Monday, 20 February 2017

ታላላቅ የቂያማ ምልክቶች

ታላላቅ የቂያማ ምልክቶች 

 እነዚህ አስር የቂያማ ምልክቶችን እንደሚከተለው በዝርዝር ከነማስረጃዎቻቸው ይቀርባሉ፡፡

አንደኛ ምልክት፡- የመህዲ መምጣት

            መህዲ ከነቢዩ صلى الله عليه وسلم  ቤተሰቦች የሐሰን ኢብን አሊ ዘር የሚወለድ ስሙና የአባቱ ስም የነቢያችንና የአባታቸውን ስም ተመሳሳይ የሆነ ምድር በአድልዎና በበደል ከሞላች በኃላ በፍትህና እኩልነት ሊለውጥ የሚመጣ ሰው ነው፡፡

            አቡዳውድ ቲርሚዚይ ከአብደላ ኢብን መስዑድ በአስተላለፉት ሀዲስ  ነቢዩ صلى الله عليه وسلم እንዲህ ይላሉ

« لا تذهب الدنيا حتى يملك العرب رجل من أهل بيتي يواطئ اسمه اسمي واسم أبيه اسم أبي ، يملأ الأرض عدلا وقسطا كما ملئت جورا وظلما »

አንድ ስሙ ከስሜ ጋር የአባቱ ስም ከአባቴ ስም ጋር የሚስማማ ሰው ዓረብን ገዝቶ ምድር በአድልዎና በበደል ከተሞላች በኃላ በፍትህና በእኩልነት ሳይሞላት ይህች አለም አትወገድም” (አቡዳውድ 4282 ቲርሚዚይ 223ዐ)

ሁለተኛው ምልክት፡- የመሲህ ደጃል መምጣት

መሲህ ደጃል በዘመን መጨረሻ አካባቢ ብቅ የሚል ሰው ሲሆን የተለያዩ ከተለምዶ ወጣ ያሉ ነገሮችን እንዲስራ አላህ ያስቻለው ፈታኝ ነው፡፡ እኔ ጌታ ነኝ የሚል ጥሪ በማድረግ ያመነበትን ጀነት መሳይ እውነታው ግን ጀሃነም በሱ የካደን ጀሃነም የሚመስል ውስጡ ግን ጀነት ያስገባል፡፡

            ሙስሊም ከአብደላህ ኢብን ዓምር ኢብኑል ዓስ በአስተላለፈው ሀዲስ ነብዩ صلى الله عليه وسلم እንዲህ ብለዋል

« يخرج الدجال في أمتي فيمكث أربعين لا أدري أربعين يوما أو أربعين شهرا أو أربعين عاما فيبعث الله عيسى ابن مريم كأنه عروة بن مسعود فيطلبه فيهلكه »

ደጃል በህዝቦቼ መሀል ይነሳና አርባ ይቆያል (አርባ አመት ይበሉ አርባ ወራት ይበሉ አርባ ቀናት ይበሉ አላስታውስም) የመርየም ልጅ ኢሳ ይወርድና አሳዶ ይገለዋል፡፡” (ሙስሊም 294ዐ አህመድ 2/166)

ቡኻሪና ሙስሊም ከአብደላህ ኢብን ዑመር እንዳስተላለፉት በአንድ ወቅት ነቢዩ صلى الله عليه وسلم ቆመው አላህን በሚገባ ካወደሱ በኃላ ስለደጃል እንዲህ ብለው ተናገሩ

ሁሉም ነቢይ እሱን እንዳስጠነቀቀው እኔም አስጠንቅቃለሁ ኑህም ህዝቦቹን ከሱ አስጠንቅቋል፡፡ እኔ ግን የትኛውም ነቢይ ያልተናገረውን ልንገራችሁና እሱ አንድ አይን ስውር ነው፡፡ ጌታችሁ ግን አንድ አይን ስውር አይደለም፡፡”  
(ቡኻሪ 2892 ሙስሊም 2931)

ሶስተኛው ምልክት፡- የኢሳ ከሰማይ በመውረድ በፍትህ መፍረድና ደጃልን ማጥፋት

አላህ እንዲህ ይላል
{ وَإِنَّهُ لَعِلْمٌ لِلسَّاعَةِ } (الزخرف : 61)
‹‹እርሱም (ዒሳ) ለሰዓቲቱ (ማወቂያ) በእርግጥ ምልክት ነው፡፡›› ዙኽሩፍ 61

