Tuesday, 21 February 2017

ለአዋቂ ልጅ ማጥባት

ለአዋቂ ልጅ ማጥባት
  
ከላይ እንደተብራራው የብዙሀኑ የፊቅህ ለቃውንት (ጁምሁር) አቋም የጥቢ ዝምድና ሁለት አመት ያለፈው ልጅ በማጥባት አይከሰትም የሚለው ነው። ሁለት አመት ያለፈው ህጻን ቢጠባ የጥቢ ዝምድናን ካላስገኘ አዋቂ ሰው ቢጠባ ፍጹም እርም ሊያደርግ አይችልም።በዚህ ጉዳይ ላይ ከምዕመናን እናት ኡሙ ሰለማ የተላለፈውን ተከታዩን ግልጽ ሀዲስ እናገኛለን፤

«እርም የሚያደርገው መጥባት አንጀት የደረሰ እና በጥቢ ዘመን ጡት ከመልቀቅ በፊት የተፈጸመ ነው» ሀዲሱን ቲርሚዚይ እና ኢብኑ ማጃህ ዘግበውታል አልባኒም በሶሂህ አቲርሚዚይ የትክክለኛ ሀዲሶች ጥንቅር ውስጥ አካተውታል። ሀዲሱን የዘገቡት አል ኢማም አቲርሚዚይ ረሂመሁላህ እንዲህ ብለዋል፤ «ይህ ትክክለኛ ሀዲስ ሲሆን ደረጃው (ሀሰኑን ሰሂህ) ነው። “እርም የሚያደርገው መጥባት ከሁለት አመት በፊት ከሆነ ብቻ ነው” የሚለው የሰሀቦችና ከእነሱም በኃላ የመጡት ታላላቅ ኡለማዎች ሁሉ አቋም ነው። ህፃኑ ሁለት አመት ከሞላው በኋላ የተከሰተ ማጥባት ምንንም እርም አያደርግም» ቱህፈቱል አህወዚይ ቅጽ 4 ገጽ 264

በተመሳሳይ ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ ለዓኢሻ «የጥቢ መዛመድ የሚከሰተው በረሀብ (ረሀብን የሚጋታ) ሲሆን ነው» ያሉትም ግልጽ መረጃ መሆኑ ተገልጿል። ሀዲሱን ቡኻሪ በቁጥር 2453 ሙስሊም በቁጥር 1455 ዘግበውታል

በዚህ ጉዳይ ላይ የብዙሀኑን አቋም የተጻረሩ ኡለማዎች መሰረት ያደረጉባቸው መረጃዎችም ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል። በመጀመሪያ ደረጃ አንቀጹ ላይ «አነዚያ ጡት ያጠቧችሁ እናቶቻችሁ፣ የጥቢ እህቶቻችሁም...» ኒሳዕ 23 ሲል “እድሜያችሁ ከሁለት አመት በታች እያለ” የሚል ገደብ አላስቀመጠም የሚል መከራከሪያ ነጥብ ያነሳሉ። በመሰረቱ ማጥባት የሚባለው ህጻን ልጅን የሚመግብ እና ጡት ከመልቀቅ በፊት ያለው መሆኑ በተለምዶ የታወቀ ከመሆኑ ባሻገር የኡሙ ሱለይም ሀዲስም በግልጽ ያስቀመጠው እውነታ ነውና ይህ መረጃ ሊሆናቸው አይችልም። በዋነኝነት የሚያነሱት መረጃ ግን፤ ቅድመ ኢስላም ይሰራበት በነበረውና ኋላ በሱረቱል አህዛብ አንቀጽ 5 በተከለከለው የማደጎ ልጅን እውነተኛ ልጅ የማድረግ ልማድ ሳሊምን ያሳደጉት አቡሁዘይፋና ባለቤቱ አብረውት በአንድ ክፍል ይኖሩ ስለነበር እና ልጁ ለአቅመአዳም ከደረሰ በኋላ በመቸገራቸው የአላህ መልዕክተኛ የሰጡትን መፍትሄ ነው። ሆኖም እነሱም ቢሆኑ ሀዲሱ እንደሚመለከተው ሰሀቢይ እንደ ሳሊም አይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ኖረው አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ (ለሀጃ) የሚፈፀም ብለው ገደብ አድርገውበታል። አል ኢማም አጦበሪ ይህንን አቋም ከደገፉት መካከል፤ አብዱላህ ኢብኑዙበይር፣ አልቃሲም ኢብኑ ሙሀመድን ጠቅሰዋል። አጧዕ፣ለይስ ኢብኑ ሳዕድ፣ ኢብኑ ሀዝም እና ዳውድ አዟሂሪይ አቋሙን እንደሚጋሩ ይነገራል። (ፈትሁልባሪ 9/147)  

ያቀረቡት መረጃ እንደሚከተለው ይነበባል፤

(የአቡሁዘይፋ ባለቤት ሰህላ ቢንት ሱሀይል መልእክተኛው ዘንድ መጥታ ሳሊምን ህጻን አድርገን እንቆጥረው ስለነበር ከኔና ከአቡሁዘይፋ ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ ያድር ነበር። ያየኛልም፤ አሁን አላህ የቁርአን አንቀጽ አውርዷልና (አህዛብ 5) ምን ይመክሩኛል? በማለት ጠየቀች። የአላህ መልዕክተኛም፦ “አጥቢው” አሏትና አምስት ግዜ አጠባችው። ከዚያን ግዜ በኋላ ልክ እንደ ልጇ ሆነ…)
አቡዳውድ (2061) ነሳኢ (3324) እና ሌሎችም ዘንድ ተዘግቧል

ሀዲሱ በምን መልኩ ሳሊም እንደጠባ አይገልጽም። ሆኖም የሀዲስ ተንታኙ አል ኢማም አን’ነወዊይ እንዲህ ብለዋል፤ «“አጥቢው” የሚለውን አስመልክቶ አልቃዲ ኢያድ እንዳሉት “ሰውነቷን ሳይነካ ታልቦ ጠጥቶት ነው የሚሆነው” ይህ ጥሩ ትንታኔ ነው። ነገር ግን ተልቅ ሆኖ እንዲጠባ በልዩ መልኩ እንደተፈቀደለት ሁሉ ይህም ለሀጃ ተፈቅዶለት ሊሆን ይችላል አላህ ያውቃል» ብለዋል። በተለይ ደግሞ ሳሊም የማደጎ ልጇ እንደመሆኑ ልክ እንደልጇ የምታየውና እሱም እንደ እናቱ የሚያያት ከመሆኑ አንጻር ነገሩ ቀለል ያለ ነው።

ሀዲሱ ሲጠናቀቅ የምዕመናን እናቶች ቢቃወሟትም ዓኢሻ ግን ይህንን የሳሊም ክስተት መረጃ በማድረግ ለተመሳሳይ ሀጃ መጠቀም እንደሚቻል አቋሟን ትገልጽ ነበር። ከዘይነብ ቢንት ኡሙ ሰለማ በተዘገበ ሀዲስ አዒሻን ስትጠይቃት ሳሊም ያገኘውን ፍቃድ በመጥቀስ መልሳለች (ሙስሊም ቁጥር 1453)
 
