Tuesday, 21 February 2017

የሙስሊም ቤተሰብ ኢኮኖሚው ገጽታ ምን መምሠል አለበት ?

የሙስሊም ቤተሰብ ኢኮኖሚው ገጽታ ምን መምሠል አለበት ? 
የሠዎች ሪዝቅ የተለያየ ነው። የአንዱ ሪዚቅ (ሲሳይ) እንደ ውቅያኖስ ሠፊ ይሆናል። ይህ ደግሞ የአላህ ችሮታ ነው። የሌላው ሪዚቅ አንደ እጅ መዳፍ  ጠባብ ይሆናል። ይህ የአላህ ጥበብ ነው። ይህ ቢሆንም ሪዝቁ የሠፋ አላህ ዘንድ የተወደደ ነው ማለት አይደለም። ሪዝቁ የጠበበም አላህ ዘንድ የተጠላ ነው ማለት አይደለም። በተቃራኒውም ገንዘብ ያገኘ ሁሉ አላህ ዘንድ የተጠላ ነው ማለት አይደለም። ገንዘብ ያጣም ሁሉ አላህ ዘንድ የተወደደ ነው ማለት አይደለም። አላህ ዘንድ መወደድና የደረጃ ብልጫ የሚገኘው በአላህ ፍራቻ  እና በመልካም ስራ ብቻ ነው። ድህነት ከትዕግስት፣ ከታታሪነት ፣ ጋር ውበት ነው፤ ሀብት ከምስጋናና ከልግስና ጋር በረከት ነው።

    ቤትን የማስተዳደር ኃላፊነት በባል ትካሻ ላይ የወደቀ ነው ኃላፊነቱና ተጠያቂነቱ የርሱ ነው። ለቤተሰቡ የሚያወጣው ወጪ አቅሙ በፈቀደ መጠን ልክ ሊሆን ይገባዋል።

      የቤት ወጭ ከብክነት እና ከንፍግነት የራቀ ሊሆን ይገባዋል። የቤት ውስጥ ስርዓት በአጠቃላይ ሚዛናዊነት ሊኖረው ያስፈልጋል።

    ሚስት ቤት የማስተዳደር ኃላፊነት በመጀመሪያ ደረጃ እርሷን የሚመለከት ባይሆንም አላስፈላጊ ወጪዎች በመቀነስና ከአቅም በላይ የሆኑ የወጪ ጥያቄዎችን ባለማቅረብ ለባልዋ ድጋፍ ልታደርግ ይገባል። ባል ለቤት የሚጠብቀው ወጭ ከፍ ባለ ቁጥር ችግር ውስጥ ይገባል፤ እዳም ውስጥ ሊዘፈቅ ይችላል። ዕዳን መሸከም ደግሞ ድንጋይ እንደመሸከም ይከብዳል። ይህ ጥሩ ባህሪውን ሊቀይረው ይችላል።ተከታትሎም የቤቱን ሠላም ያናጋዋል።

    ስርዓት ባለው መልኩ የቤት ወጪን በማውጣት እና በስስታምነት መካከል ያለውን ልዩነትን ጠንቅቆ መረዳት ያስፈልጋል። ሙስሊም ከስስት መራቅ አለበት ኢማን እና ስስታምነት በአንድ ልብ ውስጥ አይሠበሰቡም የቤት ወጭ እንደሁኔታው እንደቤተሰብ አባላት ብዛትና እንደ አካባቢው ከቤተሰብ ቤተሰብ ይለያያል። የቤት በጀትና ወጪ የቤተሰብን ብዛትና ሁኔታ እንዲሁም ፍላጎት ግንዛቤ ማስገባት አለበት።

     የቤት ወጪ ስርዓት፣ ዐቅምን በትክክል ከማወቅ ይነሳል። ወጪዎች ዐቅምን ያገናዘቡ በዐቅም የተመጠኑ መሆን አለባቸው የወጪ ቅደም ተከተሉን በስርዓት ማስቀመጥም ያስፈልጋል። የቤተሰብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ከቅንጦት እና ከትርፍ ወጨዎች ቅድሚያ ሊሠጣቸው ይገባል ያልተፈለጉና እቅድ ያልተያዘላቸው ወጭዎችን መጠንቀቅ የቤት በጀትን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመጠቀም አስፈላጊ ነው።       
 
