታ ነውና። የሚያወቃቅሰው ተኮናኝ ነገር ይህንን ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ ከመብታቸውና ከሸሪዓዊ መፍትሄዎች በላይ መራመዳቸው ብቻ ነው።

ሁለተኛው ሳንካ

የባሎች በቀዳሚዋ ሚስቶቻቸው አያያዝ ላይ ስህተት ላይ መዘፈቅና ሁለተኛዋን ሲያፈላልጉም ሸሪዓዊ ባልሆነ መንገድ የመንቀሳቀሳቸው ጉዳይ ነው።
  እርግጥ ነው በዘመናችን በያቅጣጫው የምናስተውለውን የባሎች በዳይነትና ቀድመው ያገቧቸውን ሚስቶች እርግፍ የማድረግ፣ በችግር ግዜ ከመድከም አልፋ የሞተችለትን በተመቸው ግዜ የመዘንጋት እውነታ እንዲሁም በአላስፈላጊ የኢኽቲላጥና የኸልዋ በሽታ በመጠቃት ክብረቢስ በሆነ መንገድ ለሌላ ጋብቻ መንደርደር በቀዳሚዎቹ ሚስቶች በኩል ጉዳዩ ተቀባይነት እንዳያገኝ እና ብሎም   እንዲኮነን ምክኒያት ይሆናል።  ይህ ጥፋት በአላህ ዘንድም ባሎች በዱንያም በኣኺራም የሚያዋርዳቸው ርካሽ ተግባር መሆኑን ልብ ሊሉት ይገባል።

ሸሪዓዊ ድንበሮችን መጣስ ውጤቱ የከፋ ነውና !!

  እንደሚታወቀው ለየትኛውም ስርዓታችን መመርያዎችንና የአፈፃፀም ደንቦቹን የምንቀስመውና በአርኣያነት የምንከተለው ከፈጣሪያችን ወደኛ ከተላኩልን መልእክተኛው ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ነው። እሳቸውም ከአምልኮ ስርኣትና ህግጋት ጀምሮ የማህበራዊ ኑሮ ስርኣቶችን እስከ ግላዊ የህይወት መርሆቻችን ሁሉ ምንም ሳያስቀሩ በአንደበታቸውም በተግባራቸውም መክረውናል። የሚያፀድቁትን በማፅደቅ የሚወገዘውንም በማውገዝ አስተምረውናል። ከነዚህም መካከል የትዳር ህይወት ዋነኛው የዱኒያ ላይ መጠቃቀሚያችን ነው።

  በዚህ የህይወት መስክ ነቢዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ከአንድ በላይ አግብተው ነበር። በዚህም ሂደት ውስጥ ከውዶቹ ባለቤቶታቸው መካከል አንዳቸውንም ማስፈቀዳቸው አልተዘገበም። ልክ እንደዚያው የሳቸው ባልደረቦችም ረዲየላሁ ዐንሁም ከአንድ በላይ አግብተው ነበርና ሚስቶች ነበሯቸው። ይሁንና ከመካከላቸው አንዳቸውም ፍቃድ የጠየቋቸው አልነበሩም። ይህ እንግዲህ ተጨማሪ ሚስት ለማግባት የመጀመሪያዋን ሚስት ማስፈቀድ ግድ አይደለም ለሚለው በቂ የሆነ ሸሪዓዊ መነሻ ነው። ምክንያቱም ይህ ቀድሞውንም የሚስቶች መብት አልነበረምና ኣለማስፈቀዱም የመብት ጥሰት አይሆንም።

