ህፃኑ ከሁለት አመት በፊት ጡት እንዲለቅ ማድረግ ይፈቀዳልን?
ህጻኑ ሁለት አመት
ሳይሞላው ጡት እንዲተው ለማድረግ የተቀመጡ መስፈርች ከተሟሉ ይፈቀዳል።
ጡት እንዲተው መደረጉ ህጻኑን የሚጎዳው ካልሆነ
ጡት እንዲተው የሚደረገው በሁለቱ ወላጆቹ ስምምነት
ከሆነ
«እናቶችም ልጆቻቸውን ሙሉ የኾኑን ሁለት
ዓመታት ያጥቡ፡፡ (ይህም) ማጥባትን መሙላት ለሻ ሰው ነው… (ወላጆቹ) ከሁለቱም በኾነ መዋደድና መመካከር (ልጁን ከጡት) መነጠልን
ቢፈልጉ በሁለቱም ላይ ኃጢኣት የለባቸውም፡፡» [አልበቀራ:233]
ሸይኽ አብዱረህማን አስ’ሰዕዲይ ረሂመሁላህ አንቀጹን
ሲያብራሩ እንዲህ ብለዋል፤ «አባትና እናት ህጻኑ
ሁለት አመት ሳይሞላው ጡት መጥባትን ሊያስተውት ከፈለጉ፤ “ለልጁ ጠቃሚው የትኛው ነው” የሚለው ላይ ሁለቱ ተማክረው ከተስማሙና
ፈቃደኛ ከሆኑ ማስተው ይፈቀድላቸዋል። አንቀጹ በውስጥ ታዋቂነት እንደሚያመለክተው ከሁለቱ የአንዱ ብቻ ፍላጎት ከሆነ ወይም ደግሞ ለልጁ የማይበጅ ከሆነ ጡት
ማስለቀቅ አይፈቀድም» ሳእዲ ተፍሲር ገጽ
104
ተያያዥ ነጥቦች
1. ህጻኑ የጠባው የሰው ወተት መሆን አለበት፦
ሁለት ህጻናት ከአንድ ፍየል ቢጠቡ ወንድማማቾች አይሆኑም፤ በዝምድናም አይተሳሰሩም።
ኢብኑልሙንዚር አል-ኢጅማዕ በተሰኘው መጽሀፋቸው ገጽ 77 ላይ የሊቃውንቶችን አጠቃላይ ስምምነት “ኢጅማዕ” አስተላልፈዋል። በተመሳሳይ
መልኩ ከአንድ የዱቄት ወተት ቢጠቡ ዝምድና አያስከትልም (የሳውዲ ቋሚ የፈትዋ ኮሚቴ ቅጽ 21 ገጽ 18) ምክኒያቱም የማጥባት ወንድምነት አጥቢዋ ሴት በማጥባቷ ምክንያት እናት መሆኗን ተከትሎ የሚከሰት ዝምድና ነው። እናትነት ባልተከሰተበት
ሁኔታ ወንድማማችነት አይከሰትም።
2.ህጻኑ የጠባው
ወተት መሆን አለበት፦
የአጥቢዋ ጡት ወተት
ባይኖረውና ህጻኑ ውሀ ቢጠባ ዝምድናን አያስገኝም (የሳውዲ
ቋሚ የፈትዋ ኮሚቴ ቅጽ 21 ገጽ 15) በተመሳሳይ መልኩ
አንዳንዶች እንደሚያስቡት ደም መለገስ በደም ለጋሽና በደም ተቀባይ መካከል የጥቢ ዝምድና አያስኝም (የሳውዲ ቋሚ የፈትዋ ኮሚቴ
ቅጽ 21 ገጽ 145)
3. ከሟች ሴት ቢጠባ፦
በአንዳንድ የጦርነት ጊዜያት እንደሚከሰተው እናት ህይወቷ ካለፈ በኋላ ህጻኑ ቢጠባ ዝምድና ይከሰታል ወይስ አይከሰትም?
