Sunday, 19 February 2017

የወር አበባ ጅማሬና መጨረሻ ጊዜ

 የወር አበባ ጅማሬና መጨረሻ ጊዜ
      
 ሴት ልጅ ዘጠኝ አመት እድሜ ሳይሞላት የወር አበባ ደም ሊኖርባት አይችልም፡፡ ምክንያቱም የትኛዋም ሴት ከዚህ እድሜ በፊት የወር አበባ ገጥሟት አያውቅም፡፡ 

ከዓኢሻም የሚከተለው ንግግራቸው ተዘግቧል “ልጃገረድ ዘጠኝ አመት ከሞላት ደረሰች ማለት ነው፡፡” (ቲርሚዚይና በይሐቂይ)

በአብዛኛው ደግሞ ከሀምሳ አመት በኋላ የወር አበባ ደም አይኖርም፡፡ ከዓኢሻ እንደተዘገበው “አንድ ሴት ሀምሳ አመት ከሞላት የወር አበባ ጊዜዋን አልፋለች፡፡” (አልሙግኒ 1\4ዐ6)

 አነስተኛውና አብዛኛው የወር አበባ ጊዜ

     ከዑለማዎች አቋም ትክክለኛው ለወር አበባ ብዙ ትንሽ ቀነ ገደብ አለመወሰን ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ በሴቶች ተለምዶ የሚወሰን ነው፡፡
 የተለመደው የወር አበባ ጊዜ

     በተለምዶ በአብዛኛው ጊዜ የወር አበባ የሚቆየው ስድስት ወይም ሰባት ቀናት ነው፡፡ ነብዩ (ﷺ) እንዲህ ብለዋል “የወር አበባሽን እስከ ስድስት ወይም ሰባት ቀን ጠብቂውና ታጥበሽ ሀያ ሶስት ወይም ሀያ አራት ቀናት ስገጂ፡፡” (አቡዳውድና ቲርሚዚይ)
 በወር አበባና በወሊድ ደም ወቅቶች የሚከለከሉ ነገሮች
@ በብልት ግብረ ስጋ ግንኙነት መፈፀም፦           
አላህ እንዲህ ብሏል፡-
فَاعْتَزِلُوا النِّسَاءَ فِي الْمَحِيضِۖ وَلَا تَقْرَبُوهُنَّ حَتَّىٰ يَطْهُرْنَ 
‹‹ሴቶችንም በወር አበባ ጊዜ ራቋቸው፡፡ ንጹሕ እስከሚኾኑም ድረስ አትቅረቡዋቸው፡፡›› 
(አል በቀራህ 222)
ነብዩም (ﷺ) ይህ አንቀፅ የወረደ ጊዜ ሲያብራራሩት እንዲህ ብለዋል “ከግብረ ስጋ ግንኙነት ውጪ ሁሉን ነገር መፈፀም ትችላላችሁ፡፡” ብለዋል:: (ሙስሊም ዘግበውታል)
@ የፍቺ ስነስርዓት፡- አላህ እንዲህ ብሏል፡-
إِذَا طَلَّقْتُمُ النِّسَاءَ فَطَلِّقُوهُنَّ لِعِدَّتِهِنَّ وَأَحْصُوا الْعِدَّةَ
‹‹ሴቶችን መፍታት ባሰባችሁ ጊዜ፤ ለዒዳቸው ፍቱዋቸው፡፡›› (አል ጠላቅ 1)
የዑመር ልጅ ዓብደላህ ሚስታቸው የወር አበባ ላይ እያለች ፈተዋት ስለነበር ነብዩ  ለዑመር እንዲህ  “ሚስቱን እንዲመልሳት እዘዘው….” አሉት:: (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)
@ ሰላት መስገድ፡- ነብዩ (ﷺ) ለፋጢማ ቢንት ጀህሽ   “የወር አበባሽ ሲመጣ ሰላት አቁሚ” ብለዋታል::    (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)
@ መፆም፡- ነብዩ (ﷺ) እንዲህ ብለዋል “ሴት ልጅ የወር አበባዋ በሚመጣ ጊዜ አትሰግድም አትፆምም” (ቡኻሪ ዘግበውታል)
@ ካዕባን ጠዋፍ ማድረግ፡- ዓኢሻ የወር አበባዋ ሲመጣ ነብዩ (ﷺ) እንዲህ ብለዋታል “እስክትፀጂ ድረስ ካዕባን  ጠዋፍ ከማድረግ ውጭ የተቀሩትን የሀጅ ስራዎች ሁሉ ፈፅሚ፡፡” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)
@ ቁርአን ማንበብ፡-
ይህ የአብዛኞች ሰሃባዎች፣ ታቢዕዮችና ከነሱም ቡኋላ የመጡ ዑለማዎች አቋም ነው፡፡ ሆኖም ግን ለምሳሌ ቁርአንን በቃሏ የሸመደደች ሆኗ ለማስታወስ ወይም አስተማሪ ሆና ለተማሪዎች ለማስቀራት ለመሳሰሉ ጉዳዮች ቁርአን መቅራት አስፈላጊ ሆኖ ካገኘችው ማንበብ ትችላለች፡፡ ይህ ካልሆነ ግን አንዳንድ ዑለማዎች እንዳሉት ባታነብ ይመረጣል፡፡
@ ቁርአን መንካት፡-  አላህ እንዲህ ብሏል
لَّا يَمَسُّهُ إِلَّا الْمُطَهَّرُونَ 
‹‹የተጥራሩት እንጅ ሌላ አይነካውም፡፡›› (አል ዋቂዓ 79)
መስጂድ ውስጥ መቀመጥ፡-
ነብዩ (ﷺ) እንዲህ ብለዋል “መስጂድን ጀናባና የወር አበባ ላለባቸው አልፈቅድም “ (አቡዳውድ ዘግበውታል)
እንዲሁም “ዓኢሻ የወር አበባ ላይ ሆና ነብዩ (ﷺ) ከመስጂድ ወደ ክፍልዋ ራሳቸውን አስገብተውላት ታበጥርላቸው ነበር፡፡” (ቡኻሪ ዘግበውታል)

መስጂድ ውስጥ በመንጠባጠብ የሚበክል ከሆነ ማለፍም አይፈቀድላትም፡፡ ይህ ካልሆነ ገን አትከለከልም፡፡

No comments:

Post a Comment