ብዙሀኑ ከልካይ ኡለማዎች ምላሽ፦

ይህ የሳሊም ሀዲስ እሱን ብቻ የተመለከተ ነው የሚለው የምእመናን እናቶች ምላሽ እንዳለ ሆኖ። ሀዲሱና ብይኑ በሌሎቹ ህጻን መሆንን መስፈርት በሚያደርጉ ሀዲሶች የተሻረ (ነስኽ የተደረገ) ነው የሚለውም ምላሻቸው ነው።

በርግጥ ይህንን የሳሊምን ክስተት ለተመሳሳይ ሀጃ መጠቀም የአዒሻ የግል ግንዛቤና አቋም ነበር። ሆኖም ግን በሌሎቹ የምእመናን እናቶች ዘንድ ተቀባይነት እንዳልንነበረው የሚያመላክቱ ብዙ መረጃዎች አሉ።

ከምእመናን እናት ከኡሙ ስለማ በተዘገበ ሀዲስ «ሌሎች የመልእክተኛው ባለቤቶች ማንም ሰው (በልጅነቱ) ካልጠባ በቀር በዚህ አይነት ጥቢ እነሱ ዘንድ እንዲገባም ሆነ እንዲመለከታቸው አልፈቀዱም። ለዓኢሻም “ለሳሊም በልዩ ሁኔታ የፈቀዱት “ኻስ” ፈቃድ ነው ብልን እናምናለን ሲሉ አስረድተዋታል።» ሙስሊም በቁጥር 1454 ዘግበውታል

የትልቅ ሠው መጥባት ወጤት እንደሌለው የሚገልጹ የሰለፎች አስተምህሮቶች ይገኛሉ።

1. ከዓጧዕ አልዋዲዒይ በተላለፈ መልዕክት፤ “አንድ ሰው ኢብኑ መስዑድ ዘንድ መጣና፤ የባለቤቴ ጡት ወተት ይዞ ተወጠረና እየጠባው ተፋሁት እንም አባሙሳ ዘንድ ሄጄ ስጠይቀው፤ ሀራም ሆናብሀለች አለኝ” ሲለው ኢብኑ መስዑድ ተነሳ እኛም ተከተልነውና አቡሙሳ ዘንድ ሄደ፤ ከዛም ለዚህ ሰው ምን አይነት ፈትዋ ነው የሰጠኸው? በማለት ጠየቀውና ምላሹን ሲነግረው፤ የጠያቂውን እጅ በመያዝ “አሁን ይህ ሰው ጡት የሚጠባ ነውን? ጥቢ ማለት በሰውነት ውስጥ ስጋና ደምን የሚሰራ ነው። አቡሙሳም ይህ አዋቂ ሰው በመካከላችን እያለ እኔን አትጠይቁ በማለት ተናገረ። (አብዱረዛቅ ሙሶነፍ ቅጽ 7 ገጽ 463 ላይ ጠቅሰውታል)  በሌላ አገላለጽ አቡዳዉድ በቁጥር 2059 ዘግበውታል «አጥንትን ያጎለበተና ስጋን ያበቀለ እንጂ ጥቢ አይባልም በማለት ሲመልስ፤ አቡ ሙሳ “ይህ አዋቂ ሰው በመካከላችሁ እያለ እኔን አትጠይቁኝ አለ» ሶሂህ አቡዳውድ ላይ አልባኒ ሶሂህ ብለውታል

2.ማሊክ ከናፊዕ ባስተላለፉት ሀዲስ ኢብኑ ኡመር እንዲህ ብለዋል፤ «በህጻንነቱ ካልጠባ ሰው ጋር የጥቢ ዝምድና የለም። ትልቅ ሰው የጥቢ ዘመድ አይሆንም» አል ሙወጠእ 2/603

3. ማሊክ ሙወጠእ ላይ ሶሂህ በሆነ ዘገባ አብዲላህ ኢብኑ ዲናር ከአብዱላህ ኢብኑ ኡመር አባቱ ኡመር እንዲህ ማለቱን ዘግበዋል፤ «ጥቢ ማለት የህጻንነት መጥባት ነው!» አልሙወጠእ 2/606


ብዙ ኡለማዎች ዘንድ ፈትዋ የሚሰጥበት አቋም ትልቅ ሰው ቢጠባ ዝምድናን አያስገኝም ከጋብቻም አይከለክልም። የሳሊም ሃዲስም እርሱን ብቻ የተመለከተ ነው የሚለው ነው። ከዘመናችን ኡለማዎች ኢብኑ ባዝ፣ ልጅነቱዳኢማህ ይህንኑ ምላሽ ይሰጣሉ። መጅሙዕ ፈታዋ ሊብን ባዝ 22/264 ላይ ፈታዋለጅናህ 21/41 ይመልከቱ። አንዳንዶች ደግሞ ሀዲሶቹን ሁሉንም ተግባራዊ ያደረገ ሀሳብ ያቀርባሉ።

አል ኢማም አሶንዓኒይ እንዲህ ብለዋል፤ «የሰህላህ ሀዲስን እና ለሎቹን ሀዲሶች ከማስታረቅ አንጻር ጥሩ የሚባለው የኢብኑ ተይሚያህ ንግግር ነው። ኢብኑ ተይሚያህ “ህጻን ሆኖ መጥባት ተቀባይነት ያለው መስፈርት ነው። ሆኖም ልክ ሳሊም ከአቡሁዘይፋ ባለቤት ጋር እንደነበረው ሁኔታ ቤት ውስጥ መገኘቱ የግድ ሆኖ ሳለ፤ ለሴቶች ለመከለል አስቸጋሪ ሲሆን ረዷዓ ቢጠቀም የዝምድና ተጽዕኖ ይፈጥራል” ብለዋል። በሳሊም ብቻ ከመገደብ ወይም ተሽሯል ብሎ መልስ ከመስጠት ቋንቋዊ መርሆዎችንም ጥቅም ላይ ከማዋል አንጻር ይህ ንግግራቸው ጥሩ ማስታረቂያ ነው። እነዚህኑ ምክኒያቶች በመጥቀስ የማስታረቂያውን ሀሳብ ተማሪያቸው ኢብኑል ቀዩም ዛዱልመዓድ ላይደግፈውታል» ሱቡሉሰላም ቅጽ 2 ገጽ 313

እንዲህ አይነት ሁኔታዎችን በማገናዘብ የሳውዲ ቋሚ የፈትዋ ኮሚቴ ቅጽ 21 ገጽ 40 እና 46 ላይ የሶስት እና የስምንት ወይም የዘጠኝ አመት ልጆች በመጥባታቸው ዝምድናን አጽድቀዋል።

