Sunday, 19 February 2017

ብቀላ ወይስ ምህረት…?

                                                  ብቀላ ወይስ ምህረት…?

   ኢስላም  ስንሰጥም ሆነ ስንነሳ ለአላህ ብቻ እንዲሆን ይፈልግብናል። ይህ ስሜትን ማስደሰትን መሰረት ያደረገ ሳይሆን አላህን መታዘዝን ብቻ ኢላማ ያደረገ ነው። መልካም ለዋለልን መልካምን መዋል ልንመጻደቅበት የሚገባን ነገር ሳይሆን  እርሱ በኛ ላይ ያለው ሀቅ ነዉና ተገቢ ነው። መልካም ለማይዉል ሰው መልካም መዋል ግን ከባድ ጀግንነት የሚጠይቅ በመሆኑ አላህ እንዲህ አይነቱን ግንኙነት በመልካም እንድንቀጥል አዞናል። እራሱን አሸንፎ ለበደለው ይቅር የሚል ሰው በዱንያም ይሁን በአኼራ አላህ ደረጃውን ከፍ ያደርገዋል፤  ስሜቱን፣ ቁጭቱን አሸንፏል እና ድልን ያቀዳጀዋል።

قال رَسُولِ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم : ( وَمَا زَادَ اللَّهُ عَبْداً بِعَفْوٍ إِلاَّ عِزّاً ) رواه مسلم من حديث أَبِى هُرَيْرَةَ رضي الله عنه

የአላህ መልዕክተኛ እንዲህ ብለዋል፤ “አንድ ባሪያ ይቅር በማለቱ አላህ አሸናፊነትን እንጂ አይጨምርለትም” ሙስሊም ዘግበዉታል

ይቅርታ ለሚል ሰው አላህ ታላላቅ ሽልማቶችን ቃል ገብቶለታል። አላህ እንዲህ ብሏል፤

 ( وَسَارِعُوا إِلَىٰ مَغْفِرَةٍ مِّن رَّبِّكُمْ وَجَنَّةٍ عَرْضُهَا السَّمَاوَاتُ وَالْأَرْضُ أُعِدَّتْ لِلْمُتَّقِينَ * الَّذِينَ يُنفِقُونَ فِي السَّرَّاءِ وَالضَّرَّاءِ وَالْكَاظِمِينَ الْغَيْظَ وَالْعَافِينَ عَنِ النَّاسِ ۗ وَاللَّهُ يُحِبُّ الْمُحْسِنِينَ ) آل عمران/ 133،134

(ከጌታችሁ ወደ ኾነችም ምሕረትና ስፋትዋ እንደ ሰማያትና ምድር ወደ ሆነች ገነት፥ አላህን ለሚፈሩ የተዘጋጀች ስትሆን ተቻኮሉ። ለነዚያ፤ በድሎትም ኾነ በችግር ለሚለግሱት፥ ቁጭትንም ገቺዎች፥ ከሰዎችም ይቅርታ አድራጊዎች ለሆኑት (ተደግሳለች)፤ አላህም በጐ ሠሪዎችን ይወዳል።) አል ዒምራን 133 - 134

መረጃዎችን ስናጤን ይቀር ባይነትን የሚያበረታቱ ሆነው እናገኛቸዋለን። ስለዚህም ኡለማዎች በቀልን ከማይወደዱ ባህሪያት ይመድቡታል። ይሁንና ሰዎች ይለያያሉ፤ አንዳንዱ በቀልን መፈጸም ቁጭቱን መወጣቱ አይቀርምና ይህ ተግባር ገደብ ባለው ሁኔታ ተፈቅዶ እናገኛለን። ተበዳይ ሀቁን የማስመለስ ብሎም የደረሰበትን በደል የመበቀል ጉዳይ እንደ መብት ቢፈቀድም ይህ እርምጃ ግን ብዙ ገደቦች  ያሉበት እና አስቸጋሪ ነው።  በደልን በከፋ በደል መመለስ ፍጹም የተከለከለ ነው። ወሰን ሳያልፉ መበቀልም እጅግ አስቸጋሪ ነው። ይህ ጠንቃቃነትን የሚሻ በመሆኑ ብዙዉን ጊዜ አይሳካም። በመሆኑም ተበዳይ ዞሮ በዳይ ይሆናል። ስለዚህም ይህ ርዕስ በቁርዓን ዉስጥ ባብዘኛው ከይቅር ባይነት ጋር ተያይዞ እናገኘዋለን። አላህ እንዲህ ብሏል፤