አብዛኞቹ የፊቅህ ጠበብቶች በህይወት መኖር መስፈርት ስላልሆነ እና ወተቱ የሙት ብይን ስለሌለው ዝምድና ይከሰታል የላሉ። ሆኖም
የሻፊዒያ ሊቃውንት ህይወቷ ካለፈ በኋላ ከሀላልና ሀራም ማዕቀፍ ውጭ ስለሆነች ልክ ከእንስሳ መጥባት እንደማያዛምደው ሁሉ አያዛምድም
ይላሉ። (አልሙግኒ 9/198)
4. ወተቱ ግንኙነትን መሰረት ያላደረገ ከሆነ፦
ለምሳሌ ግንኙነት ያላደረገች ድንግል የሆነች ሴት ብታጠባ ሁክሙ ምን ይሆናል? የሀንበሊ መዝሀብ ኡለማዎች፤ ይህ ብዙ
ግዜ የማይከሰት ከመሆኑ ጋር ህጻናትን ለመመገብ የተለመደ መንገድ ስላልሆነ ልክ እንደ ወንድ ለጅ ወተት የሚታይ እንጂ ዝምድናን
ለማስገኘት ከቁብ የሚቆጠር አይደለም ብለዋል (አልሙግኒ 9/206) ሆኖም ብዙሀኑ ኡለማዎች “ጁምሁሮች” ዘንድ ይህ ወተት ዝምድናን
የሚያስገኝና እርም የሚያደርግ ነው። ልጁ የጥቢ ልጇ ነው አባት አይኖረውም። ይህ የተለመደ ባይሆንም ነገር ግን በቁርአን ላይ የምናገኘው
ፈቃድ አጥቢዋ ሴት መሆንዋን እንጂ አግብታ በግንኙነት ምክንያት ጡቷ ወተት የሞላ የሚል መስፈርት የለውም ይላሉ። ኢብኑልሙንዚር
አል-ኢጅማዕ ገጽ 77 ላይ የሊቃውንቶችን አጠቃላይ ስምምነት “ኢጅማዕ” አስተላልፈዋል።
5. አጥቢዋ
ሙስሊም ካልሆነች፦
አይሁድ ወይም ክርስቲያን የሆነች ሴት ብታጠባው
ዝምድና እንደሚገኝ ግልጽ ነው። ሙስሊም ባትሆንም መስፈርቶች በተሟሉበት ሁኔታ ጋብቻም የተከለከለ ባለመሆኑ ማጥባትና ልጅን መንከባከብም
ጋብቻን ተከትሎ የሚፈቀድ ነው። በተመሳሳይ መልኩ ሙስሊም ሴት ሙስሊም ላልሆነ ልጅ ማጥባት ይፈቀድላታል።
(የሳውዲ ቋሚ የፈትዋ ኮሚቴ ቅጽ 21 ገጽ 61)
ሆኖም ከአህለል ኪታብ ሴቶች ጋር የሚፈጸም ጋብቻ
ከሚያስከትላቸው ቤተሰባዊና ማህበራዊ ችግሮች በመነሳት የማይመከር እንደመሆኑ ሙስሊም ካልሆኑ ሰዎች ጋር የጡት ዝምድና መፍጠርም
አይመከርም።
ጡት መጥባት በራሱ የሚያስከትለው የባህሪ ተጽዕኖ
እንዳለ በመግለጽ ኡመር ኢብኑልኸጧብ አይሁድና ክርስቲያኖች ዘንድ ልጆች እንዲጠቡ ማድረግን አስጠንቅቀዋል።
6. ታልቦ ቢጠጣ፦
የጥቢ ትስስር የሚከሰተው፤ ወተቱ ለህጻኑ በምግብነት በማገልገሉ፣ አጥንቱንና ስጋውን በማዳበሩ፣ ረሀብን በማስታገሱ ነው።
ወተቱ ታልቦ በእቃ ወይም በጡጦ እንዲወስደው ቢደረግ ይህ ሁሉ ጥቅም ይገኛል። ስለዚህም ከማጥባት ውጭ ባለ ማንኛውም መንገድ ወተቱ
ወደ ሆዱ እንዲደርስ ቢደረግ እንደ ጥቢ ይቆጠራል። አምስት ግዜ ከተደገመ የጥቢ ዝምድናን ያስገኛል። ይህ የብዙሀኑ የፊቅህ ሊቃውንት
(ጁምሁር) አቋም ነው። (አልሙግኒሊብን ቁዳማህ 8/ 139 ፤ አልካፊ