ሸይኽ ኢብኑ ኡሰይሚን የሳሊም ሀዲስ እሱን ብቻ የተመለከተ አይደለም የሚለውን አቋም ቢመርጡም

« እኔ ዘንድ የትልቅ ልጅ ጥቢ ተጽዕኖ አይፈጥርም። በሁሉም ሁኔታ ልክ እንደ ሳሊምና አቡሁዘይፋ  አይነት ሁኔታ ብቻ ሲሆን ነው ተጽዕኖ የሚፈጥረው። አላህ የማደጎ ልጅ መያዝን ስለከለከለ የሳሊም አይነት ሁኔታ ላይ ያለ ሰው አይኖርምና አሁን ሀዲሱን መተግበር የማጥባት ዝምድናን አይፈጥርም።ሴትንም ክልክል አያደርግም። ከሁለት አመቱ በፊት እንደውም ጡት ሳይለቅ ከጠባ ብቻ ነው የሚለው አቋም ሚዛን ይደፋል… ከዚህ አንጻር ስናየው ይህ አቋም ከአብዛኛው ኡለሞች አቋም ጋር ይታረቃል በማለት ሃሳባቸውን አስቀምጠዋል። (ሸርሁል ሙምቲዕ ቅጽ 13 ገጽ 435 እና 436)

ይህ የጥቢን ህግጋት በተመለከተ አስፈላጊ ያልኳቸውን ነጥቦች የዳሰስኩበት ጽሁፍ ሲሆን አላህ እውቀትን እና መልካም ስራን ይለግሰን ዘንድ እለምነዋለሁ።

አቡጁነይድ ሳላህ አህመድ

ጥር 16/2009

አብረው ከጠቡት ሰው ጋር የስህተት የተፈጸመ ጋብቻ

አብረው ከጠቡት ሰው ጋር የስህተት የተፈጸመ ጋብቻ

የጥቢ ዝምድና መኖሩ በምን ይወሰናል የሚለውን መልስ ማግኘት አጀንዳውን ለመዳሰስ መሰረት ነው።
ሁለት ታማኝ ወንዶች ወይም አንድ ወንድና ሁለት ሴቶች የመሰከሩበት የምስክር ማስረጃ ካለ የጥቢ ዝምድና ይጸድቃል። ይህ ከውዝግብ የራቀና ሁሉንም ኡለማዎች የሚያስማማ የጋራ አቋም ነው። የሀንበሊ መዝሀብ አቋም ከተከታዩ ሀዲሳዊ መረጃ በመነሳት፤ አንዲት በዲኗ የታመነች ሴት እኔ እገሌን፣ እገሌን አጥብቻለው ብላ ማረጋገጫ ከሰጠች የጥቢ ዝምድና መኖሩ ይረጋገጣል ብለዋል (አልሙግኒ 9/222) ሌሎቹ ዘንድ ግን ሀዲሱ አሻሚ ሁኔታዎች ሲከሰቱ ጥንቃቄ ማድረግን የሚያመለክት ብቻ ነው።

ከኡቅበት ቢን ሀሪስ በተዘገበ ሀዲስ ኡቅባህ እንዲህ ይላል። «አንዲት ሴት አገባው። አንዲት ጥቁር ሴቲዮ መጣችና አንተንም እሷንም አጥብቻችኋለው አለችኝ። ነብዩ ዘንድ መጣውና የእገሌን ልጅ እገሊትን አግብቼ ነበር። አንዲት ጥቁር ሴትዮ መጥታ ውሸቷን ሁሌታችሁንም አጥብቻችኋለው አለችን ስላቸው ትተውኝ ዞር አሉ። አሁንም ከፊትለፊታቸው መጥቼ ዋሽታ እኮ ነው አልኳቸው። እሳቸውም “ባለቤትህን ተዋት፤ ሁለታችሁንም አጥብቻለው እያለች እንዴት ይሆናል” በማለት መለሰች» በሌላ ዘገባም የአላህ መልዕክተኛ “እየተወራ እንዴት ይሆናል?” አሉት»  ቡኻሪ በቁጥር 2517 ዘግበውታል

ኢብኑ ሀጀር ሀዲሱን ሲያብራሩ እንዲህ ብለዋል፤ «“እየተወራ እንዴት ይሆናል?” የሚለው ንግግራቸው የሚጠቁመን ባለቤቱን እንዲለያት ያዘዙት ንግግርሯ ትክክል ቢሆን ሀራም እንዳይፈጸም መሆኑን ነው። ይህ ደግሞ ጥንቃቄን መሰረት ካደረገው የብዙሀኑ ኡለማዎች አቋም ጋር አብሮ ይሄዳል። ምስክርነቷን በመቀበል ነው ያሉም አሉ» (ፈትሁል ባሪ 4/374)

በጥቅሉ ይህ ሀዲስ በህጻንነት እንጅ በትልቅነት የተፈጸመ መጥባት ዝምድናን እንደማይፈጥር ከሚያሳዩ መረጃዎች መክካከል ይጠቀሳል። በተጨማሪም በዚህ ጉዳይ ላይ ቸልተኝነት እንደማይገባ ያስገነዝባል።

የሀነፊ መዝሀብ ምሁራን አንድ ወንድና ሁለት ሴቶች የመሰከሩበት ምስክርነት ካልሆነ አይቀበሉም (በዳኢዑ-ሰናኢዕ 4/14) ፤ ማሊኪያዎችም አንዲት ሴት እና አንድ ወንድ መመስከር አለባቸው ብለዋል (ቢዳየቱል ሙጅተሂድ 2/29) ፤ የሻፊዒ ኡለማዕ አራት ሴቶች መመስከር አለባቸው ብለዋል (ሙግኒል ሙህታጅ 3/224) ፤ ሁሉም ለያዙት አቋም መነሻዎች አሏቸው።

ኢብኑ በጧል ይህንን ሀዲስ ሲያብራሩ፤ «ከኢብኑ አባስ፣ ከጧውስ፣ ከዙህሪ፣ ከአውዛዓኢይና ከአህመድ እንዲሁም ከኢስሀቅ እንደተዘገበው፤ ታማኝ የሆነች አንድ ሴት ከመሠከረች በቂ መሆኑን ነው ቢሉም እንደትምል የደረጋል ብለዋል። ይህንን ሀዲስም መረጃ ያደርጋሉ። ከአውዛዒይ እንደተዘገበው ደግሞ ከመጋባታቸው በፊት ከመሰከረች ተቀባይነት አለው ከተጋቡ በኋላ ግን ተቀባይነት የለውም ብለዋል» ከአንድ በላይ ምስክርነትን መስፈርት ያደረጉ አቋሞችን ከዘረዘሩ በኋላ « ከመጀመሪያው አቋም ውጭ ያለውን ያንጸባረቁት ኡለማዎች በዚህ ሀዲስ  “እየተወራ እንዴት ይሆናል?” ያሉትን ጥንቃቄን ከማስቀደም ብቻ እንጂ መለያየታቸው ዋጂብ ሆኖ አለመሆኑን ይጠቅሳሉ። አሊይና ኢብኑ አባስን ተመሳሳይ ጥያቄ ቀርቦላቸው፤ ለጥንቃቄ ቢተዋት መልካም ነው። ነገር ግን እርሱ ላይ እርም ማድረግ ለማንም አይቻለውም። ኡመር ኢብኑል ኸጧብም የአንድን ሴት ብቻ ምስክርንት እንዳላጸደቁ ተነግሯል» ሸርህ ሶሂሁል ቡኻሪ ቅጽ 7 ገጽ 202

