የጥቢ ዝምድና መስፈርቶች
የጥቢ ዝምድና እንዲኖር ተከታዮቹ መስፈርቶች መሟላት አለባቸው።
1⇒ የሚጠባው ህጻን ከሁለት አመት በታች መሆን አለበት፦
ህፃን ልጅ በሚጠባበት
እድሜ (ጡት ሳይለቅ) በምግብነት የጠባው መሆን አለበት፤ ይህም በህጻኑ
በመጀመሪያዎቹ ሁለት አመታት የእድሜ ክልል ውስጥ ነው። የመጀመሪያዎቹ ሁለት አመታት ህጻናትን ማጥባት የተሟላና መደበኛ የማጥባት
ስርአት መሆኑ በቁርአን በሱረቱል ሉቅማን 14 እና በሱረቱል በቀራህ 233 ላይ ተጠቁሟል።
አላህ እንዲህ ብሏል፤
(وَالْوَالِدَاتُ
يُرْضِعْنَ أَوْلَادَهُنَّ حَوْلَيْنِ كَامِلَيْنِ لِمَنْ أَرَادَ أَنْ يُتِمَّ
الرَّضَاعَةَ) {البقرة : 233}
«እናቶችም ልጆቻቸውን
ሙሉ የኾኑን ሁለት ዓመታት ያጥቡ፡፡ (ይህም) ማጥባትን መሙላት ለሻ
ሰው ነው» አል በቀራህ 233
በዚህ ጉዳይ ላይ
ከምዕመናን እናት ኡሙ ሰለማ የተላለፈውን ተከታዩን ግልጽ ሀዲስ እናገኛለን፤
عَنْ أُمِّ
سَلَمَةَ رضي الله عنها قَالَتْ : قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ
وَسَلَّمَ : (لَا يُحَرِّمُ مِنْ الرِّضَاعَةِ إِلَّا مَا فَتَقَ الْأَمْعَاءَ فِي
الثَّدْيِ، وَكَانَ قَبْلَ الْفِطَامِ) والحديث صححه الألباني في صحيح
الترمذي
«እርም የሚያደርገው
መጥባት አንጀት የደረሰ እና በጥቢ ዘመን ጡት ከመልቀቅ በፊት የተፈጸመ ነው» ሀዲሱን ቲርሚዚይ እና ኢብኑ ማጃህ ዘግበውታል አልባኒም በሶሂህ አቲርሚዚይ
የትክክለኛ ሀዲሶች ጥንቅር ውስጥ አካተውታል። ሀዲሱን የዘገቡት አል ኢማም አቲርሚዚይ ረሂመሁላህ እንዲህ ብለዋል፤
«ይህ ትክክለኛ ሀዲስ ሲሆን ደረጃው (ሀሰኑን ሰሂህ) ነው። “እርም የሚያደርገው መጥባት ከሁለት
አመት በፊት ከሆነ ብቻ ነው” የሚለው የሰሀቦችና ከእነሱም በኃላ የመጡት ታላላቅ ኡለማዎች ሁሉ አቋም ነው። ህፃኑ ሁለት
አመት ከሞላው በኋላ የተከሰተ ማጥባት ምንንም እርም አያደርግም» ቱህፈቱል አህወዚይ ቅጽ 4 ገጽ 264
በዚህም መሰረት የጥቢ
ዝምድና ሁለት አመት ያለፈው ልጅ በማጥባት አይከሰትም። እርም የሚያደርገው
ማጥባት ህጻኑ ሁለት አመት ከመሙላቱ በፊት ያለው ብቻ ነው። ከሁለት አመቱ በፊት ጡት የለቀቀ ቢሆን እንኳ ቢጠባ ዝምድናው ይገኛል።
ዋናው ከሁለት አመቱ አለማለፉ እንጂ ጡት መልቀቁ አይደለም። ይህ የብዙሀኑ የሻፊኢያ ይሀንበሊያና የማሊክ እንዲሁም የከፊል ሀነፊያ
የፊቅህ ለቃውንት አቋም ነው (አልሙግኒ 9/201 ይመልከቱ)
ይህ የማጥባት ህግ እስከ 30 ወራት ይዘልቃል፤
ህጻኑ ጡት ለቀቀም አለቀቀ የሚታየው 30 ወራት አለመሙላቱ ነው ያሉት የሀነፊ መዝሀብ ኡለማዎች ሲሆኑ ተከታዩን የቁርአን አንቀጽ
መረጃ አድርገዋል። (አል መብሱጥ ሊሰርሰኺ 5/136)
{وَحَمْلُهُ
وَفِصَالُهُ ثَلَاثُونَ شَهْرًا} (سورة الأحقاف: 15)
«እርግዝናውና ከጡት መለያውም ሰላሳ ወር ነው፡፡» አል አህቃፍ 15
የሀነፊ ኡለማዎች መረጃ ያደረጉት ይህ አንቀጽ አነስተኛውን
የእርግዝና ግዜ 6 ወር አካቶ የመጣ በመሆኑ ሁለት አመት (24 ወራት) ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ነው። ሌሎች መረጃዎችም ሁለት አመት
