Tuesday, 21 February 2017

ለአዋቂ ልጅ ማጥባት

ለአዋቂ ልጅ ማጥባት
  
ከላይ እንደተብራራው የብዙሀኑ የፊቅህ ለቃውንት (ጁምሁር) አቋም የጥቢ ዝምድና ሁለት አመት ያለፈው ልጅ በማጥባት አይከሰትም የሚለው ነው። ሁለት አመት ያለፈው ህጻን ቢጠባ የጥቢ ዝምድናን ካላስገኘ አዋቂ ሰው ቢጠባ ፍጹም እርም ሊያደርግ አይችልም።በዚህ ጉዳይ ላይ ከምዕመናን እናት ኡሙ ሰለማ የተላለፈውን ተከታዩን ግልጽ ሀዲስ እናገኛለን፤

«እርም የሚያደርገው መጥባት አንጀት የደረሰ እና በጥቢ ዘመን ጡት ከመልቀቅ በፊት የተፈጸመ ነው» ሀዲሱን ቲርሚዚይ እና ኢብኑ ማጃህ ዘግበውታል አልባኒም በሶሂህ አቲርሚዚይ የትክክለኛ ሀዲሶች ጥንቅር ውስጥ አካተውታል። ሀዲሱን የዘገቡት አል ኢማም አቲርሚዚይ ረሂመሁላህ እንዲህ ብለዋል፤ «ይህ ትክክለኛ ሀዲስ ሲሆን ደረጃው (ሀሰኑን ሰሂህ) ነው። “እርም የሚያደርገው መጥባት ከሁለት አመት በፊት ከሆነ ብቻ ነው” የሚለው የሰሀቦችና ከእነሱም በኃላ የመጡት ታላላቅ ኡለማዎች ሁሉ አቋም ነው። ህፃኑ ሁለት አመት ከሞላው በኋላ የተከሰተ ማጥባት ምንንም እርም አያደርግም» ቱህፈቱል አህወዚይ ቅጽ 4 ገጽ 264

በተመሳሳይ ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ ለዓኢሻ «የጥቢ መዛመድ የሚከሰተው በረሀብ (ረሀብን የሚጋታ) ሲሆን ነው» ያሉትም ግልጽ መረጃ መሆኑ ተገልጿል። ሀዲሱን ቡኻሪ በቁጥር 2453 ሙስሊም በቁጥር 1455 ዘግበውታል

በዚህ ጉዳይ ላይ የብዙሀኑን አቋም የተጻረሩ ኡለማዎች መሰረት ያደረጉባቸው መረጃዎችም ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል። በመጀመሪያ ደረጃ አንቀጹ ላይ «አነዚያ ጡት ያጠቧችሁ እናቶቻችሁ፣ የጥቢ እህቶቻችሁም...» ኒሳዕ 23 ሲል “እድሜያችሁ ከሁለት አመት በታች እያለ” የሚል ገደብ አላስቀመጠም የሚል መከራከሪያ ነጥብ ያነሳሉ። በመሰረቱ ማጥባት የሚባለው ህጻን ልጅን የሚመግብ እና ጡት ከመልቀቅ በፊት ያለው መሆኑ በተለምዶ የታወቀ ከመሆኑ ባሻገር የኡሙ ሱለይም ሀዲስም በግልጽ ያስቀመጠው እውነታ ነውና ይህ መረጃ ሊሆናቸው አይችልም። በዋነኝነት የሚያነሱት መረጃ ግን፤ ቅድመ ኢስላም ይሰራበት በነበረውና ኋላ በሱረቱል አህዛብ አንቀጽ 5 በተከለከለው የማደጎ ልጅን እውነተኛ ልጅ የማድረግ ልማድ ሳሊምን ያሳደጉት አቡሁዘይፋና ባለቤቱ አብረውት በአንድ ክፍል ይኖሩ ስለነበር እና ልጁ ለአቅመአዳም ከደረሰ በኋላ በመቸገራቸው የአላህ መልዕክተኛ የሰጡትን መፍትሄ ነው። ሆኖም እነሱም ቢሆኑ ሀዲሱ እንደሚመለከተው ሰሀቢይ እንደ ሳሊም አይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ኖረው አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ (ለሀጃ) የሚፈፀም ብለው ገደብ አድርገውበታል። አል ኢማም አጦበሪ ይህንን አቋም ከደገፉት መካከል፤ አብዱላህ ኢብኑዙበይር፣ አልቃሲም ኢብኑ ሙሀመድን ጠቅሰዋል። አጧዕ፣ለይስ ኢብኑ ሳዕድ፣ ኢብኑ ሀዝም እና ዳውድ አዟሂሪይ አቋሙን እንደሚጋሩ ይነገራል። (ፈትሁልባሪ 9/147)  