   የቤተሰብ ፍላጎት በሚገባ ከተሸፈነ በኋላ የሚተርፍ ገንዘብ ካለ ሊቀመጥ ይገባዋል ገንዘብ የማጠራቀም ልምድ በቤት ውስጥ ማዳበር ጠቃሚ ነው። ከግዜ በኋላ ድንገተኛ ነገሮች ሊከሰቱ ይህን የተጠራቀመ ገንዘብ ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል።

  የምግብ ፍጆታ

    የብዙ ቤተሶቦች አብላጫ በጀት ለምግብ ፍጆታ ግዥዎች ይውላል የቤተሰብ የምግብ ፍጆታ ከግዥ ጀምሮ እስከ አጠቃቀም ያለው ሂደት ስርዓት ባለው መልኩ መከናወን አለበት የምግብ ብክነትና የምግብ እጥረት እንዳይኖር የቤት በጀትን በአግባቡ መከፋፈል ያስፈልጋል።

2 ለምግብ ፍጆታ የሚገዙ እቃዎችን መግቦችን ዋጋና ጥራት በትክክል ማወቅ
2 አማራጭ የፍጆታ እቃዎችን ማወቅ
2 የፍጆታ እቃዎችን ግዢ በማስታወቂያ ጫና ብቻ አለመግዛት
2 የሚያስፈልጉ እቃዎችን በሚያስፈልገው መጠን በአንድ ግዜ መሸመት
2የቤተሰብ ዐቅም የሚመጥኑ እቃዎችን መሸመት

6. የቤት ውስጥ ስነ- ምግባሮች

እዝነትን በቤት ውስጥ ማስፈን

     ወንዶች / ባሎች በቤት ውስጥ እዝነትን/ መተዛዘንን ባህል ማድረግ መቻል አለባቸው የሙዕሚኖች እናት ዓኢሻ በዘገበችው ሐዲስ ረሡል ( ሠላምና ሠላት በርሳቸው ላይ ይሁን ) የሚከተለውን መናገራቸውን ተጠቅሷል።  “አላህ ለአንድ ቤተሰብ መልካምን ሲፈቅድ በመካከላቸው መተዛዘንን ያሰፍናል።" ሐዲሱን ኢማም አህመድ ዘግበውታል።

    ለባልና ሚስት መተዛዘን በጣም ጠቃሚ የስሜት ትስስር ይፈጥርላቸዋል። ውጤቱም በህይወታቸው ላይ ግሩም ተጽዕኖ ያስገኛል። በአምባገነንነት ፣ በኃይል ቃል ትዕዛዝ በመስጠት ፣ በመጨቃጨቅና መተንፈሻ በማሳጣት ሊገኝ የማይችለውን በመተዛዘንና በመተሳሰብ ሐሳብን በመለወጥ ማግኘት ይቻላል። ለዚህም ነው ነብዩ ( ሠላምና ሰላት በርሳቸው ላይ ይሁን ) " አላህ እዝነትን ይወዳል ፤ ለኃያልና ለሌሎች ነገሮች የማይሠጠውን ለእዝነት /መተዛዘን/ ይሠጣል" በማለት የተናገሩት፡፡

መተጋገዝ

    ብዙ ወንዶች ባሎች የቤት ውስጥ ስራ ውስጥ ተሳትፎ ማድረግ ይጠላሉ። ቀላል እቃ ማቀበልን ያህል ነገር ላይ እጃቸውን ማስገባት እንኳ ያንገሸግሻቸዋል፤ በቤት ስራ ውስጥ ተሳትፎ ማድረግና የቤተሰብ አባላትን ማገዝ ደረጃቸውን ዝቅ እንደሚያደርገው የሚያስቡም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ይህ ስህተት መሆኑን ማመን ያስፈልጋል። በቤት ውስጥ ስራዎች ከቤተሰብ አባላት ጋር መተጋገዝ የመተሳሰብ አንድ ምልክት ነው። ወንዶች በዚህ ጉድ ላይ ለዓለማት እዝነት ነብይ ( ሰላምና ሠላት በርሳቸው ላይ ይሁን ) ተምሳሌታቸው አድርገው መውሠድ ይኖርባቸዋል።
ረሡል (የአላህ ሠላምና ሠላት በርሳቸው ላይ ይሁን ) በዚህ ጉዳይ ላይ እንዴት ነበሩ ?