  ይህንኑ ርዕስ በተመለከተ የሳውዲ ቋሚ የፈትዋ  ኮሚቴ 19/53

 “ተጨማሪ ሚስት ለማግባት የመጀመሪያዋ ሚስቱን ይሁንታ ማግኘት ግድ ነው ወይ?” የሚል ጥያቄ ቀርቦለት በሰጠው ምላሽ «ባል ሁለተኛ ሚስት ለማግባት ካስፈለገው የመጀመሪያ ሚስቱን ውዴታ ማግኘት ግዴታ አይሆንበትም። ነገር ግን እንደ ጥሩ ስነምግባርና በመልካም ሁኔታ ከመኗኗር አንፃር የእንስቶችን ተፈጥሯዊ ስሜት ላለመጉዳትና በዚህ ጉዳይ የሚሰማትን ህመም ለማቅለል ሲል ቢያሳውቃትና ልቦናዋን በመንከባከብ ቢያረጋጋው መልካም ነው። ለዚህም ሲባል ፊቱን ፈታ አድርጎ፣ በመልካም ግንኙነትና በጥሩ አነጋገር እንዲሁም ይህንን ፍላጎቱን የሚያሳካ ከሆነ በአቅሙ ልክ ከገንዘቡም ስጦታ ቢያበረክትላት መልካም ይሆናል።» በማለት መክሯል። (ፈታዋ አል'ለጅናህ አድ'ዳኢማህ 19/53)

የመልካም አስተዳዳሪነት ባህሪን መላበስ ክብር  ነው!

   ለቤቱ የሚቆረቆር ባል ሁለተኛ ሚስት ከማግባቱ በፊት በቅድሚያ ለመጀመሪያ ሚስቱ ቢነግራትና ለማስማማት ቢጥር ተገቢ ይሆናል። ይህም ጥሩ የሆነ ጥቅምን ያስገኝለታል። የሚገባበት አዲሱ ትዳርም ተቀባይነት እንዲኖረው፣ ከአዲሷ ባለቤቱም ጋር በሰላም ትኖርለት ዘንድ ያግዘዋል። እንዲህ ሲባል ግን ግዴታ ነው ለማለት አይደለም።

  ከክፍለ ዘመኑ ታላላቅ ፈቂሆች መካከል አል አልላማህ ሸይኽ ኢብኑ ዑሰይሚን ረሂመሁላህ “አንድ ሰው ሌላ ሚስት ለማግባት ሲነሳ የመጀመርያ ሚስቱን ማስፈቀዱ እንደመስፈርት ይደረግበታልን? ሳያሳውቃት ቢያገባስ ብያኔው ምንድነው?” ተብለው ለተጠየቁት ሲመልሱ፤

«ፍቃድ ቢጠይቃት ማግባቱን እምቢየው ትለዋለች የሚል እምነት አለኝ። ነገር ግን ቀዳሚዋን ሚስት ፈቃድ መጠየቅ የጋብቻ ሸርጥ አይደለምና ጠይቋት እንኳን እምቢ አልፈቅድም ብትለው የማግባት መብት አለው። ከዚሁ ጋር ግን እኔ እንደሚታየኝ እሷኑ ማማከር እንዳለበትና ነገሩን አምናበት እስክትቀበለውም ቢያግባባት፣ ስለምን ይህንን ጋብቻ እንደፈለገም ቢያብራራላት መልካም ነው። በዚህ ሂደት አዲሷ ሚስቱ ብትመጣባት እንኳ የቀድሞዋ ራሷን ባረጋጋችበትና የምታውቀው ጉዳይ እንዲሁም የወደደችው ስለሚሆን ሁለቱም ሚስቶች ባለ መኮራረፍና ባለ መጠላላት ምስጉን የሆነ ጥሩ ኑሮን ይኖሩ ይሆናልና የዚህ አይነቱን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲል የቀድሞዋን ማስፈቀዱና ቀድሞ መንገሩ ተገቢ ነገር ነው። ይሁንና ይህ ጉዳይ ግዴታ ነው ወይ ከተባለ ግዴታ  አይደለም።» ሲሉ አብራርተዋል።

በተጨማሪም “ይህንን ጋብቻ ቢደብቃትስ?” የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው «ምንም ችግር የለበትም» በማለት መልሰዋል።
(ፈታዋ ኑሩን አለድ'ደርብ ሊኢብኒ ዑሰይሚን)