فقال الله تعالى : (وَإِنْ عَاقَبْتُمْ فَعَاقِبُوا بِمِثْلِ مَا عُوقِبْتُم بِهِ ۖ وَلَئِن صَبَرْتُمْ لَهُوَ خَيْرٌ لِّلصَّابِرِينَ) النحل 126

 (ብትበቀሉም፣ በርሱ በተቀጣችሁበት ብጤ ተበቀሉ፤ ብትታገሡም፣ እርሱ ለታጋሾች በእርግጥ በላጭ ነው።) አነህል 126

قال تعالى:(فَمَنِ اعْتَدَىٰ عَلَيْكُمْ فَاعْتَدُوا عَلَيْهِ بِمِثْلِ مَا اعْتَدَىٰ عَلَيْكُمْ ۚ وَاتَّقُوا اللَّهَ وَاعْلَمُوا أَنَّ اللَّهَ مَعَ الْمُتَّقِينَ  ) البقرة: 194

(በእናንተም ላይ (በተከበረው ወር) ወሰን ያለፈባችሁን ሰው በናንተ ላይ ወሰን ባለፈው ብጤ በርሱ ላይ ወሰን እለፉበት፡፡ አላህንም ፍሩ አላህ ከሚፈሩት ጋር መኾኑንም ዕወቁ፡፡) አል  በቀራህ 194

قال تعالى: وَجَزَاءُ سَيِّئَةٍ سَيِّئَةٌ مِّثْلُهَا ۖ فَمَنْ عَفَا وَأَصْلَحَ فَأَجْرُهُ عَلَى اللَّهِ ۚ إِنَّهُ لَا يُحِبُّ الظَّالِمِينَ ) الشُّورى: 40 

(የመጥፎም ነገር ዋጋ ብጤዋ መጥፎ ናት፤ ይቅርም ያለና ያሳመረ ሰው ምንዳው በአላህ ላይ ነው። እርሱ በደለኞችን አይወድም። ) ሹራ 40

ይህ ከመሆኑ ጋር፤ የበዳይን ሰው ጥፋት ይቅር ማለት ከመበቀል የተሻለ መሆኑን በዛው አንቀጽ ላይ ተናግሮአል። (ይቅርም ያለና ያሳመረ ሰው ምንዳው በአላህ ላይ ነው።) ጠንካራነት እና ጀግንነት የሚለካዉም መጉዳት እየቻሉ ለአላህ ሲሉ በመተው ይቅርታ ማድረግ ላይ ነዉና አላህ እጅግ ከባድ ምንዳን አዘጋጅቶለታል።

ይህ በግለሰቦች መካከል እንደሚከሰቱ ጠቦች፣ መጎዳዳቶች እና መሰል ድንበር ማለፎችን  የሚመለከት ነው።  በቀል ለሁሉም በደሎች አይፈቀድም፤ አንዳንዱ ጉዳይ ለፍርድ የሚቀርብ እንጅ እራሱ ማስፈጸም የማይፈቀድለት ነው። እንደዚሁ፤ ከበቀል ምህረት የሚቀደመው መልካም ሆኑ ሲገኝ ብቻ ነው። ድንበር ማለፉ የተከሰተው በአላህ ሀቅ ላይ ከሆነ ወንጀል እንዲፈጸም መፍቀድን ይቅር ባይነት አድርጎ መቁጠር ተገቢ አይደለም።

ለምሳሌ፤ ተደጋጋሚ ጾታዊ ጥቃቶች የሚደርሱባት ሴት ይቀር ማለት የሻላል ብላ ወንጀሎች እንዲደጋገሙ መንገድ ከከፈተች ትክክል አይሆንም። የትዳር ጓደኛውን ቢያማግጥበት ወይም ፍርደ ገምድልነትን ቢያሳይ፤ የእሱን ባለቤት ለማማገጥ በመሞከር ወይም ፍትህን በማጓደል  መበቀል ፍጹም የተከለከለ ነው። (ወሰን ባለፈው ብጤ በርሱ ላይ ወሰን እለፉበት) የተባለው ወንጀል መፈጸምን አያካትትም ማለት ነው።