ያቀረቡት መረጃ እንደሚከተለው ይነበባል፤

(የአቡሁዘይፋ ባለቤት ሰህላ ቢንት ሱሀይል መልእክተኛው ዘንድ መጥታ ሳሊምን ህጻን አድርገን እንቆጥረው ስለነበር ከኔና ከአቡሁዘይፋ ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ ያድር ነበር። ያየኛልም፤ አሁን አላህ የቁርአን አንቀጽ አውርዷልና (አህዛብ 5) ምን ይመክሩኛል? በማለት ጠየቀች። የአላህ መልዕክተኛም፦ “አጥቢው” አሏትና አምስት ግዜ አጠባችው። ከዚያን ግዜ በኋላ ልክ እንደ ልጇ ሆነ…)
አቡዳውድ (2061) ነሳኢ (3324) እና ሌሎችም ዘንድ ተዘግቧል

ሀዲሱ በምን መልኩ ሳሊም እንደጠባ አይገልጽም። ሆኖም የሀዲስ ተንታኙ አል ኢማም አን’ነወዊይ እንዲህ ብለዋል፤ «“አጥቢው” የሚለውን አስመልክቶ አልቃዲ ኢያድ እንዳሉት “ሰውነቷን ሳይነካ ታልቦ ጠጥቶት ነው የሚሆነው” ይህ ጥሩ ትንታኔ ነው። ነገር ግን ተልቅ ሆኖ እንዲጠባ በልዩ መልኩ እንደተፈቀደለት ሁሉ ይህም ለሀጃ ተፈቅዶለት ሊሆን ይችላል አላህ ያውቃል» ብለዋል። በተለይ ደግሞ ሳሊም የማደጎ ልጇ እንደመሆኑ ልክ እንደልጇ የምታየውና እሱም እንደ እናቱ የሚያያት ከመሆኑ አንጻር ነገሩ ቀለል ያለ ነው።

ሀዲሱ ሲጠናቀቅ የምዕመናን እናቶች ቢቃወሟትም ዓኢሻ ግን ይህንን የሳሊም ክስተት መረጃ በማድረግ ለተመሳሳይ ሀጃ መጠቀም እንደሚቻል አቋሟን ትገልጽ ነበር። ከዘይነብ ቢንት ኡሙ ሰለማ በተዘገበ ሀዲስ አዒሻን ስትጠይቃት ሳሊም ያገኘውን ፍቃድ በመጥቀስ መልሳለች (ሙስሊም ቁጥር 1453)
 
ብዙሀኑ ከልካይ ኡለማዎች ምላሽ፦

ይህ የሳሊም ሀዲስ እሱን ብቻ የተመለከተ ነው የሚለው የምእመናን እናቶች ምላሽ እንዳለ ሆኖ። ሀዲሱና ብይኑ በሌሎቹ ህጻን መሆንን መስፈርት በሚያደርጉ ሀዲሶች የተሻረ (ነስኽ የተደረገ) ነው የሚለውም ምላሻቸው ነው።