ሶስተኛው ሳንካ

 የፀረ ኢስላም ሀይሎች የሚዲያ ዘመቻና የማህበረሰቡ አግባብነት ያጣ ጣልቃ ገብነት በመሰረቱ ኢስላምን በበጎ እይታ የማይመለከቱ ሀይሎች ስለ ኢስላማዊ ህግጋትና የአኗኗር ስርዓት በአግባቡ ይረዳሉም ይመለከታሉም ተብሎ አይጠበቅም። ልዩነታችን ከመሰረታዊው የእምነታችን ርዕስ ከአሃዳዊው የአምልኮ ስርኣት ጀምሮ የማይገናኝ በመሆኑ በሌሎች የአኗኗር ዘይቤያችን ላይ የሚሰነዝሩት አስተያየት ሆነ የሚያራምዱት አቋም በአብዛኛው አፍራሽ ነው። ስለዚህም ለዚህ ርዕስ የሚሰጡትን የመፍትሄ አቅጣጫ የማንጋራው ብሎም የምንቃወመው ነው።

  እንደ ምሳሌነት በሀገራችን ያለውን የሚዲያ ሽፋንና ከተለያዩ ተቋማት የሚሰነዘሩትን ውግዘቶች እንዲሁም ለሴቶች በሚል የተቀመጡትን ደንቦች ካስተዋልን በቀጥታ ሃይማኖታዊ ስርዓታችንን ለማጣጣል የሚደረጉ ፍልሚያዎች መሆናቸውን እንረዳለን። ከአንድ በላይ ያገባ እንዲታሰር፣ ሚስት ተስማምታ እንዳትኖርና ክስ እንድትመሰርት እንዲሁም ንብረት እንድትካፈልና ወደ  ወዘተ ግፊት ይደረጋል።

  በማህበረሰቡም በኩል በአንዳንድ ኢስላምን ባግባቡ ባልተረዱ ሙስሊሞችም ሆነ በሌሎች አዛኝ ቅቤ አንጓቾች የሚደረገው አጉል የሆነ ጣልቃ ገብነት ለዚህ የትዳር ስርኣት ክፉ እንቅፋት ሆኗል። በተለይ ሙስሊሙ ከልብ ሊረዳው የሚገባው በባልና ሚስት መካከል በመግባት አመፅን ማነሳሳት፣ የሚስትን ልቦና ማስሸፈት የተረገመና ከመልእክተኛው ጎዳና ያፈነገጠ መስመር መሆኑን ሊያስተውል ይገባል።

  የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም «ሚስትን በባሏ ላይ ያሳመፀ ከኛ አይደለም።» ማለታቸው በአቡዳዉድ (2175) ተዘግቦ አል አልባኒይ ሰሂህ ብለውታል ። በሌላ የአቡ ዳዉድ (5170) ዘገባም የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም «የአንድን ግለሰብ ሚስት ወይም ሰራተኛ (አገልጋይ) ያስሸፈተ ከኛ አይደለም።» ብለዋል። ይህንንም አል አልባኒይ ሰሂህ ብለውታል።

  በሌላ በኩል ባል ይህንን የመሰለ ግዙፍ ጉዳይ ከሚስቱ መደበቁ ታማኝነቱና እውነተኛነቱ ላይ ጥያቄ አይፈጥርበትም ወይ ሊባል ይችል ይሆናል። ለዚህ ምላሽ የሚሆነው ባል የመጀመርያ ሚስቱ የዚህ አይነቱን ዜና ቀድማ ብትሰማ ጋብቻውን እንደማትቀበልና የትዳሩንም ህልውና ስጋት ውስጥ እንደሚጥል ስለሚያውቅ ሊሆን ይችላል። የዚህ አይነቱን ሸሪዓዊ ብይንና ስርዓት የሚቃወሙ የጥፋት ሚዲያ ሰለባዎች በአቅራቢያዋ መብዛታቸው ትዳሯን እንድታናጋ ሊጋብዛት ይችላልና። ባል ገና ለሷ ከማሳወቁ ከሃዲና ቃሉን የማይጠብቅላት በዳይ እንደሆነ አድርጎ በመተቸት ይህ ማህበረሰብ ግፊት ይፈጥርባታል። ከዚያም የከፉ የሀሰት ወቀሳዎችን በመለጠፍ ከጅምሩ ህይወቱን ያናጉበታል።