የአላህ መልዕክተኛ ጥንቃቄን ማስቀደማቸውን የሚያስረዳ ሌላ ዘገባ አለ። አብዱላህ ኢብኑ መሊካ ከዑቅባ ሰምቻለሁ ይበልጥ የማስታውሰው ግን ጓደኛዪ ከሱ ሰምተው የነገሩኝን ነው ካሉ በኋላ፤ “ኡሙ ያህያ ቢንት አቢ ኢሐብን አገባሁ እና አንዲት ጥቁር ሴት መጥታ አጥብቻችኋለው አለችን። ለመልእክተኛው ስነግራቸው ዝም አሉኝ ደገምኩላቸው ዝም አሉኝ አሁንም ደገምኩላቸውና “ውሸቷን እኮ ነው” ስላቸው፤ “ያለችውን ብላለች፤ አንተ ውሸቷን ስለመሆኑ ምን አሳወቀህ?” ልጅቷን ተዋት አሉኝ» ጦበራኒ ዘግበውታል አልባኒም ሰሂህ ብለውታል (አል ኢርዋዕ 7/225)

በአንድ ባልና ሚስት መካከል መስፈርቶች ተሟልተው በተገኙበት መልኩ የተከሰተ የጥቢ ተዛምዶ መኖሩ ከተረጋገጠ መለያየታቸው ግድ ይሆናል!!

ህፃኑ ከሁለት አመት በፊት ጡት እንዲለቅ ማድረግ ይፈቀዳልን?

ህፃኑ ከሁለት አመት በፊት ጡት እንዲለቅ ማድረግ ይፈቀዳልን?

ህጻኑ ሁለት አመት ሳይሞላው ጡት እንዲተው ለማድረግ የተቀመጡ መስፈርች ከተሟሉ ይፈቀዳል።
ጡት እንዲተው መደረጉ ህጻኑን የሚጎዳው ካልሆነ
ጡት እንዲተው የሚደረገው በሁለቱ ወላጆቹ ስምምነት ከሆነ 

«እናቶችም ልጆቻቸውን ሙሉ የኾኑን ሁለት ዓመታት ያጥቡ፡፡ (ይህም) ማጥባትን መሙላት ለሻ ሰው ነው… (ወላጆቹ) ከሁለቱም በኾነ መዋደድና መመካከር (ልጁን ከጡት) መነጠልን ቢፈልጉ በሁለቱም ላይ ኃጢኣት የለባቸውም፡፡» [አልበቀራ:233]

ሸይኽ አብዱረህማን አስ’ሰዕዲይ ረሂመሁላህ አንቀጹን ሲያብራሩ እንዲህ ብለዋል፤ «አባትና እናት ህጻኑ ሁለት አመት ሳይሞላው ጡት መጥባትን ሊያስተውት ከፈለጉ፤ “ለልጁ ጠቃሚው የትኛው ነው” የሚለው ላይ ሁለቱ ተማክረው ከተስማሙና ፈቃደኛ ከሆኑ ማስተው ይፈቀድላቸዋል። አንቀጹ በውስጥ ታዋቂነት እንደሚያመለክተው  ከሁለቱ የአንዱ ብቻ ፍላጎት ከሆነ ወይም ደግሞ ለልጁ የማይበጅ ከሆነ ጡት ማስለቀቅ አይፈቀድም» ሳእዲ ተፍሲር ገጽ 104

ተያያዥ ነጥቦች

1. ህጻኑ የጠባው የሰው ወተት መሆን አለበት፦

ሁለት ህጻናት ከአንድ ፍየል ቢጠቡ ወንድማማቾች አይሆኑም፤ በዝምድናም አይተሳሰሩም። ኢብኑልሙንዚር አል-ኢጅማዕ በተሰኘው መጽሀፋቸው ገጽ 77 ላይ የሊቃውንቶችን አጠቃላይ ስምምነት “ኢጅማዕ” አስተላልፈዋል። በተመሳሳይ መልኩ ከአንድ የዱቄት ወተት ቢጠቡ ዝምድና አያስከትልም (የሳውዲ ቋሚ የፈትዋ ኮሚቴ ቅጽ 21 ገጽ 18) ምክኒያቱም የማጥባት ወንድምነት አጥቢዋ ሴት በማጥባቷ ምክንያት እናት መሆኗን ተከትሎ የሚከሰት ዝምድና ነው። እናትነት ባልተከሰተበት ሁኔታ ወንድማማችነት አይከሰትም።

2.ህጻኑ የጠባው ወተት መሆን አለበት፦

የአጥቢዋ ጡት ወተት ባይኖረውና ህጻኑ ውሀ ቢጠባ ዝምድናን አያስገኝም (የሳውዲ ቋሚ የፈትዋ ኮሚቴ ቅጽ 21 ገጽ 15) በተመሳሳይ መልኩ አንዳንዶች እንደሚያስቡት ደም መለገስ በደም ለጋሽና በደም ተቀባይ መካከል የጥቢ ዝምድና አያስኝም (የሳውዲ ቋሚ የፈትዋ ኮሚቴ ቅጽ 21 ገጽ  145)

3. ከሟች ሴት ቢጠባ፦

በአንዳንድ የጦርነት ጊዜያት እንደሚከሰተው እናት ህይወቷ ካለፈ በኋላ ህጻኑ ቢጠባ ዝምድና ይከሰታል ወይስ አይከሰትም? አብዛኞቹ የፊቅህ ጠበብቶች በህይወት መኖር መስፈርት ስላልሆነ እና ወተቱ የሙት ብይን ስለሌለው ዝምድና ይከሰታል የላሉ። ሆኖም የሻፊዒያ ሊቃውንት ህይወቷ ካለፈ በኋላ ከሀላልና ሀራም ማዕቀፍ ውጭ ስለሆነች ልክ ከእንስሳ መጥባት እንደማያዛምደው ሁሉ አያዛምድም ይላሉ። (አልሙግኒ 9/198)

4. ወተቱ ግንኙነትን መሰረት ያላደረገ ከሆነ፦

ለምሳሌ ግንኙነት ያላደረገች ድንግል የሆነች ሴት ብታጠባ ሁክሙ ምን ይሆናል? የሀንበሊ መዝሀብ ኡለማዎች፤ ይህ ብዙ ግዜ የማይከሰት ከመሆኑ ጋር ህጻናትን ለመመገብ የተለመደ መንገድ ስላልሆነ ልክ እንደ ወንድ ለጅ ወተት የሚታይ እንጂ ዝምድናን ለማስገኘት ከቁብ የሚቆጠር አይደለም ብለዋል (አልሙግኒ 9/206) ሆኖም ብዙሀኑ ኡለማዎች “ጁምሁሮች” ዘንድ ይህ ወተት ዝምድናን የሚያስገኝና እርም የሚያደርግ ነው። ልጁ የጥቢ ልጇ ነው አባት አይኖረውም። ይህ የተለመደ ባይሆንም ነገር ግን በቁርአን ላይ የምናገኘው ፈቃድ አጥቢዋ ሴት መሆንዋን እንጂ አግብታ በግንኙነት ምክንያት ጡቷ ወተት የሞላ የሚል መስፈርት የለውም ይላሉ። ኢብኑልሙንዚር አል-ኢጅማዕ ገጽ 77 ላይ የሊቃውንቶችን አጠቃላይ ስምምነት “ኢጅማዕ” አስተላልፈዋል።

