Monday, 20 February 2017

ተቅዋ

ተቅዋ
ውድ እህቶቼ ሆይ!

ታላቅና ከጉድለቶች ሁሉ ነፃ የሆነው አላህ በመጀመሪያዎቹና በመጨረሻዎቹም ሕዝቦች (ባሪያዎች) ላይ ያዘዘው ነገር ቢኖር አላህን ፉሩ በማለት ነበር፡፡ ይህንንም በማስመልከት ከፍ ያለው አለህ እንዲህ ይላል፡-

‹‹እነዚያንም ከበፊታችሁ መጽሐፍን የተሰጡትን እናንተንም አላህን ፍሩ በማለት በእርግጥ አዘዝን፡፡ ብትክዱም በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የአላህ ነው፡፡ (አትጐዱትም)፡፡ አላህም ተብቃቂ ምስጉን ነው፡፡›› (አል ኒሳእ 131)

በተጨማሪም መልዕክተኛው ለሕዝቦቻቸው ያስተላለፉት ትዕዛዝ (ምክር)፡- ከአቢ ኡማማ እንደተወራው ስማቸው ሱዳና ኢብኑ አጅላን አልባህሊይ ይባላል (አላህ ከሳቸው የሆነውን ይውደድላቸውና) የአላህ መልዕክተኛ በሐጀተል ወዳዕ ምክር ሲሰጡ እንዲህ ሲሉ ሰምቻለሁ ብሎ አለ፡፡

 اتقوا ربكم وصلّوا خمسكم، وصوموا شهركم، وأدّوا زكاة أموالكم، وأطيعوا أمراءكم، تدخلوا جنة ربكم

ጌታችሁን ፍሩ፣ የአምስት ጊዜ ስግደታችሁንም ፈፅሙ፣ የረመዳንንም ወር ጹሙ፣ የገንዘባችሁንንም ዘካ ስጡ፣ አሚሮቻችሁንም ታዘዙ የጌታችሁን ጀነት ትገባላችሁ፡፡”

ነብዩ ለአንድ ሰራዊት አሚር አድርገው በላኩ ጊዜ በተለየ ሁኔታ ለእራሱ አላህን በመፍራት ምክር ያስተላልፉለት ነበር፡፡  በተጨማሪም እሱ ጋር ካሉት ሙስሊሞች በጥሩ ነገር ይመክሯቸው ነበር፡፡

            ቀደምት ሳሊሆች በምክሮቻቸውና በፅሁፎቻቸው ላይ እንዲሁም ከዚህችም አለም በሞት በተለዩ ጊዜ አላህን ፍሩ ከማለት አልተወገዱም፡፡
            ዑመር ኢብኑል ኸጣብ አንዲት ፅሑፍ ወደ ልጁ አብድላህ ጽፎ ነበር የፅሑፉም መልዕክት እንዲህ ነበር የሚለው፡-

 “በመቀጠልም …… ታላቁን አላህ በመፍራት እመክርሃለሁ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው አላህን የፈራ ይጠብቀዋል፣ እሱ ጋር ያስቀመጠም ይመነደዋል፣ ላመሰገነውም ይጨምርለታል”

            አልይ አንድን ሰው እንዲህ በማለት መከረ “እሱን ከመገናኘት ምንም ቅሮት የሌለውን ያንን ታላቁን አላህ በመፍራት እመክርሀለሁ፡፡ ከእሱ ሌላ መጨረሻም የለህም እሱም (አላህ) የቅርቢቱንና የመጨረሻይቱ ሀገር ባለቤት ነው”

            ከሳሊሆች ውስጥ አንዱ በአላህ መንገድ ላይ የተገናኘው ወንድም ነበረውና ወደእሱ አንዲትን ፅሑፍ ፃፈለት
“ በመቀጠልም ይላል …
“አላህን በመፍራት እመክርሃለሁ ያህ እሱ አልጋህ ላይ ሆነህ የሚጠብቅህን፣ ከላይ ሆኖ የሚቆጣጠርህን፣ በማንኛውም ሁኔታ በቀንም ይሁን በማታ (በሌሊት) አላህን ቀልብህ ውሰጥ አድርግ፣ አላህን ከአንተ ባለው ቅርበትና በአንተ ላይ ባለው ችሎታ ልክ ፍራው፣ አንተ በእሱ እይታ (ጥበቃ) ስር እንደሆንክም እወቅ፣ ከእሱ ስልጣን ስር ወጥተህ ወደ ሌላ ስልጣን ስር አትግባ፣ ከእሱ ባለቤትነትም ወጥተህ ወደ ሌላ ባለቤትነት አትግባ፣ ከእሱ ጥንቁቅነትህ ከፍ ይበል ፍራቻህ ይብዛ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን፡፡”

ፍራቻ (ተቅዋ)፡- ማለት አንድ ሰው በራሱና በሚፈራው ነገር መሀል ከእራሱ የሆነ መጠበቂያ ሲያደርግ ተቅዋ አድርጓል ይባላል፡፡

አንድ ሰው አላህን ፈርቷል ስንል፡-

በእራሱና ከሚፈራው ነገር፣ ከቁጣውና ከጥላቻው የሚጠብቀውን ትዕዛዙን በመፈፀምና ክልከላውን በመራቅ መከላከያ ማድረግ ማለት ነው፡፡

ይኸውልሽ  ውድ እህቴ፡-

ቀደምት ሳሊሆች የተቅዋን ትርጉም በማብራራት የተጠቀሟቸው ከፊል አባባሎች፡-

አብድላህ ኢብኑ አባስ (ከእሱ የሆነውን አላህ ይውደድለትና) እንዲህ ይላል ፡-

“አላህን ፈሪዎች የሚባሉት እነዚያ አላህንና ቅጣቱን የሚጠነቀቁ ናቸው፡፡”

ጠልቅ ኢብኑ ሐቢብ ተቅዋን በማስመልከት እንዲህ ይላል ፡-

‹‹አላህን መፍራት ሲባል በአላህ ብርሃን የአላህን ትዕዛዝ ልትፈፅምና ከአላህ ምንዳ (ዋጋ) ልትፈልግ፤ እንዲሁም በአላህ ብርሃን የአላህን ክልከላ ልትርቅና ቅጣቱን ልትፈራ ማለት ነው፡፡››

አብድላህ ኢብኑ መስዑድ 
ﭿ ﭧ  ﭨ  ﭩ  ﭪ  آل عمران: 102 
የሚለውን የቁርአን አንቀፅ ሲተረጉም እንዲህ ይላል፡-
“ትዕዛዙ ሊፈፅምና ክልከላው ሊራቅ፣ ሁሌም ሊታወስ ላይረሳ፣ ሊመሰገንና ፀጋው ላይካድ”

ውድ እህቴ ታላቁን አላህ በመፍራት ላይ ጓጊ እሱ ከጉድለቶች ሁሉ የጠራ ሲሆን ሊፈራ የተገባና እንዲሁም ልቅዕናውን ልብሽ ውሰጥ ልታደርጊው ይገባል፡፡

No comments:

Post a Comment