  ሸይኹል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያ ረሂመሁላህ በመጅሙዕ አልፈታዋ (23/363) «የአንድ ሰው በባልና ሚስት መሃል ገብቶ ለማለያየት መጣር ከባድ የሆነ ኃጢኣትና የድግምተኞች ተግባር አይነትም ነው። ይህም ትልቁ የሸይጣናት ስራ ነውና።» ብለዋል።

  ሸይኽ ሷሊህ አልፈውዛንም ሀፊዘሁላህ «ሚስትን በባሏ ላይ ያበላሸ (ስርኣት አልበኛ ያደረጋት፣ በባሏ ላይ እንድታምፅ ያመቻቻት) የተረገመ ነው።» የሚል ሐዲስ ስላለ የሚስት ቤተሰቦችም ቢሆኑ በባልና ሚስት መካከል ያለውን ችግር ፈትቶ ለማስታረቅ መጣር ግዴታ ይሆንባቸዋል። ይህም ለሷም ለነሱም ጠቃሚው ነውና። ብለዋል። (አልሙንተቃ ሚን ፈታዋ አሽሸይኽ ፈውዛን (3/248-249)

  እርግጥ ጣልቃ ገቦችን ወደዳር ለማውጣት እንዲረዳው ወንድ ልጅ ሁለተኛ ሚስት ሲያገባ የቀድሞ ሚስቱን ለማሳመን እና ስነልቦናዋን ላለመጉዳት የሚጠቅሙ በርካታ የስነልቦና ባለሙያዎች ምክሮች አሉና በዚያም በመታገዝ ሊያረግባት ይገባል።

ሙእሚን የሆነች ሴትም  ባሏ ሁለተኛ  ሚስት ያገባበት ምክኒያት ምንም ይሁን ምን ጫና መፍጠርና ከኔና ከሷ ምረጥ በማለት እንዲፈታት ልትጠይቅና ማስጠንቀቅያም ልትሰጥ አይገባትም።  ይህን መጠየቋ ፍፁም የሆነ ስህተት ነው። እንደውም ሁለተኛዋን ሚስት እንዲፈታት መጠየቋ ትልቅ ወንጀል ነው። ይህንንም የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም እንዲህ በማለት አስጠንቅቀዋል።

«አንዲት ሙስሊም ሴት እህቷ (ሌላኛዋ ሚስት) እንድትፈታ መጠየቅ አይገባትም። ለሷም ከአላህ የተወሰነላት አለላትና። » ብለዋል። ይህም በቡኻሪ (4857)ና በሙስሊም (1413) የተዘገበ ሲሆን፤

«የትኛዋም እንስት ምንም ችግር በሌለበት (ለፍቺ በማያበቃ ሁኔታ) ባሏን ፍቺ ከጠየቀች የጀነት ሽታ ሃራም ይሆንባታል።» ማለታቸው ደግሞ በቲርሚዚይ (1187) በአቢዳዉድ (2226) እና በኢብኑ ማጃህ (2055) ተዘግቦ አል አልባኒም በሰሂህ አቢዳዉድ ላይ ሰሂህ ብለውታል።

  እንደሚታወቀው የባሏ በሷ ላይ ሌላ ሚስት መደረብ ብቻውን ለፍቺ የሚያበቃ ጉዳይ አይደለም። ሴቶቹ ይህንን ማስጠንቀቅያ ባለማወቃቸው ወይም ባለማስተዋላቸው ስህተት ውስጥ ይዘፈቃሉ። ብዙውን ግዜ ባል ለመጀመርያ ሚስቱ ለተጨማሪ ጋብቻ መሰናዳቱን ቀድሞ ባሳወቀ ቁጥር ለቤቱ መናጋት ብሎም ለትዳር መፍረስና ለልጆች መበተን ሰበብ እንደሚሆንም ተስተውሏል። በዚህም ሰበብ ቤተሰቡን ከመናጋት ለመጠበቅ ሲል ቀድሞ ከማሳወቅ ሲታቀብም ይታያል።