5. አጥቢዋ ሙስሊም ካልሆነች፦ 

አይሁድ ወይም ክርስቲያን የሆነች ሴት ብታጠባው ዝምድና እንደሚገኝ ግልጽ ነው። ሙስሊም ባትሆንም መስፈርቶች በተሟሉበት ሁኔታ ጋብቻም የተከለከለ ባለመሆኑ ማጥባትና ልጅን መንከባከብም ጋብቻን ተከትሎ የሚፈቀድ ነው። በተመሳሳይ መልኩ ሙስሊም ሴት ሙስሊም ላልሆነ ልጅ ማጥባት ይፈቀድላታል።
(የሳውዲ ቋሚ የፈትዋ ኮሚቴ ቅጽ 21 ገጽ 61)
ሆኖም ከአህለል ኪታብ ሴቶች ጋር የሚፈጸም ጋብቻ ከሚያስከትላቸው ቤተሰባዊና ማህበራዊ ችግሮች በመነሳት የማይመከር እንደመሆኑ ሙስሊም ካልሆኑ ሰዎች ጋር የጡት ዝምድና መፍጠርም አይመከርም።

ጡት መጥባት በራሱ የሚያስከትለው የባህሪ ተጽዕኖ እንዳለ በመግለጽ ኡመር ኢብኑልኸጧብ አይሁድና ክርስቲያኖች ዘንድ ልጆች እንዲጠቡ ማድረግን አስጠንቅቀዋል።

6. ታልቦ ቢጠጣ፦

የጥቢ ትስስር የሚከሰተው፤ ወተቱ ለህጻኑ በምግብነት በማገልገሉ፣ አጥንቱንና ስጋውን በማዳበሩ፣ ረሀብን በማስታገሱ ነው። ወተቱ ታልቦ በእቃ ወይም በጡጦ እንዲወስደው ቢደረግ ይህ ሁሉ ጥቅም ይገኛል። ስለዚህም ከማጥባት ውጭ ባለ ማንኛውም መንገድ ወተቱ ወደ ሆዱ እንዲደርስ ቢደረግ እንደ ጥቢ ይቆጠራል። አምስት ግዜ ከተደገመ የጥቢ ዝምድናን ያስገኛል። ይህ የብዙሀኑ የፊቅህ ሊቃውንት (ጁምሁር) አቋም ነው።         (አልሙግኒሊብን ቁዳማህ 8/ 139 ፤ አልካፊ ሊብን ቁዳማህ 5/65 ፤ የሳውዲ ቋሚ የፈትዋ ኮሚቴ ቅጽ 21 ገጽ 12)

7.ከሌላ ነገር ጋር ተቀላቅሎ ቢጠጣ፦

በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው ሚዛን ደፊ አቋም ወተቱ ከሌላ ነገር ጋር ቢቀላቀልም በፐርሰንት ሲታይ ብዙ ሆኖ ከተገኘ መዛመድን ያስከትላል የሚለው ነው። ከሀነፊ መዝሀብ ኡለማዎች የአቡ ዩሱፍ እና የሙሀመድ ቢን ሀሰን አቋም ሲሆን፤ የማሊኪያ የሻፊዒያና የሀንብሊያ መዝሀቦች ሁሉ አቋም ነው። (በዳኢዑ ሰናዒዕ 4/9 ፤ ሙግኒል ሙህታጅ 3/410 ፤ አልሙግኒ 9/197 ፤ አል ኢንሷፍ 9/337 ፤ ከሻፉል ቂናዕ 5/447)
ሸይኽ ኡሰይሚን ህጻኑ ከመድሀኒት ጋር ተቀላቅሎ ቢሰጠው  ወተቱ ወደ ሆዱ የሚደርስና ተጽእኖ የሚፈጥር ከሆነ እንደ ጥቢ ይታያል ብለዋል (ኑሩን አለደርብ ቅጽ 3 ገጽ 1867)

8.እርግጠኝነትና ጥንቃቄ፡-

የጥቢ ዝምድናን ለማጽደቅ እርግጠኝነት ያስፈልጋል። የማጥባት ዝምድና ከጋብቻ የሚከለክል ዝምድና የሚፈጠረበት ትስስር ነውና ሳያረጋግጡ በቸልታ ዝምድናን ማወጅ ተገቢ አይሆንም። ከእናታችን ዓኢሻ በተላለፈ ሀዲስ የአላህ መልዕክተኛ እቤት ሲገቡ አንድ ሰው እቤት ነበርና “ይህ ሰው ማነው?” በማለት ጠየቁኝ፤ የጥቢ ወንድሜ ነው አልኳቸው። እርሳቸውም “አዒሻ ሆይ! ወንድሞቻችሁ እነማን መሆናቸውን አስተውሉ። የጥቢ መዛመድ የሚከሰተው በረሀብ ሲሆን ነው” አሉ። ሀዲሱን ቡኻሪ በቁጥር 2453 ሙስሊም በቁጥር 1455 ዘግበውታል

ታላቁ የቡኻሪ ተንታኝ ኢብኑ ሀጀር እንዲህ ብለዋል፤ «የዚህ ትርጉም፤ ምን እንደተከሰተ አስተዉሉ፤ ከጠባበት ግዜ እና ከጠባው የወተት መጠን አንጻር መስፈርቶቹን ያሟላ ጥቢ ነውን? የጥቢ ዝምድና የሚኖረውና ተጽዕኖ የሚያሳድረው መስፈርትቹ ሲሟሉ ነው። ሙሀለብ እንዳሉት፤ የዚህ ወንድማማችነትን ምክንያትመለስ ብላችሁ ቃኙ፤ ጥቢ እርም የሚያደርገው መጥባት ረሀብን በሚያጠፋበት የህጻንነት እድሜ ነው…ጥቢ ከረሀብ የሚያላቅቅ ካልሆነ ቦታ አይሰጠውም እንደማለት ነው!»  ፈትሁልባሪ ቅጽ 9 / ገጽ 148

በተመሳሳይ መልኩ ለጉዳዩ ቁብ አለመስጠትና ልጆችን በጋራ ማጥባት ትልቅ ስህተት ነው። በአንዳንድ የህክምና ተቋማትም የእናት ጡት ታልቦ ሲገባ የመቀላቀል አደጋ እንዳይደርስበት ማስጠንቀቅና መከታተል ያስፈልጋል። ሙስሊም ሴት አንድን ህጻን ማጥባት ስትፈልግ እርሱንም የሚያዛምድ ተግባር ስለሆነ ከባለቤቷ ጋር መማከሯ ግዴታ ነው። በጥቅሉ የሌላ ሰውን ልጅ ከማጥባት በፊት አስፈላጊነቱን እና ተጽዕኖዎቹን ማስተዋል ግድ ይለናል።