ነገር ግን የተበደለው ግላዊ በደል ከሆነ ይቅር ማለት እና መማር ተገቢና የተሻለ ነው።
فعن عائشة -رضي الله عنها- أنَّها قالت
)وما انتقم رسول الله صلى الله عليه وسلم لنفسه   (رواه البخاري ومسلم

እናታችን  አዒሻ  ቡኻሪና ሙስሊም በዘገቡት  ሀዲስ እንዲህ ብለዋል፡ (የአላህ መልዕክተኛ ለራሳቸው ሲሉ መቼም ቢሆን ተበቅለው አያውቁም...)
ታላቁ የቁርዓን ሙፈሲር አል ኢማም አልቁርጡቢ እንዲህ ብለዋል

“(የመጥፎም ነገር ዋጋ ብጤዋ መጥፎ ናት፤)ሹራ 40 ኡለማዎች እንዲህ ብለዋል፤ አላህ ምዕመናንን ሁለት አይነት አድርጓቸዋል።
ከፊሎቹ በደልን ይቀር የሚሉ ሲሆኑ ከአንቀጹ ቀደም ብሎ 37ኛ አንቀጽ
 
وَإِذَا مَا غَضِبُوا هُمْ يَغْفِرُونَ

(በተቆጡም ጊዜ እነሱ የሚምሩ ለሆኑት።) ሹራ 37 በማለት እነሱን አውስቶ ጉዳዩን ጀምሮታል። ከፊሎቹ ደግሞ በደልን የሚበቀሉ ናቸው። አስከትሎ የመበቀልን ወሰን ገለጸ። ወሰን ማለፍ እንደማይገባ ተናገረ።” አልጃሚዕ ሊአህካሚል ቁርዓን

አላህ የበደልን ወሰን ከገለጸበት አንቀጽ በፊት 39ኛው አንቀጽ በፊት የምዕመናን በደልን መመለስን መግለጹ በቀልን የሚያበረታታ አይደለም። ምክኒያቱም፤ በቀጣዩ አንቀጽ የተሻለዉና በላጩ ምህረት ማድረግ መሆኑ ከመገለጹም ባሻገር፤ ቀጣዩ አንቀጽ ላይ የተገለሰውን አፈጻጸም ሚተገብሩትን ነው። 
  ኢብኑ ረጀብ እንዲህ ብለዋል፤ “አላህ
وَالَّذِينَ إِذَا أَصَابَهُمُ الْبَغْيُ هُمْ يَنتَصِرُونَ الشُّورى: 39
(ለነዚያም በደል በደረሰባቸው ጊዜ እነሱ (በመሰሉ)የሚመልሱ ለሆኑት (በላጭና ኗሪ ነው)።) ሹራ 39

 “ይህ ይቀር ከማለት ጋር የሚጋጭ አይደለም። በደልን መመለስ መቻልን በማሳየት መጀመሪያው በደልን የሚመልሱ ሲሆን መበቀል እንደሚችሉ አሳይተው ይቅርታ ማድረግን ማስከተላቸው የተሟላና የተሻለ ያደርገዋል።” ጃሚዑል  ዑሉም ወልሂከም 1/450
ምንም እንኳን ሰዎች በሚደርስባቸው በደል ምክኒያት ለበቀል ቢነሳሱም ለጥፋት ከሚዳርጓቸው ነገሮች መካከል መናደድ፣ ስሜታዊነት፣ በቀልን እንደ ዝና እና ጀግንነት መቁጠር፣ ትዕግስት እና ይቅር ባይነትን እንደ ባህሪ አለመላበስ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

 ከላይ መግቢያዬ ላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት፤ ይቅር ባይነት ከአላህ ከፍተኛ ምንዳን የሚያስገኝ መልካም ባህሪ ነውና በብቀላ ቁጭትን ከመወጣት ብሎም ድንበር በማለፍ ጸጸት ዉስጥ ከመዉደቅ ከአላህ የሚያገኘውን ምንዳ በማሰብ በቀልን መራቅ ብልህነት ነው።



No comments:

Post a Comment