  የዚህ ድብብቆሽ ዋነኛው ምክንያት ይህንን አምላካዊ ህገ - ብያኔ የሚቃረነው ማህበረሰብ በትዳሩ ውስጥ እጁን በአሉታዊ መልኩ ማስገባቱ መሆኑን እንዳወሳነው ሁሉ መጥፎ ተፅዕኖውን ለመጠቆም ያህል አንዳንዷ ሚስት ባሏ በግልፅ ጋብቻ ከሚደርብባት ይልቅ ያለ ጋብቻ በድብቅ ከባዕድ ሴት ጋር ሃራም የሆነ ጉድኝት ፈጥሮ ቢኖር የምትመርጥ ትኖራለች።

  ስለዚህም ባሎቻቸው ሲያገቡባቸው ቤታቸውን በአንድ እግር ከማቆምም አልፈው እስከመፋታት ሲደርሱ፤ ባሎቻቸው ባልገው ሲገኙ ግን በቀላል ሽምግልና ወይም ተቃውሞ ያልፉታል። አንዳንዴም እያወቁ  እንዳላወቁ ሆነው ያሳልፉታል። ይህ ደግሞ የተነባበረ ድንቁርና ሲሆን ለባሎችም ሁለተኛ ትዳራቸውን መደበቅ ትልቁ ምክንያት እየሆነ ይገኛል። በዚህ የተነሳ ተጨባጩን ሁኔታውን በማመዛዘን ለቀድሞው ትዳሩ፣ ለልጆቹና ለቤቱ ሰላምና ጠቀሜታ በማሰብ ደብቋት ቢያገባ ያስነውራልን ??? ባል የቤቱ አውራ መሪ ስለሆነ ለትዳሩ ጠቃሚና ጎጂ ሂደቶችን መርምሮ መራመድ ግድ ይለዋል።

  ሆነም ቀረ ሚስት ከመብቷና ከሃላፊነቷ ቀድማ እኔ ካልፈቀድኩ እበጠብጣለሁ ወይ መፈታት እፈልጋለሁ ወይ ደግሞ ያገባትን ይፍታ በሚል ዘራፍ ብትል በዱንያም በኣኪራም መጥፎ ይሆናል። እርግጥ ነው የሚወዱትን፣ የሚፈልጉትንና ለማካፈል የሚሳሱለትን ለሌሎች ባለመብቶችም ማካፈል ትልቅ ሰደቃና ከአላህ የሚገኘውን ወረታ የማስቀደም ውጤት መሆኑንም ልብ ማለት ይገባል።

  በጣም የሚያስገርመው ብዙ ሴቶች ለሁለተኛ ሚስትነት ወይም ለሶስተኛነት ወይም ለአራተኛነት የጋብቻ ጥያቄ ሲቀርብላቸው ለትዳር ካላቸው ጉጉት የተነሳ በመልካም ፈቃደኝነት ይስማማሉ።  እውነታውን ስናስተውለው ሚስት እንዳለው እያወቁ ትዳሩን ይቀበላሉ፤ ይደረባሉም። ከነሱ በኋላ ሲያገባባቸው ግን ከኔ በኋላ ማንም እንዳይሰለፍ በሚል ፈሊጥ እሳት ይጎርሳሉ።

  ውዷ እህቴ! በዚህ አጋጣሚ ልምከርሽና፤ በመልካም አያያዝ የሚያስተዳድርሽና የሚንከባከብሽ ባል እስከሆነ ድረስ ሁለተኛ ሆነሽ  ስትደረቢ እንዳስተዋልሽ ሁሉ ሲደረብብሽም አስተውዪ እላለሁ።