የጥቢ ዝምድና መስፈርቶች

የጥቢ ዝምድና  መስፈርቶች

የጥቢ ዝምድና  እንዲኖር ተከታዮቹ መስፈርቶች መሟላት አለባቸው።

1 የሚጠባው ህጻን ከሁለት አመት በታች መሆን አለበት፦

ህፃን ልጅ በሚጠባበት እድሜ (ጡት ሳይለቅ) በምግብነት የጠባው መሆን አለበት፤ ይህም  በህጻኑ በመጀመሪያዎቹ ሁለት አመታት የእድሜ ክልል ውስጥ ነው። የመጀመሪያዎቹ ሁለት አመታት ህጻናትን ማጥባት የተሟላና መደበኛ የማጥባት ስርአት መሆኑ በቁርአን በሱረቱል ሉቅማን 14 እና በሱረቱል በቀራህ 233 ላይ ተጠቁሟል።
አላህ እንዲህ ብሏል፤
(وَالْوَالِدَاتُ يُرْضِعْنَ أَوْلَادَهُنَّ حَوْلَيْنِ كَامِلَيْنِ لِمَنْ أَرَادَ أَنْ يُتِمَّ الرَّضَاعَةَ) {البقرة : 233}
«እናቶችም ልጆቻቸውን ሙሉ የኾኑን ሁለት ዓመታት ያጥቡ፡፡  (ይህም) ማጥባትን መሙላት ለሻ ሰው ነው» አል በቀራህ 233

በዚህ ጉዳይ ላይ ከምዕመናን እናት ኡሙ ሰለማ የተላለፈውን ተከታዩን ግልጽ ሀዲስ እናገኛለን፤

عَنْ أُمِّ سَلَمَةَ رضي الله عنها قَالَتْ : قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ : (لَا يُحَرِّمُ مِنْ الرِّضَاعَةِ إِلَّا مَا فَتَقَ الْأَمْعَاءَ فِي الثَّدْيِ، وَكَانَ قَبْلَ الْفِطَامِ) والحديث صححه الألباني في صحيح الترمذي

«እርም የሚያደርገው መጥባት አንጀት የደረሰ እና በጥቢ ዘመን ጡት ከመልቀቅ በፊት የተፈጸመ ነው» ሀዲሱን ቲርሚዚይ እና ኢብኑ ማጃህ ዘግበውታል አልባኒም በሶሂህ አቲርሚዚይ የትክክለኛ ሀዲሶች ጥንቅር ውስጥ አካተውታል። ሀዲሱን የዘገቡት አል ኢማም አቲርሚዚይ ረሂመሁላህ እንዲህ ብለዋል፤ «ይህ ትክክለኛ ሀዲስ ሲሆን ደረጃው (ሀሰኑን ሰሂህ) ነው። “እርም የሚያደርገው መጥባት ከሁለት አመት በፊት ከሆነ ብቻ ነው” የሚለው የሰሀቦችና ከእነሱም በኃላ የመጡት ታላላቅ ኡለማዎች ሁሉ አቋም ነው። ህፃኑ ሁለት አመት ከሞላው በኋላ የተከሰተ ማጥባት ምንንም እርም አያደርግም» ቱህፈቱል አህወዚይ ቅጽ 4 ገጽ 264

በዚህም መሰረት የጥቢ ዝምድና  ሁለት አመት ያለፈው ልጅ በማጥባት አይከሰትም። እርም የሚያደርገው ማጥባት ህጻኑ ሁለት አመት ከመሙላቱ በፊት ያለው ብቻ ነው። ከሁለት አመቱ በፊት ጡት የለቀቀ ቢሆን እንኳ ቢጠባ ዝምድናው ይገኛል። ዋናው ከሁለት አመቱ አለማለፉ እንጂ ጡት መልቀቁ አይደለም። ይህ የብዙሀኑ የሻፊኢያ ይሀንበሊያና የማሊክ እንዲሁም የከፊል ሀነፊያ የፊቅህ ለቃውንት አቋም ነው (አልሙግኒ 9/201 ይመልከቱ)

ይህ የማጥባት ህግ እስከ 30 ወራት ይዘልቃል፤ ህጻኑ ጡት ለቀቀም አለቀቀ የሚታየው 30 ወራት አለመሙላቱ ነው ያሉት የሀነፊ መዝሀብ ኡለማዎች ሲሆኑ ተከታዩን የቁርአን አንቀጽ መረጃ አድርገዋል። (አል መብሱጥ ሊሰርሰኺ 5/136)
{وَحَمْلُهُ وَفِصَالُهُ ثَلَاثُونَ شَهْرًا} (سورة الأحقاف: 15)
«እርግዝናውና ከጡት መለያውም ሰላሳ ወር ነው፡፡» አል አህቃፍ 15

የሀነፊ ኡለማዎች መረጃ ያደረጉት ይህ አንቀጽ አነስተኛውን የእርግዝና ግዜ 6 ወር አካቶ የመጣ በመሆኑ ሁለት አመት (24 ወራት) ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ነው። ሌሎች መረጃዎችም ሁለት አመት የሚለውን ከማጠናከራቸው ከሁለት አመት በፊት የሚለው አንጻር ሚዛን ደፊ ነው።






2 አምስት ግዜ መጥባት፦ 

ህፃኑ ጠግቦ ሙሉ በሆነ ጥቢ አምስት ጊዜ የጠባና በራሱ ጊዜ ጡት የተወ መሆን አለበት። አንድ ግዜም ቢጠባ በቂ ነው ያሉ ኡለማዎች እንዳሉ ሁሉ በሶስት እና በአስር የገደቡትም አልጠፉም። ሆኖም አምስት ግዜ መጥባቱ ግዴታ ነው የሚሉት የሻፍኢያ እና የሀንበሊያ መዝሀብ ኡለማዎች አቋም ሚዛን የሚደፋና በጠንካራ መረጃዎች የተደገፈ ነው። (አል ሙግኒ 9/192 ፤ አል ሙሀዘብ 2/156)
አምስት ጊዜ መጥባት መስፈርት ለመሆኑ መረጃው ተከታዩ የምእመናን እናት አዒሻ ያስተላለፈችው ሀዲስ ነው፤

عن عائشة رضي الله عنها قالت : "كان فيما أنزل من القران عشر رضعات معلومات يحرمن ثم نسخن بخمس معلومات فتوفي رسول الله صلى الله عليه وسلم وهن فيما يقرأ من القرآن."  رواه مسلم
የምእመናን እናት አዒሻ እንዲህ ብለዋል፤
«በቁርአን ላይ ከወረዱት አንቀፆች መካከል "አስር የታወቁ ጥቢዎች እርም ያደርጋሉ” የሚል ነበረ፤ በኃላ ግን ተሻረና “አምስት ግልጽ የሆኑ ጥቢዎች…” በሚል ተተካ፤ መልእክተኛው ሲሞቱም (ቅርብ ግዜ በመሻሩ አንዳንድ ያልደረሳቸው ሰዎች ዘንድ) ከቁርአን ይነበብ ነበር» ሙስሊም በቁጥር 1452 ዘግበውታል።

