Tuesday, 21 February 2017

የጥቢ ዝምድና (ረዷዓህ) እና መስፈርቶቹ

የጥቢ ዝምድና (ረዷዓህ) እና መስፈርቶቹ

ምስጋና ለአላህ የተገባ ነው። የአላህ ሰላምና እዝነት በመልዕክተኛው፣ በቤተሰቦቻቸውና በባልደረቦቻቸው ላይ ይሁን።

    ሙስሊም የሆነ ሰው ኢስላማዊ ህጎችን ማወቅና መረዳት እንዲሁም መውደድ አለበት፤ አምላካችን አላህ ጥበበኛ ነውና ለእኛ የበለጠ የሚበጀውን ያውቃል። እንደ ኢስላም፤ ከአንድ እናት ጡት የጠቡ የተለያዩ ሰዎችን የሚያስተሳስር ዝምድና አለ።  ይህ ዝምድምናም የስጋ ዝምድና እንደሚከለክለው ከጋብቻ ይከለክላል። የጥቢ ዝምድና  እና ትስስርን ተከትለው የሚከሰቱ ተያያዥ ፈቃዶች እና ክልከላዎች ስላሉ ህግጋቱ መታወቃቸው ግድ ይሆናል። ህግጋቱ  ባልታወቁበት ሁኔታ ሊፈጠሩ የሚችሉትን ቤተሰባዊና ማህበራዊ ቀውሶች ማስተዋል አይከብድም። የጥቢ ዝምድና  ድንጋጌ በቁርአን በሱና የተረጋገጠ ከመሆኑም ባሻገር በሙስሊም ሊቃውንትም አጠቃላይ ስምምነት ኢጅማዕ የተደገፈ ነው። አላህ ለጋብቻ እርም የሆኑብንን ሴቶች ሲዘረዝር እንዲህ ብሏል፤

( وَأُمَّهَاتُكُمُ اللَّاتِي أَرْضَعْنَكُمْ وَأَخَوَاتُكُمْ مِنَ الرَّضَاعَةِ ) [النساء: 23].
«አነዚያ ጡት ያጠቧችሁ እናቶቻችሁ፣ የጥቢ እህቶቻችሁም..»  ኒሳዕ 23

በሌላ አንቀጽ እንዲህ ብሏል፤
 (وَإِنْ تَعَاسَرْتُمْ فَسَتُرْضِعُ لَهُ أُخْرَى) [الطلاق: 6].
 «ለእናንተም (ልጆቻችሁን) ቢያጠቡላችሁ ምንዳዎቻቸውን ስጧቸው፡፡ በመካከላችሁም በመልካም ነገር ተመካከሩ፡፡ ብትቸጋገሩም ለእርሱ ሌላ (ሴት) ታጠባለታለች።» አጦላቅ 6

በሌላም አንቀጽ እንዲህ ብሏል፤
 (وَإِنْ أَرَدْتُمْ أَنْ تَسْتَرْضِعُوا أَوْلَادَكُمْ فَلَا جُنَاحَ عَلَيْكُمْ) [البقرة: 233].
«ልጆቻችሁንም ለሌሎች አጥቢዎች ማስጠባትን ብትፈልጉ ልትሰጡ የሻችሁትን በመልካም ኹኔታ በሰጣችሁ ጊዜ (በማስጠባታችሁ) በእናንተ ላይ ኃጢኣት የለባችሁም፡፡» አልበቀራህ 233

የማጥባት ትስስር ህግ አላህ ያዘዘውና የደነገገው ለመሆኑ እነዚህ በቂና ግልጽ ቁርአናዊ ማስረጃዎች ናቸው። በተመሳሳይ መልኩም ግልጽ የሆኑ ሀዲሳዊ መረጃዎችን እናገኛለን።

عن عائشة -رضي الله عنها- أن عمها من الرضاعة يسمى أفلح استأذن عليها فحجبته فأخبرت رسول الله - صلى الله عليه وسلم - فقال لها: "لا تحتجبي منه فإنه يحرم من الرضاعة ما يحرم من النسب" رواه البخاري ومسلمٌ

የምእመናን እናት አዒሻ ባስተላለፈችው ሀዲስ አፍለህ የተባለ በማጥባት አጎቷ የሆነ ሰው ለመግባት አስፈቀደና ተከለለችው፤ ይህንን ለመልዕክተኛው ስትነግራቸው “ከእርሱ አትከለይ፤ ምክንይቱም በዝምድና እርም የሆነ በጥቢም እርም ይሆናል” አሏት። ሀዲሱ በቡኻሪ ቁጥር (4941) እና በሙስሊም (1445) ተዘግቧል


 عن ابن عباس رضي الله عنهما قال: قال رسول الله - صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ - في بنت حمزة: (إنها لا تحل لي، إنها ابنة أخي من الرضاعة، ويحرم من الرضاعة ما يحرم من الرحم)  رواه البخاري ومسلم

ዓሊይ አቢ አቢጧሊብ የሀምዛን ልጅ እንዲይገቡ የአላህ መልዕክተኛን ሲጠይቃቸው፤ «እርሷ አትፈቀድልኝም! እርሷ የጥቢ ወንድሜ ልጅ ናት፤ በዝምድና እርም የሆነው በጥቢም እርም ይሆናል» በማለት መለሱለት። በቡኻሪ ቁጥር (5100) እና ሙስሊም (1447) ከኢብኑ አባስ ተዘግቧል።

