Tuesday, 21 February 2017

የትዳር የመጀመሪያ ወራቶች!

የትዳር የመጀመሪያ ወራቶች!
   
የትዳር የመጀመሪያ ዓመት አዲስ የህይወት  ምዕራፍ  መክፈቻ እንደመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይፈልጋል። በዚህ ወቅት የሚያጋጥሙ የቤት ውስጥ ፈተናዎችን ለመወጣት ባልና ሚስት ከባድ ኃላፊነቶች ይወድቅባቸዋል።

      የመጀመሪያ ዓመቱን  በሠላም ማጠናቀቅ የቻለ ትዳር ቀጣይ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው። በርካታ ፍቺዎች በትዳር የመጀመሪያ ዓመት እንደሚፈጽሙ የሚጠቁሙ ጥናቶች አሉ። ከዚህ ለመዳን በትዳር የመጀመሪያ ዓመት ሊወሰዱ ስለሚገቡ ጥንቃቄዎች በቂ ግንዛቤ መያዝ ያስፈልጋል።

       በትዳር ውስጥ በባልና በሚስት መካከል ሊኖር የሚገባውና እጅግ አስፈላጊ የሆነው የመተማመን መንፈስ መሠረቱ የሚጣለው በትዳር የመጀመሪያ ዓመት ነው። ባለትዳሮች በዚህ ጥንቃቄን በሚፈልግ ወሳኝ የትዳር ወቅት ይህን መተማመን እንዴት መገንባትና ማዳበር  እንደሚኖርባቸው ማወቅ ኖርባቸዋል። በዚህ ግዜ መተማመን ከሚያደፈርሱ ነገሮች ሁሉ መራቅ አለባቸው። በዚህ ግዜ በመካከላቸው በቂ የመተማመን መንፈስ መገንባት ካልቻሉ የትዳራቸው ዘላቂነትና ህልውና ከፊት ለፊቱ አደጋ ይጋረጥበታል።

     በትዳር የመጀመሪያ ወራት ባልና ሚስት የትዳር ተጣማሪዎቻቸውን ዝንባሌ፣ ፍላጎት አስተሳሰብና ጠቅላላ ስብዕና በቅርብ ለመረዳት መሞከር አለባቸው ወንዶችንና የሴቶችን ስብዕና ጅምላ በአራት ክፍሎች ከፋፍሎ ማስቀመጥ ይችላል።

@ ምክንያታዊ ስብዕና
    ይህ ስብዕና አውነታዎችና መረጃዎች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ያደርጋል፤ ሁኔታዎችን ሳይፈትሽና መርጃን ሳይመለከት ውሳኔ ለመስጠት ይቸገራል። «ምን ያህል» «ለምን» «እንዴት» የሚሉ ጥያቄዎች ዘወትር ከአንደበቱ አይጠፋም።

@ ፈጠራና ለውጥ አፍቃሪ ስብዕና
    ይህ ስብዕና ሁልግዜ መታደስ ይወዳል። ለውጥ ይፈልጋል። ሐሳቦቹ ጠንካራና ጥልቅ ናቸው። ለምሳሌ ይህን ዓይነት ስብዕና ያላት ሚስት በአዳዲስ አለባበስ ስልቶች ሁልግዜ ለባልዋ አዲስ ሆና መቅረብ ትፈልጋለች።

@ ትዕዛዝ ተቀባይና ስርዓት አፍቃሪ ስብዕና  
    ይህ  ስብዕና ለውጥና አዲስ ነገር ስሜቱን አይኮረኩረውም። ሁሉ ነገር ባለበት እንዲቀጥል ይፈልጋል። ስርዓት በጣም የሚወድ ሲሆን ስርዓት አልበኝነት ይጠላል። ለምሣሌ ይህን ዓይነት ሰብዕና ያላት ሴት ከባልዋ ጋር በምትሆንበት ግዜ ለረዥም ወቅት አንድ አይነት ልብስ ብቻ ታዘወትራለች። ስርዓት መውደድ ጥሩ ቢሆንም ስርዓት መጠበቅን በዚህ መንገድ መተርጎምን መጠበቅ ግን ስህተት ነው።

@ ስሜታዊ ስብዕና
       ይህ ስብዕና እጅግ ሲበዛ ስሜታዊ ነው። በቀላል ነገር ልቡ ይኮረኮራል፤ እንባው ዓይኖቹ ጫፍ ላይ ነው። እርጋታ ይወዳል፤ ሠዎችን መርዳት ያስደስተዋል።

    ከላይ የተጠቀሱት የስብዕና  ዓይነቶች ተፈጥሮዓዊ ሊሆኑ ይችላሉ። ባልና ሚስት የትዳር ተጣማሪያቸው ምን ዓይነት ስብዕና እንዳለቸው መረዳት እና ከዚያ ስብዕና ጋር ተስማሚ የሆነ አካሄድ መምረጥ አለባቸው አንድ አይነት ተመሳሳይ ስብዕና ካላቸው ነገሮች በተሻለ ቀላል ይሆናሉ። ስብዕናቸው የተለያየ ከሆነ ግን የመደጋገፍ የመሟሟላት ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል።


       በትዳር የመጀመሪያ ወራቶች ሊታወቁ ከሚገባቸው አስፈላጊ ነጥቦች አንዱ በቤት ውስጥ ለራስ ያለን መብት እና በራስ ላይ ያለን ግዴታ ማወቅ ነው። ኢስላም ለባልና ሚስት ለእያንዳዳቸው ያለን መብት እና በራስ ላይ ያለን ግዴታ ማወቅ ነው። ኢስላም ለባልና ሚስት ለእያንዳዳቸው የየራሳቸውን መብቶች ሰጥቷቸዋል፤ በእያንዳንዳቸው ላይ ያለውን ግዴታ  አስቀምጧል። በተለይ በመጀመሪያ የትዳር ወራቶች ኢስላም ለትዳር አጋር ያስቀመጠውን መብት መስጠትና የራስን ግዴታ መወጣት ለትዳር ስኬት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል። 

ብዙ የትዳር ፈተናዎች እና መናጋቶች ባል የራሱን መብት ሲያስታወስና  የሚስቱን መብት ሲረሳ ፣ ሚስት የራሷን መብት ስታስታውስና የባልዋን መብት ስትረሳ የሚፈጠሩ ናቸው። ይህ ሁኔታ በተለይ በትዳር የመጀመሪያ ዓመት ልዩ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል። 


No comments:

Post a Comment