            ይህን አንቀጽ አብዛኞች የቁርአን አብራሪ ዑለማዎች በኢሳ መምጣት ተርጉመዋል፡፡ ኢማም አህመድም እንደዘገቡት ኢብኑ አባስ በዚህ አንቀጽ ዙሪያ እንዲህ ብለዋል “ይህ አንቀጽ ከቂያማ በፊት ስለኢሳ መውረድ የሚጠቁም ነው፡፡” (አህመድ 1/318)

            ኢሳ እንደሚወርድ የሚገልፁ ሀዲሶች ከነቢዩም صلى الله عليه وسلم ተዘግቧል፡፡ አቡ ሑረይራ በአስተላለፉት ሀዲስ ነቢይ صلى الله عليه وسلم እንዲህ ብለዋል
« والذي نفسي بيده ليوشكن أن ينزل فيكم ابن مريم حكما عدلا فيكسر الصليب ويقتل الخنزير ، ويضع الجزية ويفيض المال حتى لا يقبله أحد ، حتى تكون السجدة الواحدة خيرا من الدنيا وما فيها »
ነፍሴ በእጄ ባለው ጌታ እምላለሁ ኢሳ በእናንተ መካከል ፍትሃዊ ፈራጅ ለመሆን መስቀልን ለመስበር፣ አሳማን ለመግደልና ግብር ለማስቀረት ይመጣል፣ ገንዘብ በጣም በዝቶ ተቀባይ ይጠፋል አንድ ሱጁድ ማድረግ ዱንያን ሁሉ ከማግኘት የተሻለ ብልጫ ይሰጠዋል፡፡”
(ቡኻሪ 3264 ሙስሊም 155)

አራተኛው ምልክት፡- የየእጁድና መእጁጅ መምጣት

            ከኑህ ልጆች ውስጥ የያፊስ ዘሮች እንደሆኑ የሚነገርላቸው ማንም ሊዋጋቸው የማይችሉ አጥፊ ቡድኖች ናቸዉ፡፡ አላህ እንዲህ ይላል
{ حَتَّى إِذَا فُتِحَتْ يَأْجُوجُ وَمَأْجُوجُ وَهُمْ مِنْ كُلِّ حَدَبٍ يَنْسِلُونَ }{ وَاقْتَرَبَ الْوَعْدُ الْحَقُّ فَإِذَا هِيَ شَاخِصَةٌ أَبْصَارُ الَّذِينَ كَفَرُوا } (الأنبياء : 96 ، 97)

‹‹የእጁጅና መእጁጅም እነርሱ ከየተረተሩ የሚንደረደሩ ሲኾኑ (ግድባቸው) በተከፈተች ጊዜ እውነተኛውም ቀጠሮ በቀረበ ጊዜ፥ ያን ጊዜ እነሆ የእነዚያ የካዱት ሰዎች ዓይኖች ይፈጥጣሉ፡፡ ›› አል አንቢያ 96-97
           
ቡኻሪና ሙስሊም ከዘይነብ ቢንት ጀህሽ እንዳስተላለፉት በአንድ ወቅት የአላህ መልዕክተኛ صلى الله عليه وسلم ወደ ቤት ገብተው አንዲህ አሉ
« لا إله إلا الله ويل للعرب من شر قد اقترب فتح من ردم يأجوج ومأجوج مثل هذه " وحلق بأصبعه الإبهام والتي تليها »

ዓረብ ጉድ ፈላበት ክፋት ቀረበ ከየእጁጅ ማእጁድ ግድብ የዚህን ያህል ክፍተት ተከፈተ በማለት በአውራ ጣታቸውና በአመልካች ጣት የክብ ቅርፅ አሳዩ፡፡” (ቡኻሪ 3346 ሙስሊም 288ዐ)

አምስተኛው ምልክት፡- በሀበሻ ሰው ከዕባ መፍረስ

            ቡኻሪና ሙስሊም ከአቡ ሑረይራ እንዳስተላለፉት ነቢዩ صلى الله عليه وسلم እንዲህ ብለዋል

« يخرب الكعبة ذو السويقتين من الحبشة »
እጆቹ ቀጫጭ የሆኑ የሀበሻ ሰው ካዕባን ያፈርሳል፡፡” (ቡኻሪ 1591 ሙስሊም 29ዐ9)