በጥቅሉ በዝምድና ምክንያት እርም የሆነ በጥቢም እርም ይሆናል” የሚለው የመልዕክተኛው ንግግር ከምእመናን እናት አዒሻ፣ ከአሊይ፣ ከኢብኑ አባስ እና ከሌሎችም ተዘግቧል። ስለዚህም የማጥባት ትስስር፤ ጋብቻን ከመከልከልና እርም ከማድረግ፣ እይታን ልቅ ከማድረግ እንዲሁም ከሴቷ ጋር ለብቻ ከመገለል አንፃር ተፅእኖ እንዳለው ኡለማዎች ሁሉ ተስማምተውበታል።

ሙስሊም ሊቃውንትም አጠቃላይ ስምምነት ኢጅማዕ ያለበት ስለመሆኑ በርካታ የፊቅህ አዋቂዎች ያጸደቁት ሲሆን፤ ኢብኑል ሙንዚር፣ ኢብኑ ሀዝም እና ሙወፈቅ ኢብኑ ቁዳማህ ይገኙበታል።
(አል ኢጅማዕ ግጽ 77 ፣ መራቲበል ኢጅማዕ ገጽ 67 አልሙግኒ 9/191 ይመልከቱ)

የጥቢ ዝምድና  ብይንና ተጽዕኖ

      የጥቢ ዝምድና ከጋብቻ ጋር በተያያዘ የዘር ዝምድና ያለውን ብይን ይጋራል። ማለትም የጥቢ ዝምድና ጋብቻን ከመከልከል፣ መህረም ከመሆን፣ ለብቻ ከመገለል እና ሴትን ከማየት አንጻር ተጽዕኖ አለው። የጥቢ ዝምድና  የቅርብ ዘመድ ከማድረጉ ባሻገር ለጋብቻ እርምነትንም ጽኑ ያደርጋል። በስጋ ዝምድና አንድ ወንድ ልጅ በእናቱ ምክንያት ለጋብቻ እርም የሚሆኑበት የእናቱ ቤተሰብ የሆኑ ሴቶች ሁሉ በማጥባት ዝምድናም እርም ይሆኑበታል። የጥቢ ዝምድና በአብዛኛው አጥቢዋ ሴት በማጥባቷ ምክንያት የምታገኘውን እናትነት መሰረት አድርጎ የሚከሰት ዝምድና እና ትስስር ነው። ዝምድናው በአብዛኛው በአጥቢዋ በኩል እንጂ በጠቢው ህጻን በኩል የሚሰራጭ አይደለም። የሚጠባው ህጻን አድጎ ልጆች ካፈራ አጥቢዋ ለልጆቹ አያት ከመሆንዋ በቀር ዘመዶቹን እና ዘመዶቿን ሁሉ አያስተሳስርም። ይህ በመጥባት ዝምድና ዙርያ ብዙዎች የሚስቱት መሰረታዊ መነሻ ነው።

የጥቢ ዝምድና ፍቃዶች እና ክልከላዎች

የጥቢ ዝምድና  ከጋብቻ ጋር በተያያዘ ሁለት አይነት ትጽዕኖዎችን ይፈጥራል።
ክልከላ፦ አላህ ለጋብቻ እርም የሆኑብንን ሴቶች ሲዘረዝር እንዲህ ብሏል፤

«አነዚያ ጡት ያጠቧችሁ እናቶቻችሁ፣ የጥቢ እህቶቻችሁም...» ኒሳዕ 23

በዚህናበዝምድና ምክንያት እርም የሆነ በጥቢም እርም ይሆናል” በሚለው የመልዕክተኛው ንግግር መሰረት የስጋ ዝምድና ክልክል የሚያደርገውን ሁሉ የጥቢ ዝምድናም እርም ያደርጋል። ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው አጥቢ ሴት ልክ እንደ እናት ትቆጠራለች፤ ክልከላው መሰረት የሚያደርገዉም እሷን ነው። ስለዚህም እሷ ላጠባችው ልጅ እሷና በስጋ ዝምድና ምክንያትከእናቱ ጋር በተያያዘ እርም የሚሆኑበት ሁሉ በአጥቢዋ እናቱም በኩል ክልክል ይሆኑበታል። በማጥባት ተጽዕኖ ምክንያትአንድ ወንድ ላይ ከጋብቻ እርም የሚሆኑበትን ሴቶች በሚከተለው መልኩ መዘርዘር ይቻላል፤
አጥቢዋ
የአጥቢዋ እናት (የጥቢ አያቱ)
የአጥቢዋ ባል እናት (የጥቢ አያቱ)
የአጥቢዋ እህት (የጥቢ አክስቱ)
የአጥቢዋ የባልዋ እህት (የጥቢ አክስቱ)
የአጥቢዋ ልጆች (የጥቢ እህቶቹ)
የአጥቢዋ የልጅ ልጆች (በጥቢ የእህቶቹ ልጆች)

ፈቃድ፦ በአንድ ሰውና እንደ እናትና ልጅ ባሉ ቅርብ ዘመዶቹ መካከል የሚፈቀድ እንደ መመልከት ለብቻ መገለልና የመሳሰሉ ፈቃዶች ሁሉ የጥቢ ዝምድናንም ተከትለው ይፈቀዳሉ።  ሆኖም የጥቢ ዝምድና  የስጋ ዝምድናን ያክል የጠነከረ አይደለምና ውርስን፣ የቀለብ ግዴታነትን እና የመሳሰሉ ድንጋጌዎችን ሁሉ አያጋራም:: (አልሙግኒ 9/191)



No comments:

Post a Comment