  እንደሚታወቀው በሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ ውሽማ፣ የሚስጥር ፍቅረኛ፣ የጭንገረድ የመሳሰሉት ባህሎች ፀያፍ የዝሙት ህይወት በመሆናቸው ቦታ የላቸውም። ከምንም በላይ ወደር በሌለው መልኩ ስለ ፍጡራኑ ፍላጎትና ጥቅም የሚያውቀው ፈጣሪ አምላካችን አላህ በደነገገልን ህገ ደንብ መሰረት አንድም ሁለትም ሶስትም አራትም በስርዓቱ ማግባት የሙስሊም ወንዶች መብት ነውና ሚስቱን ደብቆም ሆነ በግልፅ አሳውቆ እንደ ተጨባጩ ለመስለሃ ማግባቱ ያስመሰግነዋል እንጂ አያስወቅሰውም። የያንዳንዱ ባልና ሚስት እንዲሁም አካባቢና ማህበረሰብ ሁኔታን ግምት ውስጥ በማስገባት የላጤዎችንም ቁጥር ለመቀነስ መጣጣር ብልህነት ይሆናል!!
  ሊዘነጋ የማይገባው ጉዳይ ከአንድ በላይ የማግባቱ መፈቀድ ዋነኛው ፋኢዳ ላላገቡት እንስቶች የትዳር እድልን ለመፍጠር፣ አምሮትንና ከሴቶች ይልቅ ለረዥም አመታት የሚቆየውን የወንዶች ፍላጎት በሀላል ለመግታት፣ ዝርያን ለማብዛት፣ ቤተሰብን ለማስፋት፣ ዝሙትን ለመቀነስ፣ ዘርን ለመጠበቅ እና ለመሳሰሉት ሲሆን ሃላፊነት በጎደለው መልኩ ለተጨማሪ ጋብቻ በመንደርደር አዲስ ጎጆ በመሰረቱ ማግስት ነባሩን መናድ እንዲሁም ወዳዲሷ በማዘንበል ቀዳሚዋን መበደል ወይም የቀድሞ ሚስቱን ጫና ባለመታገስ አዲሷን መበደል እና የመሳሰሉት ሁለተኛ የማግባትን መብት መጠቀም ሳይሆን ህጉን ለሚፃረሩት ፈንጂ ማቀበል በመሆኑ አቶ ባልም ይጠንቀቁ እላለሁ!!!አላህ መብታችንን በስርዓቱ የምንጠቀምበትና ግዴታችንንም በአግባቡ የምንወጣ ያድርገን።

በመጨረሻም፤ ሁለት ሴቶችን በአንድ ግዜ ስለማግባት ከተጠየቀ፤

ከአንድ በላይ እስከ አራት ማግባት መስፈርቶቹ እስከተሟሉ ድረስ ችግር የለውም። ይህም በቁርአን አላህ የፈቀደው ነው።

فَانْكِحُوا مَا طَابَ لَكُمْ مِنَ النِّسَاءِ مَثْنَىٰ وَثُلَاثَ وَرُبَاعَ
ከሴቶች ለእናንተ የተዋበላችሁን ሁለት ሁለት ሦስት ሦስትም አራት አራትም አግቡ፡፡» ኒሳእ 3


ከሁለት ሴቶች ጋር በአንድ ቀን ኒካህ በማሰር ጋብቻ መፈፀምን በተመለከተም በአንድ ቀን መሆኑን የሚከለክል ነገር የለም። ከላይ የተመለከትነው ፍቃድ የጊዜ ገደብ የለውም። ሆኖም  የሁለቱን ሰርግና ጫጉላ በአንድ ቀን ማድረግ እንደማይገባ የፊቅህ ልሂቃን አሳስበዋል። ይህም  የአንዷን ሀቅ በመሙላት የሌላዋ ስለሚጓደል ነው።  

No comments:

Post a Comment