አስር የሚለው በአምስት ከተተካ በኋላ “አምስት ግልጽ የሆኑ ጥቢዎች” የሚለው ንባቡ ተሽሮ ህግነቱ ግን የፀና ሆኖ ቀረ ማለት ነው። ይህ አይነቱ ድንጋጌን ሳይሆን ንባብን ብቻ የመሻር የ “ነስኽ” አይነት የኢስላም ሊቃውንት ዘንድ የታወቀ ነው። ስለዚህም በትክክለኛው የኡለማዎች አቋም መሰረት ከአምስት ጊዜ በታች መጥባት እርም አያደርግም።

አንድ ግዜ መጥባት የሚባለው፦ ህጻኑ ጡት ከያዘ በኋላ በግልጽ ጠብቶ በሚስተዋል መልኩ ካቋረጠ አንድ ጊዜ ጠባ ተብሎ ይቆጠራል። አንዳንድ ኡለማዎች ዘንድ ለመተንፈስ ወይም ጡት ለመቀየርም ቢሆን  አቁሞ ከቀጠለ እንደ ሁለት ጥቢ ይቆጥሩታል። ሆኖም የመጥባት ገደብ በግልጽ ያልተቀመጠ በመሆኑ በተለምዶ ወደታወቀው የመጥባት ትርጉም ይመለሳል። በተቃራኒው ይህ አይነቱ ማቋረጥ እራሱን ችሎ መጥባት የሚባል አይሆንም የሚለው ትክክለኛው አቋም መሆኑን ታላላቅ ፉቀሀዕ አስምረውበታል። (አል ሙግኒ 9/194 ፤ ሙግኒል ሙህታጅ 3/417)

ታላቁ የፊቅህ አዋቂ ሸይኽ ሙሀመድ ቢን ሷሊህ አል ዑሰይሚን እንዳሉት፤ አንድ ጥቢ ማለት አንድ ማእድ እንደማለት ነው። በተለያየ ግዜ (መጅሊስ) የጠባ መሆኑ መስፈርት ነው ብዬ አምናለሁ፤ በአንድ ግዜ ጥቢ እያቋረጠ ቢቀጥል አንድ ጥቢ ነወ የሚባለው። ጥንቃቄ ከማድረግ አንጻርም የተሻለው አቋም ይህ ነው በማለት አብራርተዋል። (ኑሩን አለደርብ ቅጽ 19 ገጽ 2)

   በዚህም መሰረት ህፃኑ ጠብቷል ለማለት በማያሻማ መልኩ አምስት ጊዜ የጠባና በራሱ ጊዜ የተወ መሆኑ መስፈርት ነው። ቅጽበታዊ ማቋረጦችም ቁጥር ውስጥ አይገቡም። ከአምስት ግዜ በታች የሆነ ጥቢ ግን መስፈርት ያልተሟላበት ነውና ተፅዕኖ የለውም።


¯ የጥቢ መዛመድ እንዲከሰት እድሜው ከሁለት አመት ያልበለጠ ህጻን አምስት ግዜ መጥባት አለበት። እነዚህ ሁለት መሰረታዊ መስፈርቶች ባልተሟሉበት ሁኔታ የተፈፀመ መጥባት ከሆነ ምንም አይነት የመዛመድና እርም የማድረግ ተፅዕኖ አያሳድርም።

የጥቢ ዝምድና (ረዷዓህ) እና መስፈርቶቹ

የጥቢ ዝምድና (ረዷዓህ) እና መስፈርቶቹ

ምስጋና ለአላህ የተገባ ነው። የአላህ ሰላምና እዝነት በመልዕክተኛው፣ በቤተሰቦቻቸውና በባልደረቦቻቸው ላይ ይሁን።

    ሙስሊም የሆነ ሰው ኢስላማዊ ህጎችን ማወቅና መረዳት እንዲሁም መውደድ አለበት፤ አምላካችን አላህ ጥበበኛ ነውና ለእኛ የበለጠ የሚበጀውን ያውቃል። እንደ ኢስላም፤ ከአንድ እናት ጡት የጠቡ የተለያዩ ሰዎችን የሚያስተሳስር ዝምድና አለ።  ይህ ዝምድምናም የስጋ ዝምድና እንደሚከለክለው ከጋብቻ ይከለክላል። የጥቢ ዝምድና  እና ትስስርን ተከትለው የሚከሰቱ ተያያዥ ፈቃዶች እና ክልከላዎች ስላሉ ህግጋቱ መታወቃቸው ግድ ይሆናል። ህግጋቱ  ባልታወቁበት ሁኔታ ሊፈጠሩ የሚችሉትን ቤተሰባዊና ማህበራዊ ቀውሶች ማስተዋል አይከብድም። የጥቢ ዝምድና  ድንጋጌ በቁርአን በሱና የተረጋገጠ ከመሆኑም ባሻገር በሙስሊም ሊቃውንትም አጠቃላይ ስምምነት ኢጅማዕ የተደገፈ ነው። አላህ ለጋብቻ እርም የሆኑብንን ሴቶች ሲዘረዝር እንዲህ ብሏል፤

( وَأُمَّهَاتُكُمُ اللَّاتِي أَرْضَعْنَكُمْ وَأَخَوَاتُكُمْ مِنَ الرَّضَاعَةِ ) [النساء: 23].
«አነዚያ ጡት ያጠቧችሁ እናቶቻችሁ፣ የጥቢ እህቶቻችሁም..»  ኒሳዕ 23

በሌላ አንቀጽ እንዲህ ብሏል፤
 (وَإِنْ تَعَاسَرْتُمْ فَسَتُرْضِعُ لَهُ أُخْرَى) [الطلاق: 6].
 «ለእናንተም (ልጆቻችሁን) ቢያጠቡላችሁ ምንዳዎቻቸውን ስጧቸው፡፡ በመካከላችሁም በመልካም ነገር ተመካከሩ፡፡ ብትቸጋገሩም ለእርሱ ሌላ (ሴት) ታጠባለታለች።» አጦላቅ 6

በሌላም አንቀጽ እንዲህ ብሏል፤
 (وَإِنْ أَرَدْتُمْ أَنْ تَسْتَرْضِعُوا أَوْلَادَكُمْ فَلَا جُنَاحَ عَلَيْكُمْ) [البقرة: 233].
«ልጆቻችሁንም ለሌሎች አጥቢዎች ማስጠባትን ብትፈልጉ ልትሰጡ የሻችሁትን በመልካም ኹኔታ በሰጣችሁ ጊዜ (በማስጠባታችሁ) በእናንተ ላይ ኃጢኣት የለባችሁም፡፡» አልበቀራህ 233

የማጥባት ትስስር ህግ አላህ ያዘዘውና የደነገገው ለመሆኑ እነዚህ በቂና ግልጽ ቁርአናዊ ማስረጃዎች ናቸው። በተመሳሳይ መልኩም ግልጽ የሆኑ ሀዲሳዊ መረጃዎችን እናገኛለን።