ኢማም አህመድ ከአብደላህ ኡብን ዓምር እንዳስተላለፉት ነቢዩ صلى الله عليه وسلم እንዲህ ብለዋል

« يخرب الكعبة ذو السويقتين من الحبشة ، ويسلبها حليها ويجردها من كسوتها ، ولكأني أنظر إليه أصيلع أفيدع يضرب عليها بمسحاته ومعوله »

እግሮቹ ቀጫጭን አጥንቱ የዞረ መላጣ ሀበሻ በመቆፈሪያው እየመታ ካዕባን ያፈርሳል ከልብሷና ከጌጣጌጦቿም ያራቁታታል፡፡” (ሙስነድ 2/22ዐ)

ስድስተኛ ምልክት፡- የጪስ መቀስቀስ

አላህ እንዲህ ይላል
{ فَارْتَقِبْ يَوْمَ تَأْتِي السَّمَاءُ بِدُخَانٍ مُبِينٍ }{ يَغْشَى النَّاسَ هَذَا عَذَابٌ أَلِيمٌ } (الدخان : 10 ، 11)

‹‹ሰማይም በግልጽ ጭስ የምትመጣበትን ቀን ተጠባበቅ፡፡ ሰዎችን የሚሸፍን (በኾነ ጭስ) ይህ አሳማሚ ቅጣት ነው፡፡›› ዱኻን 1ዐ-11
            ሁዘይፋ በአስተላለፉትም ሀዲስ ነቢዩ صلى الله عليه وسلم “አስር ነገሮችን ሳታዩ ቂያማ አይቆምም በማለት ከአስሮቹ ጭስን ጠቅሰዋል፡፡”
(ሙስሊም 29ዐ1)
ሰባተኛው ምልክት፡- የቁርአን ወደ ሰማይ መውጣት

            ሁዘይፋ በአስተላለፉት ሀዲስ ነቢዩ صلى الله عليه وسلم እንዲህ ይላሉ

« يدرس الإسلام كما يدرس وشي الثوب حتى لا يدرى ما صيام ولا صلاة ولا نسك ، وليسرى على كتاب الله عز وجل في ليلة فلا يبقى في الأرض منه آية »
ከጊዜ ርዝመት የልብስ ጌጥ እንደሚጠፋው ኢስላም ይጠፋና ሰላት፣ ፆም፣ ሐጅ ምን እንደሆኑ አይታወቅም፤ በአንድ ሌሊት ምድር ላይ አንድ አንቀጽ ሳይቀር ይነሳል፡፡”   (ኢብን ማጃህ 4ዐ49 ሙስተድረክ 4/473)

ስምንተኛው ምልክት፡- ፀሐይ ከምዕራብ መውጣት

አላህ እንዲህ ይላል
{ يَوْمَ يَأْتِي بَعْضُ آيَاتِ رَبِّكَ لَا يَنْفَعُ نَفْسًا إِيمَانُهَا لَمْ تَكُنْ آمَنَتْ مِنْ قَبْلُ أَوْ كَسَبَتْ فِي إِيمَانِهَا خَيْرًا } (الأنعام : 158)

‹‹ከጌታህ ምልክቶች ከፊሉ በሚመጣ ቀን ከዚህ በፊት አማኝ ያልኾነችን ነፍስ እምነትዋ ወይም በእምነትዋ (ጊዜ) በጎ ያልሠራችን (ነፍስ ጸጸትዋ) አይጠቅማትም፡፡››                 አል አንዓም 158

            ይህን አንቀጽ ሲተነትኑ “ከጌታህ ምልክቶች ከፊሉ” የሚለውን ነቢዩ صلى الله عليه وسلم የፀሐይ ከምዕራብ መውጣት ነው ማለታቸውን ኢብን ጀሪር አጠበሪይ ተናግረዋል፡፡ (ተፍሲር ኢብን ጀሪር 8/97)

            ቡኻሪና ሙሰሊም ከአቡ ሑረይራ በአስተላለፉት ሀዲስም ነቢዩ صلى الله عليه وسلم እንዲህ ብለዋል

« لا تقوم الساعة حتى تطلع الشمس من مغربها فإذا طلعت فرآها الناس آمنوا أجمعون فذاك حين لا ينفع نفسًا إيمانها لم تكن آمنت من قبل أو كسبت في إيمانها خيرًا »