ሊብን ቁዳማህ 5/65 ፤ የሳውዲ ቋሚ የፈትዋ ኮሚቴ ቅጽ 21 ገጽ 12)
7.ከሌላ
ነገር ጋር ተቀላቅሎ ቢጠጣ፦
በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው ሚዛን ደፊ አቋም ወተቱ
ከሌላ ነገር ጋር ቢቀላቀልም በፐርሰንት ሲታይ ብዙ ሆኖ ከተገኘ መዛመድን ያስከትላል የሚለው ነው። ከሀነፊ መዝሀብ ኡለማዎች የአቡ
ዩሱፍ እና የሙሀመድ ቢን ሀሰን አቋም ሲሆን፤ የማሊኪያ የሻፊዒያና የሀንብሊያ መዝሀቦች ሁሉ አቋም ነው። (በዳኢዑ ሰናዒዕ
4/9 ፤ ሙግኒል ሙህታጅ 3/410 ፤ አልሙግኒ 9/197 ፤ አል ኢንሷፍ 9/337 ፤ ከሻፉል ቂናዕ 5/447)
ሸይኽ ኡሰይሚን ህጻኑ ከመድሀኒት ጋር ተቀላቅሎ
ቢሰጠው ወተቱ ወደ ሆዱ የሚደርስና ተጽእኖ የሚፈጥር ከሆነ እንደ
ጥቢ ይታያል ብለዋል (ኑሩን አለደርብ ቅጽ 3 ገጽ 1867)
8.እርግጠኝነትና ጥንቃቄ፡-
የጥቢ ዝምድናን ለማጽደቅ እርግጠኝነት ያስፈልጋል። የማጥባት ዝምድና ከጋብቻ የሚከለክል ዝምድና የሚፈጠረበት ትስስር
ነውና ሳያረጋግጡ በቸልታ ዝምድናን ማወጅ ተገቢ አይሆንም። ከእናታችን ዓኢሻ በተላለፈ ሀዲስ የአላህ መልዕክተኛ እቤት ሲገቡ አንድ ሰው እቤት ነበርና “ይህ ሰው ማነው?” በማለት
ጠየቁኝ፤ የጥቢ ወንድሜ ነው አልኳቸው። እርሳቸውም “አዒሻ ሆይ! ወንድሞቻችሁ እነማን መሆናቸውን አስተውሉ። የጥቢ መዛመድ የሚከሰተው
በረሀብ ሲሆን ነው” አሉ። ሀዲሱን ቡኻሪ በቁጥር 2453 ሙስሊም በቁጥር 1455 ዘግበውታል
ታላቁ የቡኻሪ ተንታኝ ኢብኑ ሀጀር እንዲህ ብለዋል፤
«የዚህ ትርጉም፤ ምን እንደተከሰተ አስተዉሉ፤ ከጠባበት ግዜ እና ከጠባው የወተት መጠን አንጻር መስፈርቶቹን ያሟላ ጥቢ
ነውን? የጥቢ ዝምድና የሚኖረውና ተጽዕኖ የሚያሳድረው መስፈርትቹ ሲሟሉ ነው። ሙሀለብ እንዳሉት፤ የዚህ ወንድማማችነትን ምክንያትመለስ
ብላችሁ ቃኙ፤ ጥቢ እርም የሚያደርገው መጥባት ረሀብን በሚያጠፋበት የህጻንነት እድሜ ነው…ጥቢ ከረሀብ የሚያላቅቅ ካልሆነ ቦታ አይሰጠውም
እንደማለት ነው!» ፈትሁልባሪ ቅጽ 9 / ገጽ 148
በተመሳሳይ መልኩ ለጉዳዩ ቁብ አለመስጠትና ልጆችን በጋራ ማጥባት ትልቅ ስህተት ነው። በአንዳንድ የህክምና ተቋማትም
የእናት ጡት ታልቦ ሲገባ የመቀላቀል አደጋ እንዳይደርስበት ማስጠንቀቅና መከታተል ያስፈልጋል። ሙስሊም ሴት አንድን ህጻን ማጥባት
ስትፈልግ እርሱንም የሚያዛምድ ተግባር ስለሆነ ከባለቤቷ ጋር መማከሯ ግዴታ ነው። በጥቅሉ የሌላ ሰውን ልጅ ከማጥባት በፊት አስፈላጊነቱን
እና ተጽዕኖዎቹን ማስተዋል ግድ ይለናል።
No comments:
Post a Comment