عن عائشة -رضي الله عنها- أن عمها من الرضاعة يسمى أفلح استأذن عليها فحجبته فأخبرت رسول الله - صلى الله عليه وسلم - فقال لها: "لا تحتجبي منه فإنه يحرم من الرضاعة ما يحرم من النسب" رواه البخاري ومسلمٌ

የምእመናን እናት አዒሻ ባስተላለፈችው ሀዲስ አፍለህ የተባለ በማጥባት አጎቷ የሆነ ሰው ለመግባት አስፈቀደና ተከለለችው፤ ይህንን ለመልዕክተኛው ስትነግራቸው “ከእርሱ አትከለይ፤ ምክንይቱም በዝምድና እርም የሆነ በጥቢም እርም ይሆናል” አሏት። ሀዲሱ በቡኻሪ ቁጥር (4941) እና በሙስሊም (1445) ተዘግቧል


 عن ابن عباس رضي الله عنهما قال: قال رسول الله - صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ - في بنت حمزة: (إنها لا تحل لي، إنها ابنة أخي من الرضاعة، ويحرم من الرضاعة ما يحرم من الرحم)  رواه البخاري ومسلم

ዓሊይ አቢ አቢጧሊብ የሀምዛን ልጅ እንዲይገቡ የአላህ መልዕክተኛን ሲጠይቃቸው፤ «እርሷ አትፈቀድልኝም! እርሷ የጥቢ ወንድሜ ልጅ ናት፤ በዝምድና እርም የሆነው በጥቢም እርም ይሆናል» በማለት መለሱለት። በቡኻሪ ቁጥር (5100) እና ሙስሊም (1447) ከኢብኑ አባስ ተዘግቧል።

በጥቅሉ በዝምድና ምክንያት እርም የሆነ በጥቢም እርም ይሆናል” የሚለው የመልዕክተኛው ንግግር ከምእመናን እናት አዒሻ፣ ከአሊይ፣ ከኢብኑ አባስ እና ከሌሎችም ተዘግቧል። ስለዚህም የማጥባት ትስስር፤ ጋብቻን ከመከልከልና እርም ከማድረግ፣ እይታን ልቅ ከማድረግ እንዲሁም ከሴቷ ጋር ለብቻ ከመገለል አንፃር ተፅእኖ እንዳለው ኡለማዎች ሁሉ ተስማምተውበታል።

ሙስሊም ሊቃውንትም አጠቃላይ ስምምነት ኢጅማዕ ያለበት ስለመሆኑ በርካታ የፊቅህ አዋቂዎች ያጸደቁት ሲሆን፤ ኢብኑል ሙንዚር፣ ኢብኑ ሀዝም እና ሙወፈቅ ኢብኑ ቁዳማህ ይገኙበታል።
(አል ኢጅማዕ ግጽ 77 ፣ መራቲበል ኢጅማዕ ገጽ 67 አልሙግኒ 9/191 ይመልከቱ)

የጥቢ ዝምድና  ብይንና ተጽዕኖ

      የጥቢ ዝምድና ከጋብቻ ጋር በተያያዘ የዘር ዝምድና ያለውን ብይን ይጋራል። ማለትም የጥቢ ዝምድና ጋብቻን ከመከልከል፣ መህረም ከመሆን፣ ለብቻ ከመገለል እና ሴትን ከማየት አንጻር ተጽዕኖ አለው። የጥቢ ዝምድና  የቅርብ ዘመድ ከማድረጉ ባሻገር ለጋብቻ እርምነትንም ጽኑ ያደርጋል። በስጋ ዝምድና አንድ ወንድ ልጅ በእናቱ ምክንያት ለጋብቻ እርም የሚሆኑበት የእናቱ ቤተሰብ የሆኑ ሴቶች ሁሉ በማጥባት ዝምድናም እርም ይሆኑበታል። የጥቢ ዝምድና በአብዛኛው አጥቢዋ ሴት በማጥባቷ ምክንያት የምታገኘውን እናትነት መሰረት አድርጎ የሚከሰት ዝምድና እና ትስስር ነው። ዝምድናው በአብዛኛው በአጥቢዋ በኩል እንጂ በጠቢው ህጻን በኩል የሚሰራጭ አይደለም። የሚጠባው ህጻን አድጎ ልጆች ካፈራ አጥቢዋ ለልጆቹ አያት ከመሆንዋ በቀር ዘመዶቹን እና ዘመዶቿን ሁሉ አያስተሳስርም። ይህ በመጥባት ዝምድና ዙርያ ብዙዎች የሚስቱት መሰረታዊ መነሻ ነው።

የጥቢ ዝምድና ፍቃዶች እና ክልከላዎች

የጥቢ ዝምድና  ከጋብቻ ጋር በተያያዘ ሁለት አይነት ትጽዕኖዎችን ይፈጥራል።
ክልከላ፦ አላህ ለጋብቻ እርም የሆኑብንን ሴቶች ሲዘረዝር እንዲህ ብሏል፤

«አነዚያ ጡት ያጠቧችሁ እናቶቻችሁ፣ የጥቢ እህቶቻችሁም...» ኒሳዕ 23

በዚህናበዝምድና ምክንያት እርም የሆነ በጥቢም እርም ይሆናል” በሚለው የመልዕክተኛው ንግግር መሰረት የስጋ ዝምድና ክልክል የሚያደርገውን ሁሉ የጥቢ ዝምድናም እርም ያደርጋል። ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው አጥቢ ሴት ልክ እንደ እናት ትቆጠራለች፤ ክልከላው መሰረት የሚያደርገዉም እሷን ነው። ስለዚህም እሷ ላጠባችው ልጅ እሷና በስጋ ዝምድና ምክንያትከእናቱ ጋር በተያያዘ እርም የሚሆኑበት ሁሉ በአጥቢዋ እናቱም በኩል ክልክል ይሆኑበታል። በማጥባት ተጽዕኖ ምክንያትአንድ ወንድ ላይ ከጋብቻ እርም የሚሆኑበትን ሴቶች በሚከተለው መልኩ መዘርዘር ይቻላል፤
አጥቢዋ
የአጥቢዋ እናት (የጥቢ አያቱ)
የአጥቢዋ ባል እናት (የጥቢ አያቱ)
የአጥቢዋ እህት (የጥቢ አክስቱ)
የአጥቢዋ የባልዋ እህት (የጥቢ አክስቱ)
የአጥቢዋ ልጆች (የጥቢ እህቶቹ)
የአጥቢዋ የልጅ ልጆች (በጥቢ የእህቶቹ ልጆች)

ፈቃድ፦ በአንድ ሰውና እንደ እናትና ልጅ ባሉ ቅርብ ዘመዶቹ መካከል የሚፈቀድ እንደ መመልከት ለብቻ መገለልና የመሳሰሉ ፈቃዶች ሁሉ የጥቢ ዝምድናንም ተከትለው ይፈቀዳሉ።  ሆኖም የጥቢ ዝምድና  የስጋ ዝምድናን ያክል የጠነከረ አይደለምና ውርስን፣ የቀለብ ግዴታነትን እና የመሳሰሉ ድንጋጌዎችን ሁሉ አያጋራም:: (አልሙግኒ 9/191)