በርግጥ ይህንን የሳሊምን ክስተት ለተመሳሳይ ሀጃ መጠቀም የአዒሻ የግል ግንዛቤና አቋም ነበር። ሆኖም ግን በሌሎቹ የምእመናን እናቶች ዘንድ ተቀባይነት እንዳልንነበረው የሚያመላክቱ ብዙ መረጃዎች አሉ።

ከምእመናን እናት ከኡሙ ስለማ በተዘገበ ሀዲስ «ሌሎች የመልእክተኛው ባለቤቶች ማንም ሰው (በልጅነቱ) ካልጠባ በቀር በዚህ አይነት ጥቢ እነሱ ዘንድ እንዲገባም ሆነ እንዲመለከታቸው አልፈቀዱም። ለዓኢሻም “ለሳሊም በልዩ ሁኔታ የፈቀዱት “ኻስ” ፈቃድ ነው ብልን እናምናለን ሲሉ አስረድተዋታል።» ሙስሊም በቁጥር 1454 ዘግበውታል

የትልቅ ሠው መጥባት ወጤት እንደሌለው የሚገልጹ የሰለፎች አስተምህሮቶች ይገኛሉ።

1. ከዓጧዕ አልዋዲዒይ በተላለፈ መልዕክት፤ “አንድ ሰው ኢብኑ መስዑድ ዘንድ መጣና፤ የባለቤቴ ጡት ወተት ይዞ ተወጠረና እየጠባው ተፋሁት እንም አባሙሳ ዘንድ ሄጄ ስጠይቀው፤ ሀራም ሆናብሀለች አለኝ” ሲለው ኢብኑ መስዑድ ተነሳ እኛም ተከተልነውና አቡሙሳ ዘንድ ሄደ፤ ከዛም ለዚህ ሰው ምን አይነት ፈትዋ ነው የሰጠኸው? በማለት ጠየቀውና ምላሹን ሲነግረው፤ የጠያቂውን እጅ በመያዝ “አሁን ይህ ሰው ጡት የሚጠባ ነውን? ጥቢ ማለት በሰውነት ውስጥ ስጋና ደምን የሚሰራ ነው። አቡሙሳም ይህ አዋቂ ሰው በመካከላችን እያለ እኔን አትጠይቁ በማለት ተናገረ። (አብዱረዛቅ ሙሶነፍ ቅጽ 7 ገጽ 463 ላይ ጠቅሰውታል)  በሌላ አገላለጽ አቡዳዉድ በቁጥር 2059 ዘግበውታል «አጥንትን ያጎለበተና ስጋን ያበቀለ እንጂ ጥቢ አይባልም በማለት ሲመልስ፤ አቡ ሙሳ “ይህ አዋቂ ሰው በመካከላችሁ እያለ እኔን አትጠይቁኝ አለ» ሶሂህ አቡዳውድ ላይ አልባኒ ሶሂህ ብለውታል

2.ማሊክ ከናፊዕ ባስተላለፉት ሀዲስ ኢብኑ ኡመር እንዲህ ብለዋል፤ «በህጻንነቱ ካልጠባ ሰው ጋር የጥቢ ዝምድና የለም። ትልቅ ሰው የጥቢ ዘመድ አይሆንም» አል ሙወጠእ 2/603

3. ማሊክ ሙወጠእ ላይ ሶሂህ በሆነ ዘገባ አብዲላህ ኢብኑ ዲናር ከአብዱላህ ኢብኑ ኡመር አባቱ ኡመር እንዲህ ማለቱን ዘግበዋል፤ «ጥቢ ማለት የህጻንነት መጥባት ነው!» አልሙወጠእ 2/606