የሚለውን ከማጠናከራቸው ከሁለት አመት በፊት የሚለው አንጻር ሚዛን ደፊ ነው።
2⇒ አምስት ግዜ መጥባት፦
ህፃኑ ጠግቦ ሙሉ በሆነ ጥቢ አምስት ጊዜ የጠባና በራሱ ጊዜ ጡት የተወ መሆን አለበት። አንድ ግዜም ቢጠባ በቂ ነው
ያሉ ኡለማዎች እንዳሉ ሁሉ በሶስት እና በአስር የገደቡትም አልጠፉም። ሆኖም አምስት ግዜ መጥባቱ ግዴታ ነው የሚሉት የሻፍኢያ እና
የሀንበሊያ መዝሀብ ኡለማዎች አቋም ሚዛን የሚደፋና በጠንካራ መረጃዎች የተደገፈ ነው። (አል ሙግኒ 9/192 ፤ አል ሙሀዘብ
2/156)
አምስት ጊዜ መጥባት
መስፈርት ለመሆኑ መረጃው ተከታዩ የምእመናን እናት አዒሻ ያስተላለፈችው ሀዲስ ነው፤
عن عائشة رضي
الله عنها قالت : "كان فيما أنزل من القران عشر رضعات معلومات يحرمن ثم نسخن
بخمس معلومات فتوفي رسول الله صلى الله عليه وسلم وهن فيما يقرأ من
القرآن." رواه مسلم
የምእመናን እናት
አዒሻ እንዲህ ብለዋል፤
«በቁርአን ላይ ከወረዱት
አንቀፆች መካከል "አስር የታወቁ ጥቢዎች እርም ያደርጋሉ” የሚል ነበረ፤ በኃላ ግን ተሻረና “አምስት ግልጽ የሆኑ ጥቢዎች…”
በሚል ተተካ፤ መልእክተኛው ሲሞቱም (ቅርብ ግዜ በመሻሩ አንዳንድ ያልደረሳቸው ሰዎች ዘንድ) ከቁርአን ይነበብ ነበር» ሙስሊም በቁጥር 1452 ዘግበውታል።
አስር የሚለው በአምስት
ከተተካ በኋላ “አምስት ግልጽ የሆኑ ጥቢዎች” የሚለው ንባቡ ተሽሮ ህግነቱ ግን የፀና ሆኖ ቀረ ማለት ነው። ይህ አይነቱ
ድንጋጌን ሳይሆን ንባብን ብቻ የመሻር የ “ነስኽ” አይነት የኢስላም ሊቃውንት ዘንድ የታወቀ ነው። ስለዚህም በትክክለኛው የኡለማዎች
አቋም መሰረት ከአምስት ጊዜ በታች መጥባት እርም አያደርግም።
አንድ ግዜ መጥባት
የሚባለው፦ ህጻኑ ጡት ከያዘ በኋላ በግልጽ ጠብቶ በሚስተዋል
መልኩ ካቋረጠ አንድ ጊዜ ጠባ ተብሎ ይቆጠራል። አንዳንድ ኡለማዎች ዘንድ ለመተንፈስ ወይም ጡት ለመቀየርም ቢሆን አቁሞ ከቀጠለ እንደ ሁለት ጥቢ ይቆጥሩታል። ሆኖም የመጥባት ገደብ በግልጽ
ያልተቀመጠ በመሆኑ በተለምዶ ወደታወቀው የመጥባት ትርጉም ይመለሳል። በተቃራኒው ይህ አይነቱ ማቋረጥ እራሱን ችሎ መጥባት የሚባል
አይሆንም የሚለው ትክክለኛው አቋም መሆኑን ታላላቅ ፉቀሀዕ አስምረውበታል። (አል ሙግኒ 9/194 ፤ ሙግኒል ሙህታጅ 3/417)
ታላቁ የፊቅህ አዋቂ
ሸይኽ ሙሀመድ ቢን ሷሊህ አል ዑሰይሚን እንዳሉት፤ አንድ ጥቢ ማለት አንድ
ማእድ እንደማለት ነው። በተለያየ ግዜ (መጅሊስ)
የጠባ መሆኑ መስፈርት ነው ብዬ አምናለሁ፤ በአንድ ግዜ ጥቢ እያቋረጠ ቢቀጥል አንድ ጥቢ ነወ የሚባለው። ጥንቃቄ ከማድረግ አንጻርም
የተሻለው አቋም ይህ ነው በማለት አብራርተዋል። (ኑሩን አለደርብ ቅጽ 19 ገጽ 2)
በዚህም መሰረት ህፃኑ ጠብቷል ለማለት በማያሻማ መልኩ አምስት ጊዜ የጠባና በራሱ ጊዜ
የተወ መሆኑ መስፈርት ነው። ቅጽበታዊ ማቋረጦችም ቁጥር ውስጥ አይገቡም። ከአምስት ግዜ በታች የሆነ ጥቢ ግን መስፈርት ያልተሟላበት
ነውና ተፅዕኖ የለውም።
¯ የጥቢ መዛመድ እንዲከሰት እድሜው ከሁለት አመት ያልበለጠ ህጻን አምስት ግዜ መጥባት አለበት። እነዚህ ሁለት መሰረታዊ
መስፈርቶች ባልተሟሉበት ሁኔታ የተፈፀመ መጥባት ከሆነ ምንም አይነት የመዛመድና እርም የማድረግ ተፅዕኖ አያሳድርም።
No comments:
Post a Comment