 ዓኢሻ ( መልካም ስራዎቿን አላህ ይቀበላት ) እንዲህ መልስ ትሰጣች።
"ቤተሠባቸውን በስራ ያግዙ ነበር ፤ የሠላት ወቅት ሲደርስ ለሠላት ከቤት ይወጣሉ። "

ይህ ሐዲስ ቡኻሪ በትክክለኛ የሐዲስ ስብስብ ስራዎች ውስጥ ዘግቦታል፡፡

   በቤት ውስጥ ለቤተሰብ በሚስት ስራ ድጋፍ ማድረግ ወንዶች  ባሎች አስፈላጊ መሆኑን ከረሡል ( ሠላምና ሠላት ይሁን ) ህይወት ትምህርት መውሰድ ይኖርባቸው አንድ ባል ለሚስቱ የቤት ውስጥ ስራ ስላገዘ "ወንድነቱን " የሚፈታተን ምንም ዓይነት ስህተት አልፈጸመም። በዚህ አካባቢ ምንም ነውር የለም። የ "ወንድነት " ጥንካሬ በዚህ የሚለካ አይደለም።

   ሚስት ባልዋ የቤት ውስጥ ስራዎችን ሲያግዛት ደስታ ይሠማታል። በመካከላቸው ያለው መተሳሰብም ይዳብራል። የመፈቃቀር ስሜትንም ያቀጣጥላል። በዚህ ላይ ባል ለሚስቱ ቤት ውስጥ ስራ እገዛ በማድረጉ የረሡልን (ሠላምና ሠላት በርሳቸው ላይ ይሁን ) የህይወት ፈለግ (ሡና ) ይከተላል። በዚህም የአላህን  ውዴታ ያገኛል።

    አንዳንድ ባል ቤት እግሩ በረገጠበት ቅጽበት ምግብ እንዲቀርብለት ይጠይቃል። ምናልባት ሚስቱ በልጆች እንከብካቤና በስራ ብዛት አስር ጉዳዩችን በአንድ ግዜ የምትሰራበትን አስር  እጆች እንዲኖራት እየተመኘች ከወዲህ ወዳ እየተዋከበች ይሆናል። ምድጃው ላይ የተጣደ ሻይ አለ። ከርሱ አጠገብ ሌላ ምግብ እየበሰለ ነው። ከዚያኛው ክፍል ጡት የፈለገ የህጻን ልጇ ልቅሶ ድምጽ ይሠማል። ሌሎች ልጆች ደግሞ ቁርዓንና ትምህርት እንድታስጠናቸው ከእግሯ ስሮች እየተከተሉ በጥያቄ ያጠድፏታል።

በዚህ ሁኔታ ላይ ነው እንግዲህ  ምግብ አሁን ካልቀረበልኝ በማለት ለመቆጣት መንደርደር የሚጀምረው ለአፍታ ያህል ራሱን ተቆጣጥሮ ምግብ እስኪቀርብለት መጠበቅ አልቻለ፤ ወይም ደግሞ ልጆቹን የማስጠናት ድርሻውን ለጥቂት ግዜያት ያህል እንኳ አልተረከበ ፣ ወይ የሚያለቅሰውን የራሱን ልጅ ሂዶ አላጫወተ ፣ እንዲያው ባለበት ተቀምጦ በዚያው ቅጽበት የጠየኩት ምግብ እንደ “መና” ከሠማይም ወርዶ ቢሆን ካልቀረበልኝ እዚህ ቤት አንድ ዓይነት የመተሳሰብ ችግር አለ ብሎ ይደመድማል ።


ለእርሱ በቅጽበት ምግብ ካልቀረበ ለዛውም በዚያ ሁሉ ወከባ መሀል አንድ ዓይነት የመተሳሰብ ችግር አለ። የሚስቱን ውክቢያ ምንም ከቁም ነገር ሳይቆጥር ምግብ በቅጽበት እንዲቀርብለት መጠየቁ ሳያንስ ለሚስቱ ምንም ዓይነት የማገዝ መልክት ሳያሳይ እጅና እግሩን አጣጥፎ መቀመጡ ደግሞ የመተሳሰብ ችግር አይደለም ። የሚያስቅም ፤ የሚያስለቅስም ድምዳሜ ነው። ባሎች ከዚህ ዓይነት ባህሪ ራሳቸውን ሊያርቁና በቤትም ከቤት ውጭም የረሱልን ( ሠላምና ሠላት በርሳቸው ላይ ይሁን) የሕይወት ፈለግ ሊተገበሩ ይገባል።

No comments:

Post a Comment