Tuesday, 21 February 2017

ጠቃሚ ነጥቦች ለትዳር !

ጠቃሚ ነጥቦች ለትዳር !


        ሁልግዜም ቢሆን በትዳር ውስጥ ችግሮች መፈጠራቸው አይቀርም። አልፎ አልፎ በባልና በሚስት መካከል መጨቃጨቆች ሊፈጠሩ ይችላል። እነዚህ ሁኔታዎች በሁሉም ትዳር ውስጥ የሚከሠቱ እና የሚጠበቁ ነገሮች ናቸው። በመነሻ ላይ ብዙም ጉዳት ላይኖራቸው ይችላል። እየተደራረቡ ስሄዱ ግን የትዳሩን ህልውና የሚፈታተን ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላሉ። በትዳር ህይወት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራሉ።

    በዚህ ወቅት ባልና ሚስት የትዳራቸውን ህልውና ለመታደግ እና መሠላቻቸትን ለማስቀረት የመፍትሄ እርምጃዎችን መውሠድ ይኖርባቸዋል። የሚከተሉት ምክረ-ሐሳቦች ትዳር ሁልግዜም ጣፋጭ ሆኖ እንዲቀጥል ይጠቅማሉ።

1 ፍፁም እና እንከን የለሽ ትዳር የለም። ባልና ሚስት ይህን ማወቅ አለባቸው። የሁሉም ሠው ትዳር ሠላማዊና ጭቅጭቅ አልባ የነርሱ ትዳር ብቻ በጭቅጭቅ የተዋጠ እንደሆን ማሠብ አይኖርባቸውም። አልፎ አልፎ የሚከሠቱ ጭቅጭቆችና አለመግባባቶች በየትኛውም ትዳር ውስጥ ሊኖር የሚችል የትዳር ህይወት አንድ ገጽታ ነወ። ይህ መገንዘብ ይጠቅማል።                                                                                      

2 አለመግባባቶች ሲከሰቱ ወደ ከረረ ጭቅጭቅ ቁመት ከመጨመራቸው በፊት ገለል ማለት በጣም ጠቃሚ ነው። ነገሮች ረጋ ብሎ በሠከነ መንፈስ ለማሰብ እና ልዩነቶችን ለማብረድ ይረዳል።                                       

3 ባልና ሚስት በመካከላቸው አለመግባባት ሲፈጠር ለራስ ጠበቃ የመቆም ዝንባሌ ማስወገድ ይኖርባቸዋል። ስህተቱን ማመን እና በስህተቱ የተፈጠረውን ችግር ኃላፊነት ችግር መቀበል እንዲሁም ጭቅጭቆችን ማለሥለስ ፣ በጭቅጭቅ ወቅት ለትዳር አጋር ፍቅር ለማሳየት መሞከር ፈተናዎችን ለመሻገር ይረዳል፤ ትዳርንም ጣፋጭ ያደርጋል።                                                                                       
4 ህይወትን በቁም ነገር ኮምጠጥ ባለ ነገሮች ብቻ  እንድትቀጥል ማድረግ ያስቸግራል። ስለሆነም ከሐራም በራቀ ሁኔታ በቤት ውስጥ የተፍታታ እና ቀለል ያለ የሚያዝናና ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል። ባልና ሚስት በየግዜው በጋራ ዘና የሚሉበት ፕሮግራም ሊኖራቸው ያስፈልጋል።                                                                

5 ባልና ሚስት ሁሌም ሊነጋገሩ ይገባል። በግልፅና በመደማመጥ የመነጋገር ባህል ማዳበር አለባቸው፤ ይህ ባህል በሠላምና በፍቅር ግዜ ብቻ ሳይሆን ፣ በአለመግባባትና በጭቅጭቅ ግዜም ሊታይ ይገባል። መነጋገር የማይችሉ ባለትዳሮች ደስታ አኖራቸውም፤ የትዳር ዕድሜው አጭር ይሆናል።                                           

6 ባለትዳሮች አንዳንድ ነገሮች በጋራ የማድረግ ወይም የማዘውተር ልምድ ማዳበር እጅጉም ይጠቅማቸዋል። አብሮ ቁርዓን (ማዳመጥ)፣ አብረው ጉዞ ማድረግ፣ አብረው ገባያ መውጣት፣ አብረው መመገብ…..                                                                                                                                                      
7 ስህተቶችን ሁሉ በትዳር አጋር ትካሻ ላይ ማሳረፍ ጭቅጭቆች እንዲዳብሩ ስለሚያደርግ ከዚህ መራቅ ያስፈልጋል።የትዳር አጋር ራሱን ማስረዳት እንዲችል ዕድል ሊሠጠው /ሊሰጣት ይገባል።                                         

8 ባለትዳሮች ለትዳራቸው በቂ ትኩረት መስጠት አለባቸው፤ ትዳራቸውን እንደ ህይወት ሊመለከቱት ይገባል። ብዙ ግዜ የባል ወይም የሚስት ትኩረት ትዳር ላይ መሆኑ ቀርቶ ስራቸው ወይንም ትምህርታቸው ላይ ሲሆን ችግሮች መፈጠር ይጀምራሉ። ይህ እንዲሆን መፍቀድ የለበትም። ስራ ወይንም ትምህርት ሊሠጣቸው ይገባል። ነገር ግን ትዳርን እና የትዳር አጋርን ወደ ማስረሳት ደረጃ ከፍ ሊሉ አይገባም። የትዳር አጋር በቂ ትኩረትና ግዜ ሊያገኝ የግድ ይላል።                                                                         

9 በትዳር ውስጥ በሁሉም ጉደይ ላይ ስሞታ ማቅረብ መሠላቸትን ይፈጥራል፤ ለትዳር ጠቃሚ አይደለም። ማሳለፍ ባህል መሆን አለበት።                                                                                                              

10 የትዳር አጋራችን ራሱን እንዲሆን መፍቀድ መቻል አለብን፤ የትዳር አጋራችን በሁሉ ነገር የእኛን ፍላጎት እንዲከተል እና ማንነቱን እንዲቀይር ማስገደድ የለብንም።

11 አክብሮት መለዋወጥ ለባለትዳሮች መሠረታዊ ነገር ነው። ፀያፍ ቁስል የሚፈጥሩ ቃላቶችን በትዳር አጋር ላይ ከመሠንዘር መቆጠብ ያስፈልጋል። በተለይ ይህ ነጥብ በንዴት እና በጭቅጭቅ ወቅቶች ሊተኮርበት ይገባል።

وَقُل لِّعِبَادِي يَقُولُوا الَّتِي هِيَ أَحْسَنُۚ إِنَّ الشَّيْطَانَ يَنزَغُ بَيْنَهُمْۚ إِنَّ الشَّيْطَانَ كَانَ لِلْإِنسَانِ عَدُوًّا مُّبِينًا [17:53]


‹‹ለባሮቼም በላቸው፡- ያችን እርሷ መልካም የኾነችውን (ቃል) ይናገሩ፡፡ ሰይጣን በመካከላቸው ያበላሻልና፡፡ ሰይጣን ለሰው ግልጽ ጠላት ነውና፡፡ ›› /ኢስራእ 53/ 

No comments:

Post a Comment