ፀሐይ ከምዕራብ ሳትወጣ ቂያማ አይከሰትም፣ ፀሐይ ከምዕራብ ስትወጣ ሲያይ ህዝቡ ሁሉ ያምናል ነገር ግን ከዛ በፊት አምና መልካምን ያልሰራች ነፍስ ያኔ ማመኗ አይጠቅማትም፡፡” (ቡኻሪ 4636 ሙስሊም 157)

ዘጠነኛ ምልክት፡- የእንስሳ መውጣት

            ስልሳ ክንድ የምትረዝም ረዣዥም እግሮችና ፀጉር ያላት የተለያዩ እንስሳዎች መልክ የያዘች እንስሳ ከቂያማ በፊት እንደምትመጣ ነቢዩ صلى الله عليه وسلم ተናግረዋል፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል
{ وَإِذَا وَقَعَ الْقَوْلُ عَلَيْهِمْ أَخْرَجْنَا لَهُمْ دَابَّةً مِنَ الْأَرْضِ تُكَلِّمُهُمْ أَنَّ النَّاسَ كَانُوا بِآيَاتِنَا لَا يُوقِنُونَ } (النمل : 82)
‹‹በእነርሱም ላይ (የቅጣት) ቃሉ በተረጋገጠ ጊዜ ሰዎቹ በአንቀጾቻችን የማያረጋግጡ እንደነበሩ የምትነግራቸውን እንስሳ ለእነርሱ ከምድር እናወጣለን፡፡›› ነምል 82
            ኢማም ሙስሊም ከአቡ ሑረይራ በአስተላለፉት ሀዲስ ነቢዩ صلى الله عليه وسلم እንዲህ ብለዋል
(ثلاث إذا خرجن لا ينفع نفسًا إيمانها لم تكن آمنت من قبل أو كسبت في إيمانها خيرًا ، طلوع الشمس من مغربها والدجال ودابة الأرض)
አንዲት ነፍስ አስቀድማ ካላነችና መልካም ካልሰራች ሶስት ነገሮች ከመጡ በኃላ ብታምን እምነቷ አይጠቅማትም ፀሐይ ከመግቢያዋ መውጣት፣ የደጃል መምጣትና የእንስሳ መውጣት” (ሙስሊም 158)
            ኢማም አህመድ ከአቡ ኢማማ በአስተላለፉት ሀዲስ ነቢዩ صلى الله عليه وسلم እንዲህ ይላሉ
« تخرج الدابة فتسم الناس على خراطيمهم ثم يغمرون فيكم حتى يشتري الرجل البعير فيقول ممن اشتريته فيقول : من أحد المخطمين »
አንዲት እንስሳ ብቅ ትልና ሰዎች አፍንጫ ላይ ምልክት ታደርጋለች፡፡” (ሙስነድ 5/268)
አስረኛው ምልክት፡- የእሳት መቀስቀስ

          ከፍተኛ ንዳድ ያላት እሳት ከዔድን ተነስታ ሰዎችን ወደ መሰብሰቢያ ቦታቸው ትሰዳለች፡፡ ከላይ በተጠቀሰው ሁዘይፋ በአስተላለፈው ሀዲስ ነቢዩ የመጨረሻው ምልክት ከየመን ከፍተኛ እሳት ይቀሰቀስና ሰዎችን ወደ መሰብሰቢያቸው ትሰዳለች፡፡” ብለዋል  (ሙስሊም 29ዐ1)
 እነዚህ ታላላቅ ምልክቶች በተከታታይ የሚከሰቱ ሲሆን ካለቁ በኃላ በአላህ ፈቃድ ቂያማ ይቆማል፡፡ አቡሑረይራ በአስተላለፉት ሀዲስ ነቢዩ
« خروج الآيات بعضها على إثر بعض ، يتتابعن كما تتابع الخرز في النظام »
የቂያማ ምልክቶች ጨሌ ገመድ ላይ እንደሚከታተለው አንዱ ከሌላው ጋር ተከታትለው ይከሰታሉ፡፡” ብለዋል (ሙዕጀሙል አውሰጥ 4283)






2 comments: