Sunday, 19 February 2017

የበሽታ ደም

የበሽታ ደም

     የወር አበባን ጊዜ የማይጠብቅ ከደም ስር መበጠስ የሚፈስ ደም ሲሆን ከወር አበባ ጋር በአይነትም ሆነ በሸሪዓዊ ብይናቸው ይለያያሉ፡፡
     ይህ ደም በመፍሰሱ ጠሃራ ከመሆኗ የማትወገድ በመሆኗ ሰላት ፆምም ሆነ ህጋዊ ግብረ ስጋ ግንኙነት መፈፀም አትከለከልም፡፡ ለዚህ ማስረጃው ፋጢማ ቢንት አቢጀህሽ ያስተላለፉት ሀዲስ ነው፡፡ “የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! እኔ የወር አበባ ደም ሳያቋርጥ ይፈሰኛልና ሰላት መተው አለብኝ? በማለት ስትጠይቃቸው እንዲህ በማለት መለሱላት “አይ ይህማ የወር አበባ ሳይሆን የተበጠሰ የደም ስር ነው የተለመደው የወር አበባሽ ሲመጣ ሰላት አቁሚና ሲሄድ ደምሽን አጥበሽ ስገጅ፡፡” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

የተለመደው የወር አበባ ጊዜዋ ሲያበቃ ገላዋን መታጠብ ግዴታዋ ሲሆን ለበሽታ ደሙ ደግሞ ሀፍረተ ገላዋን አጥባ የደም መውጫውን እንደ ጥጥ መሰል ነገር በመጠቀም አሽጋ ደም እንዳይፈስ ማድረግ አለባት፡፡ ወቅታዊ የሆነውን “ሞዴስ” ብትጠቀምም የተሻለ ነው፡፡ ከዚያ ለእያንዳንድ የሰላት ወቅት ውዱእ እያደረገች ትሰግዳለች፡፡

 የበሽታ ደም የምታይ ሴት ሶስት አይነት ሁኔታዎች ይኖራታል፡-

አንደኛ፦

የወር አበባ መምጫ ጊዜዋ እርሷ ዘንድ የታወቀ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ከሆነ በተለመደው ጊዜ የሚመጣውን ደም የወር አበባ አድርጋ ትቆጥረውና ሰላትና ፆምን ታቆማለች ይህ ጊዜዋ ሲያበቃ ደግሞ ታጥባ ትሰግዳለች፡፡ ከዚህ ውጪ ያለውን ደም እንደ በሽታ ደም ትቆጥራለች፡፡ ለዚህ ማሰረጃው ነብዩ () ለኡሚ ሀቢባ እንዲህ በማለት የተናገሩት ሀዲስ ነው “የወር አበባሽ የሚቆይብሽን ጊዜ ያህል ሳትሰግጂ ቆይና ከዚያ ታጥበሽ ስገጅ፡፡” (ሙስሊም ዘግበውታል)

ሁለተኛ፦

የተለመደ ጊዜ ከሌላትና ነገር ግን የወር አበባዋን ከበሽታ ደም የምትለይ ከሆነ ለምሳሌ የወር አበባዋ ጥቁር ወፍራም ሽታ ያለው ሆኖ የወር አበባን ባህሪ የያዘ ከሆነና የበሽታ ደሟ ደግሞ ቀይ ቀጭን ሽታ የሌለው ሆኖ የሌሎችን ደም ባህሪ የያዘ ከሆነ እንዲህ አይነቷ ሴት ሁለቱን በመለየት ትጓዛለች፡፡ ለዚህ ማስረጃው ነብዩ  () ለፋጢማ ቢንት አቢ ሁበይሽ እንዲህ ያሏት ነው “ የወር አበባ ደም ከሆነ ጥቁር ሽታ ያለው ነው ይሄኔ ሰላት ከመስገድ  ተቆጠቢ ከዚህ ውጭ ከሆነ ግን ውዱእ አድርገሽ ስገጅ ምክንያቱም ይህ ከደም ስር መበጠስ የሚመነጭ ነው፡፡” (አቡዳውድና ሃኪም ዘግበውታል)

ሶስተኛ፦ 

የተለመደ ጊዜ ከሌላትና ደሞችንም መለያ ከሌላት የአብዛኞች ሴቶችን ተለምዶ በመውሰድ ስድስት ወይም ሰባት ቀናት ሰላትና ፆምን ታቆምና ከዚያ ታጥባ ሰላተና ፆሟን ትቀጥላለች፡፡ ለዚህም ማስረጃው ነብዩ () ለሀምና ቢንት ጀህሽ እንዲህ ያሏት ነው “ይህ የሸይጧን እርግጫ ነው የወር አበባሽን ስድስት ወይም ሰባት ቀናት አድረጊውና ከዚያ ስትፀጂ ሰላትና ፆምሽን ቀጥይ ይህ ለአንቺ በቂ ነው፡፡”                              

 (አቡዳውድና ቲርሚዚይ ዘግበውታል)

No comments:

Post a Comment