ብዙ ኡለማዎች ዘንድ ፈትዋ የሚሰጥበት አቋም ትልቅ ሰው ቢጠባ ዝምድናን አያስገኝም ከጋብቻም አይከለክልም። የሳሊም ሃዲስም እርሱን ብቻ የተመለከተ ነው የሚለው ነው። ከዘመናችን ኡለማዎች ኢብኑ ባዝ፣ ልጅነቱዳኢማህ ይህንኑ ምላሽ ይሰጣሉ። መጅሙዕ ፈታዋ ሊብን ባዝ 22/264 ላይ ፈታዋለጅናህ 21/41 ይመልከቱ። አንዳንዶች ደግሞ ሀዲሶቹን ሁሉንም ተግባራዊ ያደረገ ሀሳብ ያቀርባሉ።

አል ኢማም አሶንዓኒይ እንዲህ ብለዋል፤ «የሰህላህ ሀዲስን እና ለሎቹን ሀዲሶች ከማስታረቅ አንጻር ጥሩ የሚባለው የኢብኑ ተይሚያህ ንግግር ነው። ኢብኑ ተይሚያህ “ህጻን ሆኖ መጥባት ተቀባይነት ያለው መስፈርት ነው። ሆኖም ልክ ሳሊም ከአቡሁዘይፋ ባለቤት ጋር እንደነበረው ሁኔታ ቤት ውስጥ መገኘቱ የግድ ሆኖ ሳለ፤ ለሴቶች ለመከለል አስቸጋሪ ሲሆን ረዷዓ ቢጠቀም የዝምድና ተጽዕኖ ይፈጥራል” ብለዋል። በሳሊም ብቻ ከመገደብ ወይም ተሽሯል ብሎ መልስ ከመስጠት ቋንቋዊ መርሆዎችንም ጥቅም ላይ ከማዋል አንጻር ይህ ንግግራቸው ጥሩ ማስታረቂያ ነው። እነዚህኑ ምክኒያቶች በመጥቀስ የማስታረቂያውን ሀሳብ ተማሪያቸው ኢብኑል ቀዩም ዛዱልመዓድ ላይደግፈውታል» ሱቡሉሰላም ቅጽ 2 ገጽ 313

እንዲህ አይነት ሁኔታዎችን በማገናዘብ የሳውዲ ቋሚ የፈትዋ ኮሚቴ ቅጽ 21 ገጽ 40 እና 46 ላይ የሶስት እና የስምንት ወይም የዘጠኝ አመት ልጆች በመጥባታቸው ዝምድናን አጽድቀዋል።

ሸይኽ ኢብኑ ኡሰይሚን የሳሊም ሀዲስ እሱን ብቻ የተመለከተ አይደለም የሚለውን አቋም ቢመርጡም

« እኔ ዘንድ የትልቅ ልጅ ጥቢ ተጽዕኖ አይፈጥርም። በሁሉም ሁኔታ ልክ እንደ ሳሊምና አቡሁዘይፋ  አይነት ሁኔታ ብቻ ሲሆን ነው ተጽዕኖ የሚፈጥረው። አላህ የማደጎ ልጅ መያዝን ስለከለከለ የሳሊም አይነት ሁኔታ ላይ ያለ ሰው አይኖርምና አሁን ሀዲሱን መተግበር የማጥባት ዝምድናን አይፈጥርም።ሴትንም ክልክል አያደርግም። ከሁለት አመቱ በፊት እንደውም ጡት ሳይለቅ ከጠባ ብቻ ነው የሚለው አቋም ሚዛን ይደፋል… ከዚህ አንጻር ስናየው ይህ አቋም ከአብዛኛው ኡለሞች አቋም ጋር ይታረቃል በማለት ሃሳባቸውን አስቀምጠዋል። (ሸርሁል ሙምቲዕ ቅጽ 13 ገጽ 435 እና 436)

ይህ የጥቢን ህግጋት በተመለከተ አስፈላጊ ያልኳቸውን ነጥቦች የዳሰስኩበት ጽሁፍ ሲሆን አላህ እውቀትን እና መልካም ስራን ይለግሰን ዘንድ እለምነዋለሁ።

አቡጁነይድ ሳላህ አህመድ

ጥር 16/2009

No comments:

Post a Comment